በኮንሶ በጥቂት ግለሰቦች የተፈፀመው ህገ ወጥ ድርጊት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ

በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ኮንሶ ወረዳ ሰሞኑን በጥቂት ግለሰቦች የተፈፀመ ህገ ወጥ ድርጊት ሳይባባስ ህዝብና መንግስት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት በቁጥጥር ስር መዋሉን  የደቡብ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡

በዞኑ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ  በሰገን ከተማ በየደረጃው ከተለያዩ  የህብረተሰብ  ክፍሎች  ጋር  ውይይት  እየተደረገ  ነው፡፡

የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ኩሲያ በኮንሶ ወረዳ ጥቂት ቀበሌዎች ሰሞኑን  በጥፋት ኃይሎች   በደረሰው አደጋ  የሰው ህይወት መጥፋቱን፣  በርካታ ቤትና ንብረት  መውደሙንም  ተናግረዋል፡፡ በ10ሺዎች  የሚቆጠሩ ነዋሪዎች  ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ  መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ  ክፍሌ ገብረ ማርያም የጥፋት ቡድኑ ህዝብና መንግስትን በማለያየት የአካባቢው አርሶ አደር በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆን ቢጥሩም በህብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ጥረት ማክሸፍ ተችሏል፡፡

በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና በንብረት ውድመት በክልሉ መንግስት ስም ሀዘናቸውን ገልፀው በአካባቢው ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥም ከህብረተሰቡ ጋር የተጀመሩ  ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ከቤት ንብረታቸው  የተፈናቀሉ  ወገኖችን ወደ  ቀያቸው የመመለስና አስፈላጊው  ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑንም  ኃላፊው  ተናግረዋል፡፡

በሰገን ከተማ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ውይይት የሰገን አካባቢ ህዘቦች ዞን ከተመሰረተ ወዲህ የአካባቢው ብሄረሰቦች ማህበራዊ፣  ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮንሶ አካባቢ ተነስቶ የነበረው የዞን መዋቅር ጥያቄ ህገ  መንግስታዊ  ምላሽ  ቢሰጥም  በጥቂት ኃይሎች  የአካባቢው ሰላምና ልማት መስተጓጎሉን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡

ህገ ወጥ ቡድኑ በአከባቢው ማህበረሰብም ሆነ በብሄረሰቡ ተወላጆች  ላይ  ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማድረሱንም  ነዋሪዎቹ ገለፀዋል ፡፡

ችግሩ ከዚህ በላይ እንዳይባባስ የዞኑ አስተዳደር  ከክልሉና የፌደራል መንግስት ጋር በመሆን ህብረተሰቡን  በማሳተፍ  በተሰራው የተቀናጀ ስራ በአካባቢው መረጋጋት እንዲፈጠር  ማስቻሉን  ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ንብረታቸው የወደመባቸውና ከአካባቢው የተሰደዱ አርሶ አደሮችም በኮንሶ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ  ህገ ወጥ  ቡድኖች  ከመንግስት ጋር ተባበረው ለልማትና እድገት በመስራታቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው እንደነበርም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያሻቸው ነዋሪዎቹ  አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በኮንሶ ወረዳ አንፃራዊ ሰላም  ሰፍኖ  ህበረተሰቡ  ወደ ዕለት ተዕለት ኑሮው  መመለሱን የገለፀው ክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ህዘቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል ፡፡(ኢቢሲ)