የጋዳፊና የእንግሊዝን ወዳጅነት መረጃዎች አመለከቱ

ፕሬዚዳንት ሞአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ለማስወገድ የተቃዋሚዎቹ ኃይሎች ሲንቀሳቀሱ፣ የእንግሊዝ መንግሥት ሥርዓቱን ለመቀየር በጋዳፊ ላይ የአየር ጥቃት ከማድረግ ጀምሮ የሊቢያ አምባሳደርን ከአገሯ በማባረር ድጋፏን ገልጻለች፡፡

ሆኖም አዲስ የወጣ መረጃ፣ እንግሊዝ የጋዳፊ ተቃዋሚዎችን ፀጥ በማሰኘት ከፍተኛ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ የእንግሊዝ የፀጥታ ኃይሎች የአሁኑ የተቃዋሚዎቹ መሪና የጋዳፊ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበረ ግለሰብን ዝም በማሰኘት ክንውን ውስጥ ዋነኛ ተዋናኞች መሆናቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡

እ.ኤ.አ. መስከረም 2 ቀን 2011 ይፋ የሆነው ሚስጥራዊ መረጃ እንዳመለከተው፣ የጋዳፊ ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆነው አብደል ሀኪም ቤልሀጂ እንዲያዝና ድብደባ እንዲፈጸምበት የእንግሊዝ የደህንነት ኃይሎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ በቀድሞ የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙላ ኩሳ ቢሮ የተገኘው መረጃ፣ የሊቢያ መንግሥት ከእንግሊዝ ኤምአይ 6 ባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጋልጧል፡፡ በአሁን ወቅት የጋዳፊ መንግሥት ለመገልበጥ ቀስቃሽ የሆነው የሊቢያውያን የሙስሊም ተዋጊዎች ቡድን መሪ ቤልሀጂን ለመያዝ የእንግሊዝ የፀጥታ ኃይሎች ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር፡፡