በ50 የግልና የመንግሥት ተቋማት ላይ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ ሊካሄድ ነው

በ50 የግልና የመንግስት ተቋማት ላይ ሀገራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ ማድረግ የሚያስችል ጥናት መደረጉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ  ።

ጥናቱ ከሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው 50 የግል እና የመንግስት ተቋማት ውስጥ በተባበሩት መንግስታት የንግድና ዲቨሎፕመንት ተቋም ከፍተኛ ባለሙያዎች የተካሄደ ሲሆን የባለሙያዎቹ ቡድን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ጋር መክረዋል።

ፖሊሲውን ወጥ የሆነ አስተሳሰብ ይዞ አለመፈፀም ፣ በኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ እና በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ መካከል ክፍተት መኖር፣ በተቋማት መካከል የቅንጅታዊ አሠራር ክፍተት መታየት፣ ወጥነት የጎደለው የስራ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የወጪና ገቢ ግብይት በትክክል በቴክኖሎጂ አለመደገፍ የሚሉት ችግሮች በጥናቱ ተገኝቷል።

የሚከለሰው ፖሊሲ በኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና በችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ እንዲሁም ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ቴክኖሎጂዎች እና ሀገራችንን ወደ መካከለኛ ገቢ እንዲወስዳት በሚያደርጉ ተግባራት ዙሪያ ያተኩራል ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር "ፖሊሲው ሀገራችን በለውጥ ጉዞ ላይ ባለችበት ሰዓት መከለሱ ትክክለኛ ሰዓት መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ሀገር በቀል እውቀቶችንና የግሉን ዘርፍ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማየት ይሰራል" ብለዋል ።(ምንጭ: ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር )