የስኳር በሽታ እንዳይዘን ማድረግ ያለብን ቀላል ቅድመ ጥንቃቄዎች

የስኳር በሽታ እንዳይዘን ማድረግ ያለብን ቀላል ቅድመ ጥንቃቄዎች

በዛሚ 90.1 የሬድዮ ጣቢያ በሚተላለፈው የኢትዮፒካ ሊንክ ኢዲዩቴይመንት ፕሮግራም ላይ የስኳር ህመም ከመከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከል ማድረግ የለሚገቡን እና ቀለል ስለሆኑ ቅድመ የጥንቃቄ ተግባራት ምን እንደሆኑ ተብራርቷል፡፡

ፋስት ፉድ (የተጠባበሱ ምግቦች) በተደጋጋሚ አለመገብ

የሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ እድሚያቸው ከ አስራ ስምንት እስከ ሰላሳ በሚሆናቸው ሶስት ሺህ ሰዎች ላይ ለአስራ አምስት ዓመታት ባደረገው ጥናት  እነዚህን መሰል ምግቦች የሚያዝወትሩት ከማያዘውትሩት በሁለት እጥፍ በስኳር በሽታ የመያዝ እድላቸው ጨምሮ ተገኝቷል፡፡

በየቀኑ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

በሳምንት ለአራት ሰዓት ወይም በየቀኑ ለሰላሳ አምስት ደቂቃ በእግራችን ብንጓዝ በስኳር በሽታ የመያዝ እድላችንን በ ሰማንያ በመቶ መቀነስ እንችላለን፡፡

ሴቶች ላይ በተሰራ ጥናት በሳምንት አንድ ግዜ አንኳን መጠነኛ የሚባል የአካል እንቅስቃሴ ቢያደርጉ በበሽታው የመያዝ እድላቸውን በሰላሳ በመቶ መቀነስ ይችላሉ፡፡

ሌላ በቻይና የተሰራ ጥናት በሳምንት ውስጥ መካከለኛ የሚባል የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በበሽታው የመያዝ እድልን በአርባ በመቶ ይቀንሳል፡፡ ይህም የሆነው የኢንሱሊንን ስራ በጥሩ ሁኔታ እንዲከናወን ስለሚደግፍ ነው፡፡

የቀይ ስጋ አመጋገብን መቀነስ

በሰላሳ ሰባት ሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት ሴቶቹ በሳምንት ለ አምስት ግዜ ቀይ ስጋን ተመግበው በታይፕ 2 ዳያቤቲስ (ስኳር ህምም 2) የመያዝ እድላቸው በሃያ ዘጠኝ በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል፡፡

ቀረፋን መመገብ ማዘውተር

በስለሳ አምስት አዋቂ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት አንድ ግራም ቀረፋ የገባበት ምግብን በቀን ሶስቴ ለተከታታይ አራት ወራት ተመግበው ጨመሮ የነበረው የስኳር መጠናቸው በአስር በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ቀረፋ የኢንሱሊንን እንቅስቃሴ እንደሚጨምር እና የኮሌስትሮል እና የስብ መጠንን ለመቀነስም ይረዳል ተብሏል፡፡

ጭንቀትን መቀነስ

ጭንቀት ለበርካታ በሽታዎች የሚያጋልጥ ነው፡፡ የስኳር ህመም እንዲከሰትም ምክንያት ስለሚሆን በተቻለ መጠን ራስን ከጭንቀት ማራቅ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

በቂ እንቅልፍ ማግኘት

በአንድ ሺህ ሰባት መቶ ወንዶች ላይ በተደረገ ጥናት በቀን ውስጥ ከስድስት ሰዓታት በታች የሆነ እንቅልፍ የሚተኙ ሰዎች በቀን ውስጥ ከስድስት ሰዓታት በላይ ከሚተኙት ሰዎች በስኳር በሽታ የመያዝ እድላቸው በእጥፍ ጨምሮ ተገኝቷል፡፡

የደም ምርመራ ማድረግ

የስኳር መጠንን መመርመር በተለይም ከ አርባ አምስት ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ፣ የክብደት መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች ፣ በቤተሰብ የስኳ በሽታ ያለባቸው እና የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች የስኳር በሽታ ምርመራን ማድረግ ሊወሰድ የሚገባውን ጥንቃቄ ለመውሰድ ያስችላቸዋል፡፡