ጀርመን በሃይድሮጅን የሚሠራ የባቡር ሙከራ በተሳካ ሁኔታ አካሄደች

ጀርመን በዓለማችን የመጀመሪያው በሃይድሮጂን የሚሰራ ባቡሩዋን ሙከራ በተሳካ ሁኔታ አድርጋለች ፡፡

ባቡሩ 300 የሚሆኑ ተሳፍሪዎችን የመጫን አቅም ያለውና በስዓት 240 ኪሎሜትር ይጓዛል ፡፡ በባቡሩ አናት ላይ የተገጠመው ማሽን ሀይድሮጂን እና ኦክሲጅንን ስቦ ወደ ኃይል በመቀየር ወደ ባቡር የውስጥ ክፍል ለሚገኙ ባትሪዎችን ይልካል፡፡

እንደ ግዙፉ የፈረንሳይ ኢንጅነሪንግ ኩባንያው አልስቶም ገለፃ አሁን ላይ በአገሪቱ ያሉ ፈጣን ባቡሮች በመጨረሻ ፍጥነታቸው በስዓት 140 ኪሎሜትር የሚጓዙ ናቸው፡፡

በግዙፉ የፈረንሳይ ኢንጅነሪንግ ኩባንያው አልስቶም የተሰራው ይህ አዲሱ ኮራዲያ አይሌት የተሰኘው በሃይድሮጂን ሀይል የሚሰራው ባቡር ግን ወደ አየር የሚለቀው የውሃ እንፋሎትን ብቻ በመሆኑ በአለማችን የአየር ጠባይ ለውጥ መቀያየር ትልቁን ቦታ የሚይዘውን የካርቦን ልቀትን መቀነስ የሚያሥችል ከመሆኑም ባለፈ የድምፅ ልቀቱም ዝቅተኛና ምንም አይነት የነዳጅና ጋዝ ሽታ የሌለው በመሆኑ ንፁህ መጓጓዥያ አስብሎታል፡፡

ባቡሩ በቀጣይ በጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ባቡሮችን ከገበያው ያስወጣልም ነው የተባለው፡፡ የጀርመን ስድስት የተለያዩ ግዛቶች 60 የሚደርሱ እነዚህን ባቡሮች ለመግዛት ስምምነት ማድረጋቸውም ታውቋል፡፡፡፡

እ.አ.አ ከታህሳስ 2021 ጀምሮ በሀገሪቱ ባሉት ቹክስሃቨን ፣ብሬመርሃቨንና ብክስትሁድ በተባሉ የተለያዩ የጀርመን ግዛቶች በይፋ ስራ ይጀምራሉ ነው የተባለው፡፡

በባቡር የሚጓጓዙ የሀገሪቱ ዜጎች በ4 አመታት ውስጥ በዚህ የመጀመሪያው በሆነው በሃይድሮጂን ኃይል በሚሰራ ባቡር መጓጓዝ ይችላሉ፡፡

በጀርመን ሳክሶኒ ግዛት በቀጣይ ሀይድሮጂንን በመጠቅም በንፋስ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለመስራት መታቀዱም ተገልጿል፡፡

ሌሎች እንደ ዴንማርክ ፤ኔዘርላንድ ፤ ብሪታንያ እና ኖርዌይ ያሉ ሀገራትም ባቡሩን የመግዛት ፍላጎት በማሳየት ላይ እንደሚገኙ ያስነበበው ሲጂቲኤን ነው፡፡