ሰንደቅ ዓላማውን አለማክበር ህገ-መንግስቱን መፃረር ነው!

                                              ዘአማን በላይ
የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዕውን ለማደረግ ውድ የህዝብ ልጆች ባካሄዱት እልህ አስጨራሽና መራር ትግል መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው ባመጡት ህገ-መንግስት ላይም አዲሱን ሰንደቅ ዓላማ በማስመልከት ድንጋጌ አስፍረዋል። በዚህም መሰረት በህገ-መንግስቱ አንቀፅ ሶስት ላይ ሰንደቅ ዓላማውን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሃሉ ብሔራዊ አርማ (ኮከቡና ጨረሮቹ) እንደሚኖሩት በግልፅ ተቀምጧል። ህገ-መንግስተን ተከትሎም በዚህም በ1988 ዓ.ም. በቁጥር 16/1988 “የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ” እንዲወጣ መሰረት ጥለዋል—ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሰንደቅ ዓላማውን ላስረከቡን ውድ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልጆች ክብርና ምስጋና ይግባቸውና። 
ታዲያ ይህን ዕውነታ በሚገባ የተገነዘቡት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰማዕታቱን አደራ ተቀብለው በተለይም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ተሰባስበው አያሌ ሀገራዊ ተግራትን ፈፅመዋል። ዙሪያ መለስ ዕድገትን እያስመዘገቡም ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል። ሰንደቅ ዓላማውን የማንነታቸው መገለጫ በማድረግም በአንድነትና በእኩልነት ዘልቀዋል። 
የኢፌደሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነት መገለጫ ነው። አደሲቷ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች የሚገኙባት ናት። ባለፉት ዓመታት ይህን ልዩነት እንደ ጥንካሬ በመውሰድ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት የተፈጠረው ብሎም ብጥብጥና ሁከት ውስጥ እንዳትገባ ማድረግ የተቻለው ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችልና ዘለቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ ስለተቻለ መሆኑ እሙን ነው። ለዚህም ደግሞ ዋስትናው ህገ-መንግስቱ ነው። 
እርግጥ በህገ-መንግስቱ ሳቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ መብቶች (የግልና የቡድን) በተቀናጀ መልኩ አንዱ የሌላውን በሚደግፍ አኳኋን ተመልሰዋል። በዚህም ብዝሃነትን ለማስተናገድ ችግር የነበሩ በርካታ ጉዳዩች ሊመለሱ ችለዋል። ይህም የሀገሪቱ ልማት ላለፉት 14 ዓመታት ያለ አንዳች ሳንካ ፈጣንና ተከታታይ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አድርጓል።
እርግጥ ባለፉት ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ትሩፋት ሊገኝ የቻለው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት እየተመሩ ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ሌት ተቀን በመስራታቸው መሆኑን ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። 
በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሰረት አድርጎ በመቁጠር በ‘ባንዴራው’ ስር ተጠልሎ ድህነትን ለማሸነፍ ላለፉት ዓመታት ታግሏል። የትግሉ ባለቤትም በመሆን ላይ ይገኛል። ለዚያውም ከዓለም በፈጣን ዕድገት ከቻይና እና ከህንድ ቀጥሎ የልማት ተምሳሌታዊ ማማውን ጫፍ ላይ ሰቅሎ። እናም ድሉን ይበልጥ ለማጠናከር የሚችልበትን በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከአንዴም ሁለቴ ተልሞ ወደ መከከለኛ ገቢ የመገስገስ ራዕዩን ተያይዞታል—ነገሩ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉት ነውና። 
አበው “ለብልህ አይነግሩትም” እንዲሉ፣ በሁሉም የልማት ዘርፎች ከጫፍ እሰከ ጫፍ በመንቀሳቀስ በ‘ባንዴራው’ አጊጦና አሸብርቆ የትናንት የውርደት ምንጩ የሆነውን ድህነት ዛሬ ላይ ድል በመንሳት ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው—የሀገራችን ህዝብ። ብዝሃነቱ የድሉ ምንጭ እንጂ የልዩነቱና የመፋለሱ ምክንያት እንዳልሆነ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት በተግባራዊ ክንዋኔው ያረጋገጠው ይህ ህዝብ፤ ነገም ይህን ጥንካሬውን አጠናክሮ መቀጠሉ አጠያያቂ አይሆንም። 
ይሁንና ከዚህ የህዝቡ ፍላጎት ውጪ በሆነ መንገድ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ፀረ-ሰላም ሃይሎችና እዚህ ሀገር በተጨባጭ በመምጣት ላይ ያለውን ለውጥ የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች በሰልፍ ሰበብ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ለማኮስመን ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ የህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሆነውን መሰረታዊ ጉዳይ አለመቀበል በመሆኑ ከህገ መንግሰቱ ጋር የሚጣረስ ነው። ተቀባይነትም ሊኖረው አይችልም።
እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ህዝቦችና ሃይማኖቶች አንድነትና እኩልነት መገለጫ በመሆን ዜጎች በስሩ ተሰባስበው ዛሬ ላይ ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ነው። ስለ ሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሲነሳ፤ ጉዳዩ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም ከግምት ውስጥ ገብቶ ይመስለኛል። 
ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቡድንም ይሁን በሀገር ደረጃ ከአንድነት ውጪ የሚከናወን ምንም ዓይነት ነገር የለም። አዎ! አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል። አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖሩ ይመስለኛል። 
የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅ መሰባሰቢያ ጥላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ አይካድም። እናም የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ጠብቀው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን የትኛውም ወገን ሊያውቀው የሚገባ ይመስለኛል። 
ሰንደቅ ዓላማው በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የተቀየሰው ህዳሴ መሰረትም ነው። ከዚህ አኳያም ሀገራችን በምጣኔ-ሃብት እንድታድግ፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ብሎም በርካታ ተግባራት ገቢራዊ ሆነው ውጤት ተገኝቶባቸዋል፤ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ። ለዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ፍትህ መረጋገጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተ ይመስለኛል።
ለነገሩ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለውን የአንድነትና የእኩልነት ዓርማን አንግቦ በየደረጃው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ የሚገኘው የሀገራችን ህዝብ አሁን ካለበት “እሱነቱ” መላቀቅና መለወጥ አይፈልግም ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም የቀደምት አበውንና እመውን የስልጣኔ ማንነት እየተመለከተ፣ የሀገሩን የድህነትና የኋላ ቀርነት ግርዶሽን በመቅደድ ወደ አዲስ ማንነቱ ተቀይሮ ለመታደስ የማይፈልግ ዜጋ ይኖራል ብዬ ስለማላስብ ነው። በመሆኑም ህዳሴውን እውን ለማድረግና መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን የሚሻ ዜጋ ሁሉ ከሰንደቅ ዓላማው አንፃር የሚነሱ ማናቸውንም ተግባራት ሊቃወምና የድርጊቱን ፈፃሚዎች በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል ባይ ነኝ።
በአጠቃላይ ሰንደቅ ዓላማውን መቃወም ማለት ቀደም ሲል ያነሳኋቸውንና በአንድነትና በእኩልነት ሊገኙ የሚችሉ ትሩፋቶችን ‘አልፈልግም” ከማለት ባሻገር፤ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መፃረር መሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል። በቅርቡም ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደው የተመከትናቸው ወገኖች ሰንደቅ ዓላማውን ባለማክበር የሚፈፀሙ ተግባራት ከዚሁ አንፃር የሚታዩ ናቸው። ሀገራችን ውስጥ በሚካሄዱ ማናቸውም ሰላማዊ ሰልፎች የሚታዩ የማይታወቁ ሰንደቅ ዓላማዎች የህዝቦችን አንድነት የማይቀበሉ እንዲሁም የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ እኩልነት መብቶችን የሚነፍጉ በመሆናቸው በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ሊኖራቸው ስለማይችል በፅናት ልንታገላቸው ይገባል እላለሁ።