ናሳ ከመሬት ጋር የሚመሳሰል ፕላኔት ፍለጋ አዲስ መንኮራኩር ሊያመጥቅ ነው

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማእከል /ናሳ/ ከመሬት ጋር የሚመሳሰል ፕላኔት ፍለጋ አዲስ መንኮራኩር ወደ ህዋ ሊያመጥቅ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ናሳ ከመሬት ጋር የሚመሳሰል ሌላ ፕላኔት ፍለጋ አዲስ የሚያመጥቀው መንኮራኩር “ቴስ” የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፥ በመሬት ዙሪያ የሚገኙ ፕላኔቶች ላይ አሰሳ እንደሚያደርግም ተነግሯል።

መንኮራኩሩ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ከዋክብቶችን የብርሃን መጠን በመለካት እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ አዳዲስ ፕላኔቶችን ማግኘት አንደሚቻልም የአሜሪካ የጠፈር ምርመራ ማእከል ናሳ ተስፋ አድርጓል።

ከነዚህ ውስጥም 500 የሚደርሱት ፕላኔቶች ህይወታዉያን ለሆኑ ሁሉ ለኑሮ ተስማሚ ሊሆኑ ይችላሉም ብሏል።

ናሳ ከዚህ ቀደም ለመኖር አመቺ የሆኑ ከመሬት ጋር የሚመሳሰሉ ፕላኔቶችን ለማፈላለግ “ክለፐር” የተባለ መንኮራኩር ሲጠቀም መቆየቱም በመረጃዉ ተጠቅሷል፡፡

ሆኖም ግን አሁን እንደ አዲስ የሚመጥቀው “ቴስ” የተባለው አዲሱ መንኮራኩር “ክለፐር” ከተባለው መንኮራኩር በ400 እጥፍ በሚበልጥ የማፈላለግ ስራ ይሰራል ነው የተባለው።

“ክለፐር” ከተባለው መንኮራኩር ለ9 ዓመታት በነበረው ቆይታ 2 ሺህ 343 ከፕላኔት ጋር የሚመሳሰሉ ነገሮችን ያገኘ ሲሆን ከእነዚህም ወሰጥ 30ዎቹ ከመሬት ጋር የተቀራረበ ቅርጽ እንዳላቸውም ተለይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን “ክለፐር” መንኮራኩር ነዳጅ እየጨረሰ በመምጣቱ እና ስራውንም በአግባቡ መከወን ስለተሳነው “ቴስ” በተባለው መንኮራኩር ተተክቷል።

መንኮራኩሩ አዲሱ ፕላኔት መጠን፣ ክብደት እና አጠቃላይ ይዘቱን ተመራማሪዎቹ ያሳዉቃል ነዉ የተባለዉ፡፡

እነኚህን አካላት ተጨማሪ በማድረግ የተገኙት ፕላኔቶች የሰዉ ልጅ ሊኖርባቸዉ የሚችል ፕላኔቶች መሆናቸዉን ለማረጋገጥ ይረዳል ተብሏል፡፡

በተለይ ደግሞ አንድ ፕላኔት ከፀሃይ በትክክለኛዉ ርቅት ላይ የሚገኝ ከሆነና በቂ የሙቀት መጠን መስጠት የሚችል ከሆነ ውሃማ አካላት የመኖር እድሉ የሰፋ እንደሆነና የሰዉ ልጅ መኖር የሚያስችል እንደሚሆንም ነዉ የተገለፀዉ፡፡

የምርምር ተቋሙ ባቀደዉ ልክ መስራት ከቻለ አዲሱ መንኮራኩር ቴስ በቀጣይ አንድ አመት ዉስጥ ብቻ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ አዳዲስ አለማትን ማግኘት ይችላል ሲል ናሳ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ (ምንጭ፤ ሲጂቲኤን)