ሶማሊያና ኳታር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

ሶማሊያና ኳታር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና በተለያዩ መስኮች አብረው ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

ኳታር በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለማጥፋት በጋራ ለመሥራት  ዝግጁ  መሆኗንም ገልጻለች  ።

የአረብ ሊግ ሀገራት አባል ሆኑት ሶማሊያና ኳታር እኤአ ከ1970 ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ፈጥረው የቆዩ ሀገራት ሲሆኑ  በተለይ ኳታር በንግድ  እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሽብርተኝነት ከሶማሊያ እንዲጠፋ እና ሀገሪቱ የተረጋጋች እንድትሆን የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላሂ ቢን ናስር ካሊፋ አልታሀኒ እና የሶማሊያው አቻቸው ሀሰን አሊ ካሀየር በኳታር ዶሀ ባደረጉት ውይይት መሰረት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ለማጠናከር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በኳታር እና ሶማሊያ መካከል እነዚህ ስምምነቶች ሲፈረሙ ከሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገኙ  ሲሆን የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር  ሼህ አብዱላሂ ቢነ ናስር ቢን ካሊፍ አልታሀኒ  በሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር የተመራውን የልዑክ ቡድን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ሶማሊያና ኳታር አሁን  በዋናነት ከፈፀሟቸው ስምምነቶች እና ከተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ የሀገራቱን የገንዘብ አያያዝ ፖሊሲ ማስተካከልና ከመጠን ያለፈን የግብር አከፋፈል ለማስተካከል በጋራ ለመሥራት ተፈራርመዋል፡፡

በሶማሊያ የኳታር ባለሃብቶችን በማበረታታት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለመሥራት እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሚስችል የመግባቢያ ሰነድም ተፈርሟል፡፡

በሶማሊያ የባህር ላይ ትራንስፖርት እንዲስፋፋ በማድረግ ኢኮኖሚውን ማገዝ ሌላው የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ነው፡፡በንግድ በኢኮኖሚ እና በቴክኒካዊ ጉዳዮች በትብብር መስራትም እንዲሁ የስምምነቱ አካል ነው፡፡

ሶማሊያና ኳታር ወደብን በመጠቀም አብረው ለመልማትና ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድም  ተፈራርመዋል፡፡

በኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ዲፕሎማሲውን ማጠናከር እንደሚገባም በሁለቱ ሀገራት በኩል ታምኖበታል፡፡

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር በሶማሊያ አሁን ላይ እየተከሰተ ያለውን ሽብርተኝነት ለማስቀረት በጋራ  እንደምትሰራ ለልኡክ ቡድኑ ገልፀውላቸዋል፡፡ 

ሁለቱ ሀገራት በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ እና በሶማሊያ ያለውን ቀውስ ለመታደግ በጋራ እንደሚሰሩም ተስማምተዋል  ፡፡(ምንጭ: አልጀዚራ )