ዋትስአፕን የተጠቃሚዎችን መልዕክት በመለወጥ ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ የሚያቀርብ አዲስ መተግበሪያ መኖሩ ተደረሰበት

ዋትስአፕን የተጠቃሚዎችን መልዕክት በመለወጥ ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ የሚያቀርብ አዲስ መተግበሪያ መኖሩ ተደረሰበት

ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ሲባልለት የነበረውን ዋትስአፕን ሰብሮ የሚገባና የተጠቃሚዎችን መልዕክት በመለወጥ ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ የሚያቀርብ አዲስ መተግበሪያ መኖሩተደረሰበት።

የመረጃ መረብ ደህንንት (ሳይበር ሴኪዩሪቲ) ባለሙያዎች፤ አንድ መተግበሪያ የዋትስአፕ መልዕክትን በመጥለፍ ተጠቃሚዎች ያላሉትን ነገር እንዳሉ በማስመሰል መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚችል ደርሰንበታል እያሉ ነው።

ኦዴዎ ቫኑኑ የተሰኙ የቴክኖሎጂው ባለሙያ እንደገለጹት፤መሣሪያው ተጠቃሚዎች ዋትስአፕ ላይ የተላላኩትን መልዕክት አጭበርባሪዎች እንደሚፈልጉት ማጣመም እንዲችሉ ዕድል ይሰጣል ተብሏል።

መተግበሪያው አንድ ወገን ለወዳጅ ዘመድ  የሰላምታ መልዕክት ቢልክ ወደ ሐሰተኛ ዜና በመቀየር ለሌላ የዋትስአፕ ተጠቃሚ ወይም ቡድን መላክ ያስችላል ነው የተባለው።

ላስ ቬጋስ ላይ በተካሄደ አንድ የሳይበርሴኪዩሪቲ ምክክር ላይ ይፋ የተደረገው ይህ መመዝበሪያ መሣሪያ 'የኮምፒውተር መዝባሪዎች የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን መልዕክት እንዳሻቸው እንዲጠቀሙበት ያስችላል' ተብሎለታል።

የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ፌስቡክ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

«ሰዎች ዋትስአፕ ላይ የፃፉትን የትኛውንም መልዕክት መቀየር ይቻላል» ይላሉ ኦዴዎ። አልፎም የእውነተኛውን ዋትስአፕ ተጠቃሚ ማንነት መቀየር እንዲሚያስችል ባለሙያው ይናገራሉ።

ሌላ መሰል አጭበርባሪ መተግበሪያ ደግሞ ለሰው 'ኢንቦክስ' ያደረጉትን መልዕክት አስተያየት [ኮሜንት] በማስመሰል ያወጣ  እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው፤ ነገር ግን ፌስቡክ ይህንን መተግበሪያ ማስወገድ መቻሉን  ተናግረዋል።

ይህኛውን የዋትስአፕ መልዕክት ቀማኛነት ለመከላከል ግን ፌስቡክ አቅሙ የለኝም የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው የመረጃ መረብ ደህንንት ባለሙያው ኦዴዎ ይገልፃሉ።

ይህንን መሣሪያ የፈጠሩት ሰዎች ዓላማ ምን ይሆን? ተብለው ለተጠየቁት  ጥያቄ፤  ዋትስአፕ ተጋላጭ መሆኑን ለማሳየትና ደህንነቱን የበለጠ ሊያጠናክር እንደሚገባው ለማሳሰብ ነው ብለዋል።

«ዋትስአፕ ከዓለም ሕዝብ 30 በመቶ ያህሉን ያገለግላል። እኛ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን። ሐሰተኛ ዜና [ፌክ ኒውስ] ትልቅ አደጋ ጋርጦብናል። ሁለን እርግፍ አድርገን ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰል የለብንም።»

ዋትስአፕ የሐሰተኛ ዜና ማስፋፊያ አንዱ መድረክ እንደሆነ ይነገርለታል፤ በተለይ ደግሞ በሕንድ እና ብራዚል። የሃሰተኛ መረጃዎቹ ሥርጭት ግጭት ከማስነሳት አልፎ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል።

ዋትስአፕ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ መላዎችን ቢያቀርብም አደጋው ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ አይመስልም። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)