ግብፅ ለሱዳኑ ፕሬዝደንት ኦመር አልበሽር የጉብኝት ግብዣ አቀረበች

ግብጽ  ለሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦመር አልበሽር የጉብኝት ግብዣ አቀረበች ። 

በጉብኝቱ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ሁለቱ አገራት የናይል ድንበር ተሸጋሪ ወንዝን በተመለከት ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሱዳን መስማማቷን ተከትሎ አገራቱ ውስጣቸው ቅራኔ አድሮባቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ሁለቱ ሱዳኖች ወደ መለያየቱ ሲያመሩ ለአገራቱ ቅርብ የነበሩ ጎረቤቶቻቸው በአደራዳሪው ኢጋድ በኩል እና በግላቸው ሲያደርጉት በነበረው የማግባባትና የመዳኘት ስራ የግብፅ ሚና ጎልቶ አለመታየቱም ግብፅ ለሱዳን የቅርብ እሩቅ እንድትሆን ያደረገ መሆኑ ይነገራል ፡፡

ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ዳግም ጉርብትናቸውን ለማደስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ያሳዩት አገራቱ አሁን የሻከረው ግንኙነታቸው እየተለሳለሰ የመጣ ይመስላል፡፡

ግብፅና ሱዳን በባህል በፖለቲካው በንግድ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመተሳሰር ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩም ነው የሚነገረው፡፡

ለዚህም ነው ከዚህ ቀደም በመካከላቸው ተጥሎ የነበረው የወጪ እና ገቢ ንግድ ክልከላ እንዲነሳ የተደረገው፡፡

ሱዳን የመንግስታቱን ድርጅት ሪፖርት መሠረት አድርጋ ከግብፅ የምትገዛቸውን የአሳ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ጥላ የነበረውን እገዳም ማንሳቷ ይታወሳል፡፡

የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የሱዳኑን አቻቸውን ወደ አገራቸው መጋበዛቸውም በሌሎች ዘርፎች ላይ ለመስማማትና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ነው ተብሏል፡፡

የፕሬዝደንት ኦመር አልበሽርን የግብፅ ጉብኝት ግብዣን ያቀረቡት በሱዳን የግብፅ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኦሳማ ሻልቶት ከሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሁለቱን አገራት በአህጉራዊ እና በቃጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በጋራ ሊሰሯቸው ስለሚችሏቸው አጀንዳዎቻቸው በሚኒስትሮቻቸው በኩል እንደሚወያዩ እና የመግባቢያ ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙም ተነጋግረዋል ነው የተባለው፡፡

የፕሬዝደንቱ ልዑክ ገብኝት ምናልባትም በህዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመሞ የዘገበው ሱዳን ትሪቡን ነው፡፡

ሱዳንና ግብፅ ከሚያዋስናቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው በተጨማሪ ለአመታት የቆየው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው እና ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲያቸው በተጨማሪ አፍሪካዊ እና የአረቡ አገር ንቅናቄ አንድነታቸውን አጠናክሮ ቆይቷል፡፡