የቻይናው አየር መንገድ በበረራ ወቅት ሞባይል መጠቀም የሚከለክለውን ህግ ሊያነሳ ነው

የቻይና አየር መንገድ  በበረራ ወቅት መንገደኞች የሞባይል ስልካቸውን እንዳይጠቀሙ የሚከለክለውን ህግ ሊያነሳ መሆኑ ተገለጸ ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በቻይና አየር መንገድ የሚጓዙ መንገደኞች አውሮፕላኑ መሬትን ከመልቀቁ በፊት የሞባይል ስልኮቻቸውን እንዲዘጉ የሚያስገድድ ህግ እንዳለ የሲጂቲኤን ዘገባ ያሳያል፡፡

ይህ መሆኑ ደግሞ በበርካታ መንገደኞች በአየር መንገዱ አሰራር ላይ ቅረታን እንዲያቀርቡ ሲያደርጋቸው ቆይቷል፡፡

አየር መንገዱ ያረቀቀውና  ከቀጣዩ የፈረንጆች ጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚያደርገው ህግ መንገደኞች በበረራ ወቅት የሞባይል ስልኮቻቸውን እንዲጠቀሙ ይፈቅዳል ነው የተባለው፡፡

የቻይና ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እንዳስታወቀው በቻይና አየር መንገድ የሚጓዙ መንገደኞች ሞባይላቸውን እንዲዘጉ የሚያስገድደውን አሠራር የሚሽር ህግ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

በዚህም መሰረት መንገደኞች በበረራ ላይ ሆነው ስማርት ስልኮችን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችና ታብሌቶችን መጠቀም የሚችሉ ይሆናል፡፡

የቻይና ሲቪል አቪዬሽን አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ዙ ታኦ እንደገለጹት ከቻይና አየር መንገድ በተጨማሪም ሌሎች በቻይና የሚገኙ አየር መንገዶች ይህንን ህግ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ያውዝ ስፕሪንግ አየር መንገድ ሌላኛው በቻይና የሚገኝ የአየር መንገድ ሲሆን መንገደኞች በጉዞ ወቅት የሞባይል ስልኮቻቸውን እንዲጠቀሙ የሚፍቅደውን ህግ እኤአ በ2018 መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ይህ ህግ ተግባራዊ መሆኑ በተለይም በአየር መንገዶቹ የሚገለገሉ መንገደኞችን በእጅጉ የሚያስደስት ሆኗልም እየተባለ ነው፡፡

አሁን ድረስ እየተተገበረ በሚገኘውና ሞባይል ስልክን በበረራ ወቅት እንዳይጠቀሙ በሚከለክለው ህግ መሠረት በቻይና አየር መንገዶች የሚደረጉ ረጃጅም በረራዎች አሰልቺ እንደነበሩም በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች እየተገለጸም ይገኛል፡፡

አየር መንገዱ የሞባይል ስልኮችን የመጠቀም መብትን ቢሰጥም ኢንተርኔት ለመጠቀምም ሆነ ጥሪን ለማስተላለፍ የሚያስችል ኔትዎርክ አይኖራቸውም ቢባልም በአውሮፕላኖቹ ላይ በሚገጠም ዋይ ፋይ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ጥረቶች እየተደረጉ ነው ሲል የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡