የተሻሻሉ መፀዳጃ ቤቶችን በመጠቀም ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል ተገለፀ

በተሻሻሉ የመፀዳጃ ቤቶች በመጠቀም ተላላፊ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሱትን የጤና ችግር መከላከል እንደሚቻልና ለዚህም በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስድስተኛ ጊዜ በአገር ደረጃ ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የመፀዳጃ ቤት ቀን በማስመልከት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደገለፁት በተለይ የተሻሻሉ የመፀዳጃ ቤቶችን በመጠቀም እንደ አተት የመሳሰሉ የወረርሽኝ በሽታዎች የሚያደርሱትን የሞትና የህመም ስቃይ ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ መለወጥ ይገባል፡፡

በአገራችን የጤና ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር ተቀርፆ ተግባራዊ በመደረጉ እንዲሁም በፓኬጆቹ ውስጥ ለግልና ለአካባቢ ጤና አጠባበቅ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ አገርአቀፍ የመሰረታዊ የመፀዳጃ ቤት ሽፋን 72 በመቶ ደርሷል።

ህብረተሰቡ የተሻሻለ የመፀዳጃ ቤት መገንባትን አስፈላጊነት፣ አያያዝ እና በአግባቡ መጠቀምን እንዲያጎለብት በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ በአውቶብስ መናኸሪያዎችና በመሳሰሉት የጋራ መፀዳጃ ቤቶችን መገንባትና ጥቅም ላይ ማዋል ያለውን ጠቀሜታ እንዲረዳ ማድረግ የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል፡፡

የጤናው ሴክተር ለብቻው ይህን ችግር ሊፈታው እንደማይችል የገለፁት ዶ/ር ሊያ በአገር አቀፍ ደረጃ ስምንት የሚሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በጋራ በመቀናጀት በተለይ በከተሞች ያለውን ችግር ለማቃለል አዲስ የአሰራር ቅንጅት በመንደፍ ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሃይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳኘው ታደሰ በበኩላቸው በአገሪቱ በተሻሻለ መፀዳጃ ቤት የሚጠቀሙት ነዋሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን አስታውሰwale::

በተለይ በከተሞች አካባቢ ግንባታዎች ሲከናወኑ ለመፀዳጃ ቤት ግንባታ ትኩረት እንዲሰጥና እንዲሁም የህብረተሰቡ የዘመናዊ መፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ግንዛቤ እንዲጎለብት የማስተማርና ቴክኒካዊ ድጋፍን የማጠናከሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ /መረጃው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው/