የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ችሎታ በረጅም እድሜ ልምምድ የሚመጣ መሆኑን ጥናት አመላከተ

የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ችሎታ በረጅም ጊዜ የእድሜ ልምምድ የሚመጣ መሆኑን በቅርቡ የወጣ አንድ የአሜሪካ ጥናት አመላክቷል፡፡

የቀዶ ህክምና የህክምና አገልግሎት በተለይም በህክምናዉ አለም ዉስጥ ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዘርፉ ያሉ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ይህንን ጥንቃቄ እና ትኩረት እንዲሁም ችሎታ የሚጠይቅ ስራ በሚገርም ሁኔታ ሲያከናዉኑትም ይስተዋላል፡፡

ታዲያ አልፎ አልፎም ቢሆን በዚህ ሙያ አሳዛኝ አጋጣሚዎች መስማታችን አይቀርም፡፡ በተለይም ደግሞ ከቀዶ ህክምና ጋር የተለያዩ የህክምና ስህተቶችም ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡

ለዚህም ይመስላል በቅርቡ የወጣዉ አንድ የአሜሪካዉያን ጥናት በዚህ ሙያ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች ምንም እንኳን በፅንሰ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ትምህርት የሚሰጣቸዉ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን ከልምድ ማነስ ጋር የሚፈጠሩ ስህተቶች እንደሚያጋጥሙ ነው በመረጃዉ የተጠቀሰው፡፡

የልዩ ቀዶ ህክምና ሃኪሞች የሚኖራቸዉ ክህሎት እድሜያቸዉ በጨመረ ቁጥር ልምዳቸዉ እና ችሎታቸዉ በዛዉ ልክ እንደሚጨምርም ነዉ ጥናቱ ያመላከተዉ፡፡ 

በተለያዩ የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህክምናቸዉን የሚከታተሉ ታካሚዎች የመሞት እና የመዳን እድላቸዉ በቅርብ በሚከታተላቸዉ ወንድና ሴት ሃኪሞች ቢሆን ልዩነት አለዉ ተብሏል፡፡

በሃምሳዎቹ የእድሜ ክልል ዉስጥ ባሉ ሴት ሃኪሞች ክትትል የሚደረግላቸዉ ታካሚዎች የመሞት እድላቸዉ አነስተኛ መሆኑን ነዉ በሎስ አንጀለስ ዴቪድ ጊፈን የሜዲካል ኮሌጅ የህክምና አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ዩሱኬ ሱጋዋ የሚናገሩት፡፡ 

ዶክተር ሱጋዋ እና ባልደረቦቻቸዉ እንደሚሉት በአንድ የቀዶ ህክምና ባለሙያ ስራ ላይ ፆታ እና እድሜ ምን ያህል ልዩነት ሊያመጣ እንደሚችል ያብራራሉ፡፡

ክህሎታቸዉም በዛዉ ልክ በልምድና በእድሜ እያደገ እንደሚሄድ ጭምር፡፡

የቀዶ ህክምና ባለሙያዉ እድሜዉ እየጨመረ በሄደ ቁጥር በእጁ የሚያከናዉኗቸዉን ስራዎች መቀነስ አልያም ከቴክኖሎጂዉ ጋር ራሱን አዋህዶ መቀጠል አለመቻል ሌላዉ ሊያጋጥም የሚችሉ ችግሮች ቢሆኑም፡፡

በጥናቱ እንደአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2011 እስከ 2014 ከፍተኛ ቀዶ ህክምና ያካሄዱ ታካሚዎች ላይ ምልከታ ተደርጓል፡፡

ወደ 46 ሺ የሚጠጉ የቀዶ ህክምና ሃኪሞች ህክምናዉ የተደረገላቸዉ ስምንት መቶ ዘጠና ሁለት ሺ ሁለት መቶ ታካሚዎች ባጠቃላይ በ30 ቀናት ዉስጥ ያጋጠመዉ የሞት መጠን በመቶኛ ሲሰላ 6 ነጥብ4 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የቀዶ ህክምና ሃኪሞች እድሜአቸዉ ከ40 ዎቹ በታች የሆኑት የሞት መጠን 6 ነጥብ 6 በመቶ፣በ40ዎቹ ላይ ያሉት 6 ነጥብ 4 በመቶ፣በ50ዎቹ እና 60 ዎቹ ያሉት ደግሞ ያሉት 6 ነጥብ 3 በመቶ አጠቃላይ የሞት መጠን እንዳጋጠማቸዉ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በሴት እና በወንድ የቀዶ ህክምና ሃኪሞች ላይ ያጋጠመ አጠቃላይ የሞት መጠን ደግሞ በሴቶች 6 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን በወንዶች 6 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ይህ ማለት ግን ታካሚዎች በእድሜ የገፉ የቀዶ ህክምና ሃኪሞችን ይመርጣሉ ማለት አይደለም፡፡ በሃኪሞቻቸዉ ክህሎት ፣ተግባቦት ችሎታ  እና ቤተሰቦቻቸዉ በሚያደርጉት ምርጫ ነዉ አብዛኛዉን ጊዜ ታካሚዎች ቀዶ ህክምና ሃኪሞቻቸዉን የሚመርጡት ሲሉ ነው ዶክተር ዩሱኬ የሚናገሩት፡፡

ያም ሆነ ይህ አሁን የተደረገዉ ጥናት የሚያሳየዉ የቀዶ ህክምና ሃኪሞችን ክህሎት እና ብቃት ለማሳደግ ስልጠናዎችን በተከታታይ መስጠት ወጣት የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን ማስተማርና ክትትል ማድረግ በክህሎት ክፍተት የሚከሰተዉን የሞት መጠን መቀነስ እንደሚያስችል ያሳየ መሆኑን ሲጂቲኤን ያወጣዉ ዘገባ አመላክቷል፡፡