ፕሬዚዳንት ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን ዕውቅና መሥጠታቸው ተቃውሞ እያስነሳ ነው

ፕሬዚዳንት ዶናልድ  ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን ለመጀመሪያ ጊዜ  ዕውቅና መሥጠታቸው ተቃውሞ እያስነሳ ነው ።

ይህን ተከትሎም ከአረብ ሊግ እስከ መላዉ የዓለማችን የሙስሊም ሀገራት፤ ከሀያላን ሀገራት እስከ የአሜሪካ የዉጭ ዲፕሎማቶች የተቃዉሞ ናዳ እየወረደ ነው፡፡

ወትሮም አወዛጋቢ ዉሳኔዎችን ለማስተላለፍ እንግዳ ያልሆኑት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ቃሌ አይታጠፍም በማለት በፈረንጆቹ ታህሳስ 6 2017 ኢየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሰ መዲና ናት ሲሉ መንግስታቸዉ በይፋ እዉቅና መስጠቱን ለዓለም አወጁ፡፡

ቴላቪቭ የሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲ መቀመጫም እሳቸዉ እንደሚሉት ወደ አዲሲቷ የእስራኤል ርዕሰ መዲና ኢየሩሳሌም እንደሚዘዋወር ማረጋገጫ ሰጡ፡፡ ምንም እንኳ ኢምባሲውን ወደ እየሩሳለም ለማምጣት ቀላል ጊዜ ባይፈጅም ትራምፕ በቀጠናዉ ነዉጥን ይቀሰቅሳል በሚል በቀደምቶቻቸዉ ተፈርቶ የነበረዉን ሀሳብ ወደ ተግባር ለማስገባት እየተንደረደሩ ናቸዉ፡፡

የእስልምና፣ የጀዉሽ እና የክርስትና ሃይማኖቶች ቅድስት ከተማ ተደርጋ የሚትታየዉ ኢየሩሳለም  እስራኤል እና ፓሌስታይን በግጭታቸዉ ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ በጋሃድ የሚታወቅ ነዉ፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲና ብለዉ በይፋ በማወጃቸዉ አድናቆታቸዉን እየገለፁላቸዉ ነዉ፡፡ ነገር ግን ሌሎች የአሜሪካ ወዳጆች ፈረንሳይ እና እንግሊዝም ሳይቀሩ ጉዳዩን በአሳሳቢነቱ ይዘዋል፡፡

የፍልስጥኤም ፕሬዚዳንት ማሃሙድ አባስ እንዳሉት ደግሞ አሜሪካ እራስዋን ከአደራዳሪነት ወደ ማጋጨት ተሸጋግራለች በማለት ነዉ የትራምፕን ዉሳኔ የተቹት፡፡ እናም አባስ ፍልስጥኤማውያንና ሌሎች አካላት ለተቃዉሞ አደባባይ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል መላዉ እየሩሳሌምን እንድትቆጣጠር   የሚያደርጋትን ዉሳኔ በመቃወም ችግሩ በድርድር ብቻ እንዲፈታ ሃሳብ እያቀረቡ ነው፡፡

የትራምፕ ዉሳኔ በወግ አጥባቂ የሪፓብሊካን ፓርቲያቸዉ አባላት በርካታ ድጋፍ ብያስገኝላቸዉም የካቢኔ አባላቶቻቸዉን ጨምሮ በርካቶች ኮንነዉታል፡፡ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቴሌርሰን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጃምስ ማቲስ ዉሳኔዉን ከተቃወሙት ዉስጥ ናቸዉ፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን በነጩ ቤት ንግግራቸዉ እንዲህ ሲሉ ዉሳኔያቸዉን አስተላለፉ- አሁን ጊዜዉ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሰ መዲና መሆኗን በይፋ የማሳወቅ ዉሳኔ ላይ የደረስንበት ነዉ፡፡

የቀድሞ ፕሬዝዳንቶቻችን ዉሳኔዉን አክብደዉ በማየታቸዉ እስካሁን እዉን ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡ እኔ ግን ወሰንኩ አሉ፡፡ የትራምፕ ዉሳኔ ወትሮም ቀዉስ የማያጣትን የመካከለኛ ምስራቅን ቀጠና ወደ ሌላ ግጭት እና አለመረጋጋት እንዳያመራት ከወዲሁ ስጋቶችን ፈጥሯል፡፡

በጆርዳን አማን አካባቢ በሚኖሩ የፍልስጥኤም ሰፋሪዎች እና በስታምቡል የአሜሪካ ኤምባሲ አካባቢዎች ተቃዉሞዎች ከወዲሁ መሰማት ጀምረዋል፡፡

ዋሽንግተን የራስዋን ዉሳኔ አስተላልፋ አሁን የእስራኤልን እርምጃ ብቻ በመጠባበቅ ላይ ናት ይለናል የሮይተርስ ዘገባ፡፡ እስራኤል ኢየሩሳሌምን የማትከፈል ከተማዋ በማድረግ የሁሉም ሀገራት ኢምባሲዎች በዚያዉ እንዲሰባሰቡ ፍላጎት አላት፡፡ ፍልስጥኤማዉያን የከተማዋ ምስራቃዊ ክፍል የነፃዋ ፍልስጥኤም መዲና እንዲሆን ይሻሉ፡፡ እስራኤል ይህቺን የኢየሩሳሌምን ምስራቃዊ ክፍል በ1967ቱ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በቁጥጥሯ ስር ብታስገባም እስካሁን ግነ ከዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ዕዉቅና አልተቸራትም፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከፍልስጥኤም ጋር የሚደረግ የትኛዉም ድርድር ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ርዕሰ መዲና ማድረግን ግንዛቤዉ ዉስጥ ያስገባ መሆን አለበት የሚል አቋም ማንፀባረቅ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ያ ደግሞ መላዉ የኢየሩሳሌምን ከተማ ባለቤትነት በእስራኤል ስር የሚያስገባ ነዉ፡፡

የፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት ሞሃሙድ አባስ ኢየሩሳሌም የፍልስጥኤም ጥንታዊ ከተማ ናት ሲሉ ጩኸታቸዉን አሰሙ፡፡ የዮርዳኖሱ ሁሴን ኢቢሽ ደግሞ የትራምፕን ዉሳኔ በመቃወም ከፍልስጥኤም ጎን መቆሟን አረጋገጠች፡፡

 የፍልስጥኤም እስላማዊ ቡድን ሃማስ ትራምፕን የፍልስጥኤምን ወረራ እየደገፉ ነዉ ሲሉ ከሰሱ፡፡ ፍልስጥኤም በቤቴሊሄም የሚበራዉን ማብራት በማጥፋትም ዉሳኔዉን ተከትለዉ የተቃዉሞ ምልክት አሳይታለች፡፡

ቻይና እና ሩሲያ የአሜሪካ ዉሳኔ በቀጠናዉ አደገኛነት ላይ ነዳጅ የሚያርከፈክፍ ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ደግሞ በጉዳዩ ላይ ለመምከር አርብ ለዉይይት ስብብባ ጠርቷል፡፡ (ምንጭ: አልጀዚራ እና ሮይተርስ)