ሰሜን ኮሪያ የተሳካ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አደገች

ሰሜን ኮሪያ የትኛውም የዓለም ክፍል መድረስ የሚችል የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራን በተሳካ ሁኔታ ማከናወኗን አስታውቃለች፡፡

ሀገሪቱ የማስወንጨፍ ሙከራው በጃፓን የባህር ክልል ላይ እንደተከናወነ ያስታወቀችው ይህ ሚሳኤል አህጉር ተሻጋሪ ሲሆን ፥ 930 ኪሎ ሜትሮችን ተምዘግዝጓል ነው የተባለው፡፡

ሀገሪቱ ይህን ያህል ርቀት የተጓዘ ሚሳኤል እንዲወነጨፍ ስታደርግም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ብቻ ያስወነጨፈቻቸውን ሚሳኤሎች ብዛት 11 ያደረሰችበትን ሙከራ ማከናወኗ ተነግሯል፡፡

ህዋሶንግ 14 የተሰኘው ይህ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል 930 ኪሎሜትሮችን በአየር ላይ ለመምዘግዘግ 39 ደቂቃዎች ነበር ያስፈለጉት፡፡

ከምዕራባዊ ፒዮንግያንግ የተወነጨፈው ሚሳኤል ከባህር ጠለል በላይ እስከ 2 ሺህ 802 ኪሎሜትር ድረስ በመጓዝም ጃፓን የምጣኔ ሃብታዊ ቀጠና በማለት በለየችው የባህር ክልል ማረፉን ፒዮንግያንግ አስታውቃለች፡፡

ሀገሪቱ  የመወንጨፍ አቅሙ የአሜሪካ የድንበር ወሰንን አልፎ ጥቃት ማድረስ የሚችል የመጀመሪያው የተሳካ አህጉር  ተሻጋሪ የሚሳኤል ሙከራ መሆኑን ገልጻለች፡፡

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃይ ኢን በበኩላቸው፥  የአሁኑ የደቡብ ኮሪያ ሚሳኢል አይ ሲ ቢ ኤም የተሰኘው አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በማጥናት ላይ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ የአሁኑ የሚሳኤል ሙከራ ፒዮንግያንግ ምንያህል የቀጣናው ሀገራት ስጋት እየሆነጭ መምጣቷን በግልፅ ያመለከተ ድርጊት ሲሉ ኮንነውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ በቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ ላይ የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ አፋጣኝ እልባት እንደሚያሻውና በዚህ ዙሪያም በሞስኮ እየመከሩ የሚገኙት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ዢን ፒንግ በሀገሪቱ ላይ ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

አቤ ሀገራቸው በፒዮንግያግ ላይ ጫና ለማሳደር ከአሜሪካ እና ከደቡብ ኮሪያ ጋር ጠንካራ ውህደትን እንደምትፈጥርም አስታውቀዋል፡፡

የጃፓን ካቢኔ ዋና ፀሃፊ ዮሺዴ ሱጋም ከእስከዛሬው የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ለረጅም ደቂቃዎች በአየር ላይ የተጓዘና ብዙ ኪሎሜትሮችንም ያቋረጠ እስካሁን እንዳላጋጠማቸው ነው የገለፁት፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ እና ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር ከሁለት ቀናት በፊት ተገናኝተው መምከራቸው ይታወሳል፡፡( ምንጭ: ሲኤን ኤንና አልጀዚራ )