የቻይና ባቡር ኮርፖሬሽን የ283 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የቻይና ባቡር ኮርፖሬሽን እ.ኤ.አ በ2017 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዩአን ወይም 283 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡    

በቻይና መንግስት የሚተዳደረው የቻይና የባቡር ኮርፖሬሽን የተመሠረተው እ.ኤ.አ በ1950 ሲሆን ሲመሠረት በሚኒስትር መሥሪያ ቤትነት ነበር፡፡    

በ2013 ከሚኒስትር መሥሪያ ቤት ወደ ኩባንያ የተሸጋገረ ሲሆን በሃገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ አገልግሎት እየሠጠ ይገኛል፡፡    

ኩባንያው የባለፈው ዓመት ሪፖርት ይፋ ያደረገ ሲሆን የተገኘው ትርፍ 1 ነጥብ 8 ዩአን ወይም 283 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ እና ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገበው ትርፍ በ69 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ነው የተገለጸው ፡፡

የሲአርሲ ገቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ10 አሃዝ ዕድገት ላይ ያለ ሲሆን እኤአ በ2016 አንድ ትሪሊዮን ዩአን ወይም 160 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ በ11 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ኩባንያው ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት 12 ነጥብ 46 ቢሊዮን ዩአን የቅድመ ታክስ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን በ2016 የነበረው የ 1 ነጥብ 17 ቢሊዮን ዩአን ኪሳራን ማስመለስ ችሏል፡፡

ሲአርሲ በ2017 ያስመዘገበው እዳ 272 ቢሊዮን ሲሆን በ2016 ከነበረው የ620 ቢሊዮን ዩአን እዳ ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ተገለጸው፡፡

ሲአርሲ በ2017 ከትራንስፖርት አጠቃላይ ገቢ 694 ነጥብ 3 ቢሊዮን  በማግኘት የ17 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህ እድገት ደግሞ ኩባንያው በ2013 ከሚኒስተር መስሪያ ቤትነት ወደ ኩባንያነት ከተሸጋገረ ቡኃላ የተገኘ ሁለተኛው ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ከመንገደኞች ማጓጓዣ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ ደግሞ 319 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዩአን ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ 13 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የጭነት መጓጓዣ ገቢ በ2016 ከነበረው በ23 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማሳየቱን የኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በዚህ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 2018 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ደግሞ የቻይና ባቡር ኮርፖሬሽን 179 ቢሊዮን ዩአን ገቢ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ የመንገደኞች ማጓጓዣ ገቢ ትልቁን ድርሻ መያዙን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡