የተበከለ አየር አዲስ የሚወለዱ ህጻናትን ሳንባናአንጎል ዕድገት እንደሚጎዳ ተገለጸ

  የተበከለ አየር አዲስ በተወለዱ 17 ሚሊየን ህፃናት የሳንባና የአንጎል እድገት ላይ ችግር ፈጥሯል ሲል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኔሴፍ) አስታውቋል፡፡

በአለም ላይ የሚገኙ 17 ሚሊየን ህጻናት የሚኖሩት ከተፈቀደው ንጹህ የአየር  መጠን 7 እጥፍ የሚልቅ የአየር ብክለት ባለበት አካባቢ እንደሆነና ይህም የአንጎልና የሳንባ እድገታቸውን እየጎዳው እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የህጸናት አድን ድርጅት(ዩኒሴፍ) ባለፈው እሮብ ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ከ12 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህፃናት የሚኖሩት በደቡብ እስያ ሀገራት መሆኑን በሳተላይት ምስሎች በመታገዝ በአየር ብክለት ከፍተኛ ጫና የደረሰባቸውን ቦታዎች ማወቅ መቻሉንም ነው ድርጅቱ አክሎ የገለፀው፡፡

የአየር ብክለቱ በዓለም የጤና ድርጅት ለንፁህ አየር ብሎ ካስቀመጠው መስፈርት ከበለጠ ህፃናቱን ንጹህ አየር እንዳያገኙ በማድረግና  የመተንፈሻ አካላቸውን በመጉዳት ዘላቂ ለሆነ የጤና ችግር እንደሚያጋልጣቸው ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የአየር ብክለት ህጻናቱን በአስም፤የሳንባ ምች እና ሌሎች ተመሳሳይ ህመሞች እንዲጠቁ ያደርጋቸዋልም ነው የተባለው፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው በማደግ ላይ ያሉ ህጻናት አንጎል ከአዋቂዎች በበለጠ ትንሽ መጠን ባላቸው መርዛማ ኬሚካሎች ይጎዳል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሰው ደግሞ የህጻናቱ አየር ቶሎ ቶሎ ማስገባትና የሰውነት የመከላከል አቅማቸው ሙሉ በሙሉ አለመዳበር ነው፡፡

 

ወላጆች ልጆቻቸው ለትንባሆ ጭሶች፤ለምግብ ማብሰያነት የሚጠቀሟቸውን ነዳጅና ከሰሎች እንዲሁም ማሞቂያዎች ያላቸውን ተጋላጭነት ሊቀንሱ እንደሚገባና የአየር ብክለት ስለሚያስከትላቸው ጉዳትም የህዝቡን ግንዛቤ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል፡፡  

የህጻናት የመጀመሪያዎቹ 1 ሺህ ቀናት የአንጎል እድገት ጤናማነት በቀሪው የህይወት ዘመን እድገታቸው እና የመማር ችሎታቸው ላይ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታወቃል፡፡

ሆኖም የአየር ብክለት መጨመር ለህፃናቱ ጤንነት አሳሳቢ ስለሆነ ሊታሰብበት እንደሚገባ ዩኒሴፍ ጥሪ አቅርቧል።( ምንጭ: ሮይተርስና ቢቢሲ)