የቻይናው “ሁዋጂያን ግሩፕ” በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የኢንዳስትሪ ከተማ ሊገነባ ነው

የቻይናው "ሁዋጂያን ግሩፕ" በኢትዮጵያ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኢንዳስትሪ ከተማ ለመገንባት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

በቻይና የሚገኙ ታዋቂ የቴክኖሎጂ ተቋማት በኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ጀማል በከር ከሁዋጂያን ግሩፕ ፕሬዝዳንት ሁዋሮንግ ዛንግ ከተመራው የተቋሙ አመራሮች ቡድን ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ጉዳዮች ዙርያ መክረዋል፡፡

ምክክሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች በሀገር ውስጥ በሚመረቱበትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ለአፍሪካ ገበያ ለማቅረብ በሚቻልበት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በሚፈጠርበት ሁኔታ እንዲሁም በማምረቻ ተቋማት የሚሰራ የሰው ሀይል ማሰልጠን በሚቻልበት ዙርያ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

ሁዋጂያን ግሩፕ ካለፉት ሰባት አመት ጀምሮ በኢትዮጲያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ ላይ ያለ ተቋም ሲሆን በአሁኑ ስአት አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለቀላል ኢንዱስትሪ ማምረቻ የሚሆንና የስራ እድልን የሚፈጥር የኢንዱስትሪ ከተማ ለመገንባት በሂደት ላይ አንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታው ጀማል በከር መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ለልኡካኑ ገልፀውላቸዋል።

(ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)