ድርጅቱ የኮሌራን በሽታ ሥርጭት በ90 በመቶ ለመቀነስ ማቀዱን ገለጸ

የዓለም የጤና ድርጅት እና አጋሮቹ የኮሌራን በሽታ ስርጭት እኤአ በ2030 90 በመቶ ለመቀነስ ማቀዱን አስታወቀ ፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት በሰኔጋል የነበረውን የበሽታው ስርጭት ሙሉ በሙሉ ማስቆም መቻሉን ገልጾ አሁንም ስርጭቱን የምናስቆምበት መሳሪያ አለኝ ብሏል፡፡

ንፅሕና አለመጠበቅ ጦርነት እና ርሃብ  ዋና ዋና የበሽታው መንስኤዎች መሆናቸውን ቢቢሲ የመንን ለአብነት ጠቅሶ በጤና አምዱ ላይ ዘግቧል፡፡

ይህው የኮሌራ በሽታ የከፋ የሚያደርገው ከሌሎቹ በሽታዎች በተለየ መልኩ ቶሎ ህክምና ካልተደረገበት ጊዜ አይሰጥም፤ በሰዓታት ውስጥ ለህልፈተ ህይወት ይዳርጋል፡፡

እንደዘገባው ከሆነ የመን በተከታታይ ዓመታት የጦር ምድር በመሆኗ በሽታው በፍጥነት በመዛመት የዜጎቿን ህይወት ቀጥፎባታል፤ በርካቶቹንም በጣረሞት እያሰቃየባት ይገኛል፡፡

በሃገሪቱ ብቻ ከ770ሺህ በላይ ሰዎች የበሽታው ተጠቂዎች ናቸው፤ 2ሺዎቹ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አብዛኞቹም ህፃናት ናቸው፡፡

ከየመን በተጨማሪ ህንድ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ እና ሃይቲ  ዜጎቻቸው በበሽታው ከተጠቁባቸው ሃገራት መካካል ተጠቅሰዋል፡፡

ይህው በሽታ በኢትዮጵያ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ወይም አተት በመባል ይታወቃል፤ ባለፈው ዓመት በሽታው በሃገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች  ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል፤ ምንም እንኳን በቀላሉ መቆጣጠር ቢቻልም ፡፡

ይህው በቀላሉ መከላከል የሚቻለው እና ድንገት በወረርሺኝ መልክ እየተከሰተ የበርካቶችን ህይወት የሚቀጥፈውን በሽታ ሥርጭቱን ለመግታት የዓለም የጤና ድርጅት፣ የዓለም መንግስታት፣ በጎ አድራጊዎች እና ሌሎች በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በጋራ በመሆን በሚቀጥሉት 12 ዓመታት የበሽታውን ሥርጭት 90 በመቶ ለመቀነስ ማቀዳቸውን ተሰምቷል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንዳሉት ከሆነ በኮሌራ ምክንያት እያለፈ ያለውን ህይወት እጃችን ላይ ባሉ መሳሪያዎች መከላከል እንችላለን፣ ፍኖተ ካርታው ላይ እንዳለው በክትባት፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት በማሳደግ፣ ንፅህናን በመጠበቅ ስርጭቱን መቆጣጠር እንችላለን ብለዋል፡፡

የድርጅቱ የኮሌራ ፕሮግራም ሃላፊ ዶክተር ዶሚኒክ ሌግሮስ በበኩላቸው በሴኔጋል የነበረውን የበሽታውን ስርጭት ሙሉ በሙሉ ማስቆማቸውን ጠቅሰው በሽታውን የምንከላከልባቸው መሳሪያዎች በጃችን ላይ አሉ እነሱን ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በተበከለ ምግብና መጠጥ አማካኝነት በሚከሰተው የኮሌራ በሽታ በአለም አቀፍ ደረጃ በየ ዓመቱ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ 2ነጥብ9 ሚልዮኖቹ ደግሞ የበሽታው ተጠቂ ይሆናሉ፡፡( ምንጭ: ቢቢሲና የዓለም ጤና ድርጅት)