ዘመናዊ ምስጢራዊ ካሜራ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 28/2008(ዋኢማ)-በዘመናዊነቱ እጅግ የመጠቀ የውጭ ግድግዳ ላይ የሚለጠፍ ምስጢራዊ ካሜራ ተመርቶ ለገበያ ቀረበ፡፡

ካሜራው ኔስት ካም በተሰኘ ኩባንያ የተመረተ ሲሆን የሚፈለገው ቦታ ላይ ለመለጠፍ በጣም ቀላል እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡ ለዚህም ከማግኔት የተሰራ አካል እንደተገጠመለት የኔስት ካም ኩባንያ ምርት ሥራ አስኪያጅ መሁል ናሪያዋላ ይናገራሉ፡፡

ካሜራው 130 ዲግሪ መሽከርከር የሚችል ሲሆን የተለያዩ ክስተቶችን በምስልና በድምፅ ቀርፆ ለሚመለከተው አካል ማስረጃዎችን ያቀብላል፡፡ ካሜራው ከቀን በተጨማሪ በሌሊትም ምስሎችንና ድምፆችን በጥራት ለመቅረፅ የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል፡፡

እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ የተነገረለት ምስጢራዊ ካሜራ በ199 ዶላር ለገበያ መቅረቡን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ሰውና ሌሎች ግዑዝ አካላትን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችለው ሶፍት ዌርም እንደተገጠመለት በዘገባው ተመልክቷል፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሠዓት የሚከናወኑ ውጫዊ ክስተቶችን እየቀረፀ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፡፡ ጫጫታና ሁካታ የበዛባቸው ትዕይንቶችም ጥራት ያለው ምስልና ድምፅን ከመቅረፅ እንደማያዳግቱት ነው የተዘገበው፡፡

ኔስት ካም አውት ዶር የሚል ስያሜ የተሰጠው ካሜራ ድምፅና ምስልን ከመቅረፅ በተጨማሪ ቤት ውስጥ ላለ አካል መረጃዎችን ወዲያውኑ ያስተላልፋል፡፡ ለዚህም ቤት ውስጥ የሚቀመጥ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ካሜራ በዚሁ ኩባንያ አማካኝነት ቀደም ሲል ለአገልግሎት በቅቷል፡፡

ውጭ ከሚለጠፈው ካሜራ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ካሜራ ቤት ውስጥ መቀመጡ መረጃዎችን በፍጥነት ለመቀባበል ያስችላል፡፡ ውስጥ ያለው አካል በውጭ የሚካሄዱትን ክስተቶች በቀላሉ ይመለከታል፤መረጃዎችን ያገኛል፡፡

የካሜራው ለአገልግሎት መብቃት ሰዎች በካሜራው የተቀረፁትን ክስተቶች ራቅ ያለ ቦታ ላይ ሆነውም በስማርት ስልክ አማካኝነት መረጃዎችን በቀላሉ የሚያገኙበት ዕድል ፈጥሯል፡፡ ለዚህ አገልግሎትም በስማርት ስልክ ላይ የሚጫን ሶፍት ዌር የተዘጋጀ ሲሆን የሚጠየቀው የክፍያ መጠንም ተገልፃል፡፡  በመሆኑም ለ10 ቀን 10 ዶላር፣ለወር ደግሞ 30 ዶላር  ወጭ ይጠይቃል ተብሏል፡፡

ካሜራው ሁሉም ሊጠቀሙበት የሚገባ ወሳኝና አስፈላጊ የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤት እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡

ምንጭ፤ ቴክ ኒውስ ወርልድ