መቆም ለማይችሉ እፎይታን የሰጠ ፈጠራ

መቆም የማይችሉ ሰዎችን እንዲቆሙ የሚረዳ አዲስ ዊልቼር ዕውን ሆነ፡፡ በአሜሪካውያን የተፈጠረው አዲሱ ዊልቸር ለዘመናት በመቆም ችግር ሲሰቃዬ ለነበሩ ሰዎች ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥ ነው የተነገረው፡፡

አዲሱ ዊልቼር በዘይት ኃይል (በሃይድሮሊክ) የሚንቀሳቀስ ሲሆን ተጠቃሚዎቹ እጀታውን በመግፋትና ዘይቱን በመርጨት ከፍ እንዲልና እንዲወርድ ያደርጋሉ፡፡ ዝቅ ማድረግና መቀመጥ ሲፈልጉም ይህንኑ ሥርዓት ይጠቀማሉ፡፡

ዊልቸሩ ሙሉ በሙሉ ብቃቱ ተረጋግጦ ለአገልግሎት ሲበቃ ብዙዎች እንደሚደሰቱ ከፈጣሪዎቹ አንዱ የሆኑት ሚስተር ጌሪ ጎልዲሽ ይናገራሉ፡፡ መቆም የማይችሉ ሰዎች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙበትን ዕድል በመፍጠር ረገድም ቀዳሚው መሆኑን ነው የሚጠቁሙት፡፡

‹‹በእግራቸው ለመቆም ሲቸገሩ የነበሩ ግለሰቦች እፎይ የሚሉበት ቀን ተቃርቧል›› ሲሉም የዊልቸሩን አስፈላጊነት ይገልፃሉ፡፡

ዊልቸሩ ጌሪ ጎልዲሽ፣አንድሪው ሀንሰንና ኤሪክ ኒኬል በተባሉ ግለሰቦች መፈጠሩን ዴይሊ ሜይል አስነብቧል፡፡