ፌስ ቡክ ለማስታወቂያ አጋቾች እጅ አልሰጥም አለ

አዲስ አበባ፣ነሐሴ04/2008(ዋኢማ)- በፌስ ቡክ የሚተላላፉ ማስታወቂያዎችን ለማገት የሚደረገውን ጥረት እያከሸፈ መሆኑን ፌስ ቡክ አስታወቀ፡፡

በዓለም ላይ ከፍተኛ ደንበኞችና ተከታታይ ያሉት ፌስ ቡክ ከማስታወቂያ ቢሊዮን ዶላሮችን ይሰበስባል፡፡

ይህን ለመገዳደር የሚደረጉ ሙከራዎችንም በየጊዜው እያከሸፈ መጥቷል፡፡ ዛሬ ቢቢሲ ያስነበበውም የዚሁ ጥረት አንድ አካል ነው፡፡

 ማስታወቂያዎችን ለማገት(ከዕይታ ለመሰወር) በሥራ ላይ የዋለው ኤዲ ብሎኪንግ ሶፍት ዌር ፌስ ቡክን ለመገዳዳር ከመሞር አልቦዘነም፡፡ ሶፍት ዌሩን በኮምፒውተሮች ላይ በመጫን ማስታወቂያዎችን ከዕይታ ለመሰወር ሙከራ አድርጓል፡፡

ፌስ ቡክ ግን በዚህ አልበገርም ብሏል፡፡ ሶፍት ዌሩ በእኔ ላይ መሰልጠን አይችልም እያለ ነው፡፡

የሶፍትዌሩን ክልከላ በማክሸፍ ደንበኞቹ የሚፈልጉትን ማስታወቂያዎች የሚያዩበትን አቅጣጫ እየተከተለ እንደሆነ የፌስ ቡክ ኩባንያ አስታውቋል፡፡

‹‹የኤዲ ብሎኪንግ ሰፍት ዌር በተጫነላቸው ኮምፒተሮች ላይ የሚጠቀሙ ደንበኞች የሚፈልጉትን ማስታወቂያ እየመረጡ እንዲመለከቱ ማድረግ ችለናል›› ይላሉ የፌስ ቡክ የማስታወቂያ ክፍል ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር አንድሪው ቦስ ዎርዝ፡፡

ለዚህ የሚረዳ ስልትም ነድፈናል ብለዋል፡፡ ማስታወቂያዎቹ በሚፈለገው መጠን ይለቀቃሉ፤ለዕይታ ይበቃሉ፡፡

‹‹ደንበኞች የሚረባውንም፤ የማይረባውንም ማስታወቂያ መከታተል የለባቸውም›› ያሉት ሚስተር ዎርዝ የተመረጡትን ግን የመከታተል ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡

ማስታወቂያ አጋቹ ሶፍትዌር በሞባይል ስልኮች ላይ የተሳካ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ የሞባይል ስልክ ደንበኞች ላሉት ፌስቡክ ትልቅ ድል ነው፡፡ ማስታወቂያዎቹን በብዛት መልቀቅና ማሰራጨት ይችላል፡፡

ፌስ ቡክ በቅርቡ ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ስድስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ከማስታወቂያ መሰብሰቡ ተመልክቷል፡፡

በዓለም 200 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ኤዲ ብሎኪንግ ሶፍት ዌር ይጠቀማ ተብሏል፡፡

ምንጭ- ቢቢሲ