ከቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች 977 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኘ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 27/2008 (ዋኢማ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች 977 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

የሚኒስቴሩ የሰብል ምርቶች ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ መሐመድ ለዋልታ እንዳስታወቁት፤የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ  ከ870 ሺ 349 በላይ ቶን ወደ ውጭ አገሮች በመላክ 977 ሚሊዮን 146 ሺ የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡

በበጀት ዓመቱ 354 ሺ 275 ቶን የቅባት እህሎችን በመላክ 563 ሚሊዮን አሜሪካን  ዶላር  ለማግኘት  ታቅዶ  433 ሺ 486 ቶን  ምርት  በመላክ  472 ሚሊዮን 653 ሺ የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን አብራርተዋል፡፡

እንደዚሁም 362 ሺ 646 ቶን የጥራጥሬ ምርቶችን በመላክ 244 ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 375 ሺ 969 ቶን ምርት በመላክ 232 ሚሊዮን 468 ሺ የአሜሪካን ዶላር ገቢ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

በ2007 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች የዘንድሮው በመጠንም በገቢም የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኤክስፖርት አፈፃጸሙ በመጠን ጭማሪ ያሳየበት ምክንያት ምርት በክምችት እንዳይያዝና በወቅቱ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርብ ከክልሎች ጋር የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ በመደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡