ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከከተሞች መስፋፋትና የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ገልጸው ጉዳቱን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ድንገተኛ ጉዳቶች ኮሚሽን የበሽታዎችንና ድንገተኛ ጉዳቶች ሥርጭት፣ ስፋትና ክብደት እንዲሁም ሊተገበሩ የሚችሉ የመከላከልና ህክምና ስልቶች እንዲሁም አዋጪ አካሄዶችን ሲያጠና የነበረውን ሪፖርት አቅርቧል፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየቀረፀ ለሚገኘው የተመረጡ የጤና አገልግሎቶች ማዕቀፍ ዝግጅት የኮሚሽኑ ሪፖርቱ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ዶክተር ሊያ ተናግረዋል፡፡

በተላላፊ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ላይ የተመዘገበው መልካም ውጤቶች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ለመድገም በትኩረት እንደሚሰራም ዲኤታዋ ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)