ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች 142 ሚሊየን ዶላር ገቢ አገኘች

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች 142 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሃና አርያስላሴ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመን 85 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የማምረቻው ዘርፍ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ባለፉት ዓመታት እየቀነሰ ቢመጣም ከማምረቻው ዘረፍ የሚገኘው ገቢ ግን ጭማሪ እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርክ 142 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን በመጠቆም ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።

ገቢውን ካመነጩት ዘርፎች መካከል የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶችና ሌሎች ምርቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ተገልጿል።

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰንሻይን፣ ኪንግደምና አንቴክስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጎብኝተዋል።

በአዲስ አበባ የቻይና አምባሳደር ታን ጄይን ለኢዜአ እንደተናገሩት÷ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሏል።

ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የቻይና ባለሃብቶች ተሳትፎ  ጉልህ መሆኑንም ጠቁመዋል።