ኡጋንዳ 5ሺህ ተጨማሪ የሰላም አስከባሪዎችን ወደ ሶማሊያ እንደምትልክ አስታወቀች

አልሻባብ ከሶማሊያ ለማጥፋት ኡጋንዳ 5ሺህ ተጨማሪ የሰላም አስከባሪዎችን ወደ ሶማሊያ  እንደምትልክ አስታወቀች ።     

አልሸባብ ከሶማሊያ ለማጥፋት ኡጋንዳ 5 ሺህ የሰላም አስከባሪዎችን ከአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ውጭ ለመላክ መወሰኗን ስታስታውቅ አሜሪካ ደግሞ ወሰድኩት ባለችው የአየር ጥቃት በርካታ ታጣቂዎችን ስለመግደሏ ገልፃለች፡፡

የኡጋንዳ መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ብርጋዴር ሪቻርድ ካርማየር ለሺንዋ እንደተናገሩት ስለአፍሪካ አንድነት የቆምን በመሆናችን በራሳችን ወጭ እና ተነሳሽነት ለሶማሊያ ሰላም መቆማችንን ለማሳየት 5ሺ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማሊያ እናሰፍራለን ብለዋል፡፡

ቃልአቀባዩ ከዚህም በላይ እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ኃይል ለማስፈር ዝግጁ መሆናቸውን ቢናገሩም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እንደሚፈልጉ አልሸሸጉም፡፡ 

ካርማየር በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ አሚሶም አልሸባብን  ለማጥፋት መሥራት እንዳለበት ተናግረው ውስንነት ይታይበታል ያቅሙን ያህል ሊሰራ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙስቬኒ ኡጋንዳ ወደ ሶማሊያ 5 ሺህ ሰላም አስከባሪዎችን እንደምትልክ እቅድ ማውጣቷን የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚንስትር ለሆኑት ዶናልድ ያማማቶ መስከረም ወር ላይ ነው የነገሯቸው፡፡

የኡጋንዳ ጦር በዚህ ያህል ብዛት ወደ ሶማሊያ ማምራቱ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አቅሙን ያጠናክርለታል ተብሏል፡፡

ሞስቬኒ ለሶማሊያ ተልዕኮው ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ቢደረግላቸው ለሰላም ማስከበር ተልዕኮው መሳካት እንደሚያግዝ  ለያማማቶ መናገራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ኡጋንዳ ፣ቡሩንዲ፣ኬንያ፣ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በአሚሶም ተልዕኮ ሰላም አስከባሪ ወታደር ያዋጡ ሀገራት ናቸው፡፡

በተያያዘ ዜና የአሜሪካ መከላከያ ኃይል በርካታ የአልሸባብ ታጣቂዎችን በአየር ጥቃት ገድያለሁ ብሏል፡፡ በአፍሪካ አደገኛ ከተባሉት የሽብር ቡድኖች አንዱ አልሸባብ ሲሆን የዶናልድ ትራንፕ አስተዳደር በተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸመበት ይገኛል፡፡

አሜሪካ ከሞቃዲሾ በስተምዕራብ 160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሰው አልባ የጦር ጀት በወሰደችው ጥቃት በንጹሃን ላይ ያደረስው ጉዳት እንዳለ የጠየቀው የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ ኮማንድ ምላሽ አልሰጠበትም፡፡

ይህ የአሁኑ የአየር ጥቃት በሳምንት ለ2ኛ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የዓለም አቀፉ የሽብር ቡድን አልቃኢዳ ክንፍ በሆነው የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሶማሊያ አለመረጋጋት መንስኤ አልሸባብ ላይ የትራንፕ አስተዳደር በዚህ አመት በተደጋጋሚ የሰው አልባ የጦር ጀቶችን በመጠቀም ጥቃት አድርሶበታል፡፡  አመቱን ሙሉ የዘለቀው የአሜሪካ ጥቃት 15 ያህል መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ሽንዋ እና አሶሼትድ ፕረስ የመረጃው ዋቢ ናቸው፡፡