ሙሾ አውራጅ አምደኞች

ኢብሳ ነመራ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በነሐሴ 14/32ዐዐ3 ህትሙ በገፅ 3 ላይ “መልዕክቱን ትቶ መልዕክተኛውን” በሚል ርዕስ በአልአዘር ኬ የቀረበ ጽሁፍ ማስነበቡ ይታወሳል ፡፡ ጽሁፉ ያተኮረው ከኢትዮጵያ የዕርዳታ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በቢቢሲ የቀረበ ዘገባና መንግሥት ዘገባውን በተመለከተ የሰጠው ምላሽ  እንዲሁም ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ ላይ ነው፡፡አሁን  የረሃብ እና የዕልቂት ዜና የመላው አለም መነጋገሪያ መሆኑን ያስታወሰው ይህ ፅሁፍ፣ በዓለም የምግብ ድርጅት ግምት 11.3 ሚሊዮን የሚሆኑ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሕዝቦች ከ65 ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ረሃብ መጠቃታቸውን ይጠቅሳል፡፡ በዚህ አስከፊ የረሃብ ጉዳይ ላይ ሶማሊያ የታላላቅ የዜና ምንጮች ትኩረትን  ከኢትዮጵያ መረከቧንም ይገልፃል፡፡

የአለም የዜና ምንጮች የረሀብ ዜና  ከኢትዮጵያ ይልቅ ሶማሊያ ላይ ማተኮር ያስቆጫቸው መሆኑን አገላለፃቸው የሚየሣብቅባቸው አልአዛር ኬ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር ከረጅም ማቅማማት በኋላ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የረሀብ ተጎጂዎች መኖራቸውን ማሳወቁን ገልፀዋል፡፡ሁኔታውን “ኢትዮጵያን ችግሩ ያልነካት ወይም መጣሁብሽ እያለ ሲያስፈራራት ቆይቶ ድንገት እርሷን ትቶ በጀርባዋ ወደ ሶማሊያ ጓዙን ጠቅልሎ ገባ እንዴ እንድንል አድርጓል” ሲሉ ገልፀውታል፡፡ እዚህ ላይ አቶ አልአዛር ለአንባቢያቸው ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት የኢትዮጽያ መንግሥት በኢትዮጵያ የተከሠተው ድርቅ ያስከተለውን ችግር ደብቆታል የሚል ነው፡፡

በቅድሚያ የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ሶማሊያ ላይ ማተኮሩ በራሣቸው በመገናኛ ብዙሃኑ የተወሰነ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ድርቅና ረሀብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ላይ ያተኩር የነበረው ወደ ሶማሊያ መዞሩም በኢትዮጵያም በሶማሊያም ውሣኔ የተደረገ ሣይሆን አስከፊ ረሀብ የተከሰተው በሶማሊያ በመሆኑ የተፈጠረ ሁኔታ ነው፡፡ ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ የአድማጭ ተመልካቻቸውን ቀልብ የሚስብ የተለየ ነገር ስለሌለ ነው ለሶማሊያ ሠፊ የዘገባ ሽፋን እንዲሰጡ ያደረጋቸው፣ በቃ፡፡ አቶ አልአዛር ኬ ደግሞ የሌለውንም ቢሆን ለምን አጋናችሁ አታወሩም በሚል የተቆጩ ይመስላሉ እናም ይህን ቁጭትዎን ለራሣቸው ለመገናኛ ብዙሃኑ ብታስረዱዋቸው የተሻለ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የግብርና ሚኒስቴር የድርቁን ወሬ ከረጅም ማቅማማት በኋላ ገለፁልን ያሉት ደግሞ ነጭ ውሸት ነው፡፡ ኢትዮጵያን አስከፊ ቸነፈር እንዲመታት የሚፈልጉ ይመስል የዘንድሮውን ድርቅ ዋነኛ መቃወሚያና መኖራቸውን ማሣወቂናያ አድርገው የያዙት ተቃዋሚዎችም መንግሥት ዘግይቶ አሣውቀ አላሉም፡፡ እንዲያውም ክረምቱ ዘግይቶ በመግባቱ ቀድሞም በመውጣቱ የምግብ እጥርት ሊያጋጥም እንደሚችል ከያዝነው አመት መግቢያ ጀምሮ ሲገልፅ መቆየቱ ነው የሚታወቀው፡፡ ያም ሆነ ይህ አልአዛር ኬ በቀጥታ ዘንድሮው ድርቅ ካስከተለው የምግብ እጥረት ጋር ባይገናኝም፣ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያደረባቸውን ቁጭት የሚክስ ነገር አግኝተዋል፤ የቢቢሲን ዘገባ፡፡ ይህንንም “ባለፈው ሰሞን ቢቢሲ ለአለም ሕዝብ አይንና ጆሮ ያቀረበው ፕሮግራም ግን ይህን የሀገራችን ሚዲያዎችና መንግስት የሶማሊያ ችግር ብቻ አስመስለው ለማቅረብ የሞከሩት ጉዳይ ላይ ድንገተኛ አቧራ አስነስቷል” ሲሉ ገልፀውታል፡፡

እርግጥ ነው፣ አልአዛር ኬ ከመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ውጭ ሆነ በሚል ያስቆጫቸው ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት ባይሆንም፣ ቢቢሲ በእርዳታ አሰጣጥ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ ረሃብ አለ ሊያስብል የሚችል ዘገባ አቅርቧል፡፡ ዋናው ነገር የዘገባው መቅረብ ሣይሆን ዘገባውን ለማቅረብ ያነሣሣቸው ምክንያትና ዓላማው፣ የዘገባው ትክክለኛና ሚዛናዊ  መሆን ነው፡፡

የቢቢሲ መርማሪ ጋዜጠኞች ቱሪስት መስለው ከለጋሾች የሚገኝ እርዳታ አጠቃቀም ላይ ዘገባ እንዲሠሩ ያደረጋቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊዘገብ የሚገባ አሣሣቢ ነገር ስላለ ነው የሚለው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡ የእርዳታ አጠቃቀም ላይ ከዚህ ቀደምም ተመሣሣይ ስሞታ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ቀርቦ ራሣቸው የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት የኢትየጵያ ለጋሾች ቡድን በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ምርመራ አካሂዶ ጥቆማው መሠረተ ቢስ መሆኑን አሣውቋል፡፡ እዚህ የለጋሾች ቡድን ውስጥ የቢቢሲ ባለቤት የሆነው የእንግሊዝ መንግስትም አለበት፡፡

ይህ ሆኖ ሣለ፣ የቢቢሲ ጋዜጠኞች አገር አቋርጠው፣ ባህር ተሻግረው በደቡብ የሃገሪቱ አካባቢ ወደምትገኝ አንዲት መንደር እንዲጓዙ ያደረጋቸው ሌላ መነሻ ምክንያት አለ ማለት ነው፡፡ ይህም በያዝነው ዓመት መግቢያ አካባቢ በ1976/77 ኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ ረሃብ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ከለጋሾች የተሰጠው እርዳታ በወቅቱ በትጥቅ ትግል ላይ በነበረው ሕወሃት ለመሣሪያ ግዢ ውሏል የሚል ዘገባ አቅርቦ፣ በመጨረሻም ዘገባው የተሳሳተ በመሆኑ ዕርዳታው ሲከፋፈል በቦታው የነበረውና ዋነኛው የዕርዳታው አሥተባባሪ የነበረውን ሰር ቦብ ጌልዶፍን ይቅርታ እንዲጠይቅ በመገደዱ የተፈጠረበትን ሐፍረት መሸፈኛ ፍለጋ ነው። በወቅቱ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህወሃትንና የኢትዮጵያ መንግስትን በቀጥታ ይቅርታ ባይጠይቅም ሸፍጠኝነቱ ግን  ተጋልጧል። ይህን ሐፍረቱን መሸፈን ነበረበት፡፡

እናም እውነትም ይሁን ሃሰት ግድ ሳይሰጠው አንዳች የሚናፈስ ነገር ይገኝ ይሆናል በሚል ተደብቀው የገቡት መርማሪ ጋዜጠኞች፣ ሊመረምሩ የፈለጉትን የዕርዳታ አጠቃቀም ችግር የት ጋር እንዳለ እንኳን ግንዛቤ የነበራቸው አይመስሉም። የምርመራ ዘገባ ሲሰራ ግን የሚመረመረው ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ማስረጃዎች  በመያዝ  የሚጀመር መሆኑ ይታወቃል፡፡ጋዜጠኞቹ ያደረጉት ከዚህ በተቃራኒ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገቡ በኋላ መንግስት ላይ መቃወሚያ ምክንያት መፈለግን ዋና ስራቸው አድርገው ወደያዙት፣ ትንሹን ነገር ያለ ወጉ አጋነው፣ ቢቻል ፈጥረው ከማውራትና ከማስወራት ወደኋላ የማይሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ሄደው የሚያወሩትን እንዲሰጡዋቸው ነበር የጠየቁት።

ይሁን፣ በተቃዋሚዎች ጥቆማ ምርመራው መሰራቱ በራሱ እንደችግር ላይወሰድ ይችል ይሆናል ። ሆኖም ከዘገባው አጠራጣሪ ጭብጥ ጋር ተያይዞ ሲታይ፣ ዘገባውን ድራማ የሚያስመስለው ነገር አለ። በቅድሚያ የምርመራ ዘገባው ናሙና ያተኮረው ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ፓርቲ በሚንቀሳቀስበት የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ፣ 1700 ሰዎች የሚኖሩበት መንደር ላይ ነው የተባለው። ይህች መንደር በዙሪያዋ ጥጋብ በሞላባቸው መንደሮች መከበቧና፣ ነዋሪዎቿም  በየትኛው ምርጫ እንደሆነ ባይገለፅም ተቃዋሚዎችን መርጠዋል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ  ኢህአዴግ ስላልመረጡት ሊቀጣቸው እርዳታ እንዳያገኙ አድርጓል ነው የተባለው፡፡ ዘገባው አንድ የሰባት ልጆች እናት የሆኑ የመንደሯን ነዋሪ ጠቅሶ ልጆቻቸውን ሳርና አረም ሲመግቡ አይተናል ብሏል። ጋዜጠኞቹ በመንደሯ በቆዩባቸው ሁለት ሳምንት ውስጥም ሰባት የመንደሯ ነዋሪዎች መሞታቸውን መመልከታቸውን ጋዜጠኞቹ በአስረጂነት ጠቅሰዋል።

ይህን የዘገባውን ጭብጥ ልብ ብለን ስናስተውል፣ አጠራጣሪ ሆኖ እናገኘዋለን። በቅደሚያ 1700ሰዎች ይኖሩባታል የተባለችው መንደር ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ተቃዋሚ ፓርቲን ለመምረጣቸው ተጨባጭ ማስረጃው ምንድ ነው? ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲን ነው የመረጡት እንበል። ከነባር የኢትዮጵያ የህዝብ አኗኗር ባህል አኳያ  ሰዎች ሲርባቸው ሳርና ቅጠል ወደመብላት ከመሄድ ይልቅ በቅድሚያ በአቅራቢያቸው ያለን ጎረቤትና መንደር ነዋሪ የሚላስ የሚቀመስ እንዲሰጣቸው ወደ ወደመለመን ነው የሚሄዱት፡፡ ልብ በሉ ዙሪያቸው የጠገቡ፣ መንደሮች አሉ ብሏል – ቢቢሲ በዘገባው።

የማይታመንና የማይመስል ቢሆንም  በዙሪያቸው ያሉት መንደሮች የጠገቡ ነዋሪዎችም፣ ኢህአዴግ እንዳደረገው ሊቀጡዋቸው ከመንደሯ ለመጡ ረሀብተኞች አናበላም፤ አናጠጣም ብለው አመጹ እንበል። እዚህ ላይ  የሰው የሕይወት ስርዓት ሳርና ቅጠል እየተመገበ መኖር እንደማያስችል መታወቅ ይኖርበታል። የቢቢሲ ጋዘጤኞች አየናቸው ያሉዋቸው ሰባት ልጆቻቸውን ሳርና አረም የሚመገቡ ሴት፣ ይህን ያደረጉት ኢህአዴግና የአጎራባች መንደር ነዋሪዎች አናበላም አናጠጣም ብለው ለረሀብ ባጋለጡዋቸው ጊዜ ሁሉ ነው? ወይንስ ቱሪስት መስለው መንደሯ የገቡት ጋዜጠኞች ባዩዋቸው አንድ አጋጣሚ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ረሀብ ባጠቃቸው ጊዜ ሁሉ ነው እንዳይባል፣ ሰው እንደ እንስሳ ሳርና ቅጠልን ተመግቦ ወደ ኃይልነት በመቀየር ህይወቱን ጠብቆ መኖር የሚያስችል የህይወት ስርዓት ስለሌለው ውሸት ይሆናል። ሁኔታው የተፈጠረው ጋዜጠኞቹ ባዩበት አጋጣሚ ብቻ ከሆነ ደግሞ፣ የዕርዳታ አሰጣጡን በተመለከተ ቀድሞ የተያዘ አቋምን ዕውነት ለማስመሰል ሆን ተብሎ የተሰራ “ድራማ” ወደመሆኑ ያዘነብላል።

ጋዜጠኞቹ በመንደርዋ ቆየንበት ባሉት ሁለት ሳምንታት፣ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን አይተናል በሚል ያቀረቡትም፣ እንደማስረጃ ሊቀርብ የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም 1700 ሰዎች በሚኖሩበት የገጠር መንደር በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሰዎች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት በተፈጥሮ ሞት ህይወታቸው ማለፉ ያለና የተለመደ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

የቢቢሲ ጋዜጠኞች እንደጋዜጠኛ የዘገቡትን ነገር አየን፣ ሰማን ብለው ከማሰራጨታው በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የክልልንና የፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ አነጋግረው ሃሳባቸውን ማካተት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ የጉዳዩን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሚዛናዊ ዘገባ የማቅረብ ሞያዊ ግዴታ ስላለባቸው፡፡ጋዜጠኞቹ ይህንን አለደረጉም፡፡ ይህ ብቻውን የዘገባውን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡

አንግዲህ አልአዛር ኬ አቧራ አስነሳ ያሉትና በአጠቃላይ ዕውነተኝነቱ እጅግ አጠራጣሪ የሆነ ወሬ፣ ወይም በእርሳቸውና በቢቢሲ አባባል “የምርመራ ዘገባ”፤መንግስት “መሰረተ ቢስ ነው” በማለቱም የተሰማቸወን ብስጭት ገልጸው፤«… እንዲህ ያለው የመንግስት ዕልህ ዋነኛ ምንጭ ለዘመናት ክፉኛ የተጠናወተው የአሞግሱኝና የግነን በሉኝ አባዜ ነው» ብለዋል፡፡ አልአዛር. ኬ ቅን አመለካከት ቢኖራቸው ኖሮ በቅድሚያ በዘገባው ትክክለኛነት ላይ ማተኮር ይገባቸው ነበር።

መንግስትን የአሞግሱኝና የግነን በሉኝ አባዜ የተጠናወተው ነው የሚለው ውንጀላቸውም ከተራ ዘለፋ ያልተለየ የግል ስሜታቸውን ብቻ የሚገልፅ ነው። ባለፉት አመታት እንዳስተዋልነው፣ በተለይ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ቢቢሲን የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሀን  እሰኪሰለች ድረስ መንግስትን ሲወቅሱና ሲኮንኑ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ሙገሳ የሚያገኘው እጅግ አልፎ አልፎ ነው። በመሆኑም ትችትና ውንጀላን እንጂ ሙገሳን ብዙም አልተለማመደውም፣ አልተጠናወተውምም። ውንጀላና ትችት ሲቀርብበት ሳይደናገጥ ስራውን የሚሰራው፣ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የሚያውክ ሲመስለውም በሰከነ አኳኋን በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ መስጠት ያስቻለውም ይሄው ነው።

እናም አልአዛር ኬ መንግሥትን መተቸት ወግ መስሏቸው፣ በጎ ቢሠራ እንኳ መሞገስ የሚገባው ስላልመሰላቸው ሐሣብን የመግለፅ ነፃነት ያስገኘላቸውን መብት ተጠቅመው በማንቋሸሽ የጥላቻ ስሜታቸውን ለመግለፅ ያደረጉት ነው፡፡ በጎ ጎኑም መነገር እንዳለበት ቢያስቡማ ኖሮ ቢቢሲ ዘገባውን ካቀረበ ከጥቂት ቀናት በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂላሪ ክሊንተን “እ.ኤ.አ በ 2002 እና በ2003 ከ 13 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ለረሃብ ተጋልጠው ነበር፡፡ አሁን ለምግብ እጥረት የተጋለጡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ 5 ሚሊዮን በታች ነው፡፡ ይህ የረሃብተኞች ቁጥር ትንሽ ነው ባይባልም፣ በአጭር ግዜ ውስጥ የታየው መሻሻል ግን አስደናቂ ነው፡፡”ሲሉ የተናገሩትንም በጽሁፋቸው ላይ በጠቀሱ ነበር፡፡ በዚሁ ሰሞን የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት/USAID/ ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጥረት እንጂ ረሃብ የለም፤በሚል መግለጫ ማውጣቱንም ልብ በሉ፡፡

አልአዛር ኬ ከአንድ ተኩል አስርተ አመት በፊት መንግሥት ዋነኛ ትኩረቴ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሦስቴ እንዲመገብ ማድረግ ነው በሚል የያዘውን ፖሊሲና የሐብታም አርሶ አደሮች መፈጠርንም ተችተውታል፡፡ “አርሶ አደሩን ባለብዙ ሚሊዮን ብር አድርጌያለሁ ስለዚህ አሙግሰኝ ለሚለው መንግሥት የቢቢሲው ዘገባ ቅስም የሚሰብርና ጉንጭ የሚያቀላ የሐፍረት ስሜት ቢፈጥር አይገርምም” በማለት፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖረች  አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ የዚህ ድህነት ዋና መገለጫ ደግሞ የግብርናን ያህል እድሜ ባስቆጠረ ኋላቀር የግብርና ቴክኖሎጂና የአመራረት ሥልት እራሱን እንኳን በወጉ መመገብ የማይችል /በቀን ሦስቴ መመገብ የማይችል/ አብዛኛውን የአገሪቷን ሕዝብ የሚሸፍነው የአርሶ አደሩ ኑሮ ነው፡፡ የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በዋናነት  ግብርናና ገጠር ላይ ያተኮረው እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአገሪቱን ሕዝብ የሚሸፍነው አርሶ አደር ራሱን በወጉ መመገብ እንዲችል፣ የአገሪቱን ድህነት ያህል ደካማ ቢሆንም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና በመሆኑ የግብርናን ምርታማነት በማሣደግ ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችም መፈጠርና ማደግ የሚያስችል የካፒታል ክምችት ለመፍጠር ነው፡፡ አልአዛር ኬ ይህ የመንግሥት ፖሊሲ ምንም ውጤት አላስገኘም ባይ ናቸው፡፡ የቢቢሲ ዘገባም ይህን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አማኝ አድርገው መንግሥትን   ያጋለጠ ነው ባይ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ገና ከድህነት ለመውጣት የምትፍጨረጨር አገር መሆኗ ግልፅ ነው፡፡ ለዘመናት ሥር የሰደደ ድህነት ከአንድ ተኩል አስርት ባልዘለሉ አመታት ብን ብሎ ይጠፋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ዋናው ነገር ባለፉ አንድ ተኩል አስርት አመታት  የነበረውንና አሁን ያለውን በማነፃፀር የተሻለ ነገር አለ ወይንስ የለም? የሚለውን ማጤን ነው፡፡ እዚህ ላይ መሻሻል መኖሩን ማንም አይክድም፤ ምናልባት ክርክር ሊነሣ የሚችለው ከዚህ በላይ መሆን ይችል ነበር ወይንስ አይችልም? የሚለው ነው፡፡ ይህ እራሱን የቻለ ሰፊ አጀንዳ ስለሆነ በዚህ ፅሁፍ ላይ አላነሣውም፡፡

በሚሊየን ብር የሚገመት ሃብት ያፈሩ  አርሶና አርብቶ አደሮች የመፈጠርም ጉዳይ በስሚ ሰሚ የምናውቀው ሣይሆን በተጨባጭ ያየነው ነው፡፡ ከምንም ተነስተው በመቶ ሺዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሐብት ያፈሩ በርካታ  አርሶና አርብቶ አደሮች ተፈጥረዋል፡፡ ቀድሞ በመኪና ተሳፍሮ መጓዝ ብርቅ ሲሆንባቸው የነበሩ አሁን የራሣቸው መኪና ለመግዛት የበቁ አርሶና አርብቶ አደሮች  ተፈጥረዋል፡፡ ድሮ በአህያ ከሚጫን ምርት በላይ የሌላቸው አሁን በጭነት መኪና ለገበያ የሚቀርብ ምርት ያፈሩ፣ የራሣቸው የጭነት መኪና ለመግዛት የበቁም አርሶና አርብቶ አደሮች መፈጠራቸውም እውነት ነው፡፡ እነዚህ አርሶና አርብቶ አደሮች ሞዴሎች በመሆናቸው ጠንክሮ ከተሰራ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስና ከዚህም የበለጠ ስኬት ማግኘት እንደሚቻል ለተቀረው ሰፊ አርሶና አርብቶ አደር መልእክት እያስተላለፉና ልምዳቸውን በስፋት እያካፈሉ ያሉ ናቸው፡፡ የመንግሥት ጥረትም ለስኬት የሚያበቁ በጎና አወንታዊ ተሞክሮዎች ይበልጥ እየሰፉ እንዲሄዱ የሚያግዙ ሁኔታዎችን በመፍጠር የአርሶና አርብቶ አደሩን ሕይዎት በመሰረታዊነት መለወጥና ተጠቃሚነቱን በሂደት/ደረጃ በደረጃ/ ማረጋገጥ ነው፡፡ ስትራቴጂውም ይህን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ መሠረተ ቢሱ የቢቢቢ ዘገባ ዓላማ ይህን ማደብዘዝ ነው፣ የአልአዛር ኬ ፅሁፍም አላማም ይህንኑ ማስተጋባት ነው ፡፡

የረሀብተኞች ቁጥር ላይ ስለላለውም አለመግባባት አንስተዋል፣ አልአዛር ኬ፡፡ የረሃብተኛው ቁጥሩ አሁን ከተገለፀው በላይ ነው የሚለው ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መወዛገቢያ ሆኗል ባይ ናቸው፡፡

እንግዲህ፣ ዘንድሮ በተከሰተው ድርቅ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ዜጐችን ቁጥር በተመለከተ፣ ከሌላው ጊዜ የሚለየው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም የኢትዮጵያ መንግሥትና ለጋሾች  ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ዜጐች /4.5 ሚሊዮን/ መሆናቸውን መግለፃቸው ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለምግብ እጥረት ተጋለጠ በሚል የገለፁት አሃዝ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ አሐዝ በግምት የተደረሰበት  ሣይሆን፣ ጥናት ተሠርቶ የተገኘ ነው፡፡ አልአዛር ኬ የሚነግሩን የረሐብተኛው ቁጥር ከዚህ በላይ ነው የሚለው መግለጫ ምንም አይነት ጥናት ባልሠሩ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተወራ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህመንግሥት የረብተኞቹን ቁጥር በይፋ አሣውቆ አርዳታ ጠይቋል፡፡ እርዳታ እስኪደርስ የምግብ እጥረቱ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ከመጠባበቂያ የህሕል ክምችት ምግብ እያከፋፈለ ይገኛል፡፡ ይህን ከቁብ ሣይፅፉ የረሀብተኛው ቁጥር ከዚህ በላይ ነው እያሉ የሚንጫጩት ተቃዋሚዎችና እንደ አልአዛር ኬ ያሉ አጋፋሪዎቻቸው ናቸው፡፡ አልአዛር ኬ የፅሁፋቸው ርዕስ ያደረጉትን ለቢቢሲ ቃላቸውን ከሰጡት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር የተፈጠረው አተካሮ “መልዕክቱን ትቶ መልዕክተኛውን” ማጥቃት ይመስላል በሚል ያቀረቡት ላይ አጭር አስተያየት ሠጥቼ ፅሁፌን ላጠቃልል፡፡

መንግሥት ለቢቢሲ ዘገባና የራሣቸውን አላማ ለማሣካት መሠረተ ቢስ ወሬ ላናፈሱ የተቃዋሚ መሪዎች ምላሽ የሰጠው፣ የወሬውን መልዕክተኞች ለማጥቃት ሣይሆን የመልዕክቱን አላማ መሠረተ ቢስነት ለማሣየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሥር የሰደደ ድህነት ለማስወገድ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ በአየር መዛባት ‐ በድርቅ ምክንያት ለረሀብ የተጋለጡ ዜጎች የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው፣ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ እናም ማንም ለራሱ ዓላማ ኢትዮጵያ ላይ በሟረተ ቁጥር፣ ሟርቱን አምናችሁ ሙሾ የምትወርዱ አስለቃሽ ጋዜጠኞችና ዓምደኞች ራሳችሁን ፈትሹ፤ከሁሉም በላይ ለሕሊናችሁ እደሩ፡፡