ኢትዮጵያ በሚቀጥለው አመት ሳተላይት እንደምታመጥቅ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት አስታወቀ

ኢትዮጵያ በሚመጣው 2012 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ሳተላይት እንደምታመጥቅ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡

ሳተላይቷ በኢትዮጵያ እና በቻይናውያን ኢንጂነሮች ተሰርታ ግምገማዉን ያለፈች መሆኗን የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ገልጸዋል፡፡

ሳተላይቷ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የምታመጥቅ ሲሆን በአራት ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ሰብስባ እንደሚታመጣ ጠቅሰዋል፡፡

በቆይታዋም ማዕድናት ያሉበትን አካባቢን የመለየትና ቦታውን የማሳወቅ፣ የአየር ንብረት ሁኔታን ማሳወቅ፣ በሀገሪቱ የግብርና ሥራዎች የሚከናወንባቸው ቦታዎችን ለሰብል አመቺ መሆናቸውን የመለየት ስራውን እንደሚታከናወን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

በተጨማሪም ሳተላይቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ በስፔስ ሳይንስ የተሰማሩ ተማሪዎች ዕውቀት ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ወደ ፊት በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እንዲመጥቅ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ለሳተላይቷ የ6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከቻይና እንደተደረገ የገለጹት ዶክተር ሰሎሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢንስትቲዩቱ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የድጋፍ ስምምነቱ እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የስፔስ ሳይንስ ለማሳደግ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡