የህመም ስቃይ ማስታገስ እና እንክብካቤ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎች ሊተገበር ነው

የህመም ስቃይ ማስታገስ እና እንክብካቤ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎች ሊተገበር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ጀኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ገ/ሚካኤል በህመም ስቃይ ማስታገስ እና እንክብካቤ ዙሪያ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ እንደገለፁት ህሙማን ወደ ጤና ተቋማት ሲመጡ የተሻለ ህክምና በማግኘት የተረጋጋና ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ የህመም ስቃያቸው ማስታገስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከህመም ነፃ ህክምና በ17 ሆስፒታሎች ውስጥ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፥ በዚህ ዓመትም በሁሉም ሆስፒታሎች ህክምናውን ለመተግበር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህመም ስቃይ ማስታገስ እንክብካቤ የሥራ መመሪያ ያዘጋጀና ለጤና ባለሙያዎችም ሥልጠና የሰጠ መሆኑን ዶክተር ዳንኤል ገ/ሚካኤል አስረድተዋል።

ለዚሁ ክምናው እገዛ የሚያደርጉ የመድሃኒት አቅርቦት ግብአቶችን የሚሟላበትን ሁኔታዎች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እያመቻቸ እንደሆነም ነው ዶክተር ዳንኤል የተናገሩት።

ወደፊትም የህመም ስቃይ ማስታገስ እና እንክብካቤ ህክምና በመላው ሀገሪቷ በሚገኙ በሁሉም ሆስፒታሎች እና 3ሺህ800 ጤና ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ የሚተገበር ሲሆን፥ የዘርፉን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሏል።

የአንድ ህመምተኛ ህመም አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ መንፈሳዊ ኢኮኖሚያዊ  እና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚያካትት በመሆኑ ለህመም ስቃይ ማስታገሻ እና እንክብካቤ ህመም ትኩረት ተሰጥቶበት መስራት እንደሚያስፈልግ በኮንፈረንሱ ውይይት ላይ ተነስቷል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)