ባለሥልጣኑ ለደንበኞቹ የሚሰጣቸዉን አገልግሎቶች ቀልጣፋ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ መቆጣጣሪያ ሥርዓትን ይፋ አደረገ

የፌዴራል ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ለደንበኞቹ የሚሰጣቸዉን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ የመቆጣጣሪያ ሥርዓት የሆነዉን አዲስ እና ዘመናዊ የአሰራር ይፋ አደረገ፡፡

በእዚህ ዘመናዊ እና ለሀገራችን በአይነቱ አዲስ በሆነዉ የአሰራር ሥርዓት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክር አሚር አማን ባደረጉት ንግግር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚሰጣቸዉን አግልግሎቶች አስተማማኝ መሆን እንደሚጠበቅባቸዉ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአምስት አመቱ የጤናዉ ዘርፍ ሊተገብራቸዉ በእቅድ ከያዛቸዉ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች መካከል አንዱ የሆነዉ የመረጃ አብዮት መሆኑን አዉስተዉ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም የጀመረዉን መረጃን በኤሌክትሮኒክ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት የሚከናወኑ ተሞክሮ ይበልጥ ሊበረታታ እና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባዉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል የምግብና መደኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸዉ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አልፎ አልፎ የሚታየዉን የመድኃኒት እጥረት በቋሚነት ለመፍታት እንዲቻል ብሎም የመድኃኒት ምዝገባ ሥርዓቱን የተቀላጠፈና ምቹ ለማድረግ ብሎም መሠረታዊ ለዉጥ ማምጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን አብራርተዋል፡፡

በትላንትናው ዕለት በጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ተመርቆ በይፋ ሥራዉን የጀመረዉ ይህ የኤሌክትሮኒክ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት በመታገዝ ከሚከናወኑት ሥራዎች መካከል ህገወጥ መድኃኒቶችን የመለየትና የማወቅ፣ የመድኃኒት ግዥን፣ የምግብና መድሀኒት ብቃት ማረጋገጫን ማከናወን፣ የምግብ ምዝገባ እንዲሁም የመድኃኒት ምዝገባን ማከናወን ሲሆን ሁሉንም አገልግሎቶች በቀላሉ ካሉበት ቦታ በመሆን በኦንላይን ማከናወን ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ሚኒስቴር)