ብንኖርበት ምናለበት!

በኃይሉ ቁምላቸው

በወዳጅ ሶሻሊስት አገር ነፃ የትምህርት ዕድሉን አግኝቶ ቆይታውን በዚያው አደረገ፡፡ የእንስሳት ጤና ትምህርቱንም ተከታትሎ እንደጨረሰ ወደ አገር ቤት ተመለሰ፡፡ በደርግ ጊዜ ነው፡፡ የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ – ምናልባትም ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት፡፡ እናም ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አንደኛው ክፍለ አገር ተመድቦ በሙያው ማገልገልን ያዘ፡፡

በዚያ በተመደበበት ከተማ ኧረ አስደናቂ ታሪክም አለው፡፡ አህያን በቀዶ ሕክምና አዋልዷልም እየተባለ ስሙ በበጎ ይነሳል፡፡ ምን ያደርጋል./ መጨረሻው አላማረም፡፡ በሙያው ደስተኛ አልሆነም፡፡ እሱ እንደሚያስበው የእንስሳት ሐኪም መሆኑ ብቻውን በማኅበረሰቡ ዘንድ የተለዬ ክብርና እውቅና አያሰጥም በሚል አመለካከት ከህሊናው ጋር ዘወትር ይጋጫል፡፡

ይታያችሁ! በግሉ በፈጠረው የተሳሳተ ስሜት ከሙያው ጋር ጨርሶ ዝምድና የሌለውን የፊዚክስ መምህር ሆኖ ለመስራት እስከመጠየቅም ደርሷል፡፡

አሁን በአዲሱ ዓመት ይህንኑ የእንስሳት ጤና ሐኪም አይሆኑ ሆኖ እዚህ አዲስ አበባ ስታዲም ዙሪያ አገኘነው፡፡ ከሃያ ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡

ከእንስሳት ሐኪሙ ጋር ስለነበረን ቆይታ ለጊዜው እዚህ ላይ ገታ እንዳደርግ ውድ አንባቢዎቼ ፍቀዱልኝ፡፡ ወደ ኋላ ላይ መመለሴ አይቀርምና ስለ እሱ የማጫውታችሁ ይኖረኛል፡፡

የፅሁፌ መነሻ ወደሆነው ዋናው ጉዳይ እንሸጋገር፡፡ ይኸውም ቶርባ የተባሉ ፀሐፊ ከሣር ቤት መስከረም 7 ቀን 2004 ዓ.ም በዚሁ አዲስ ዘመን ጋዜጣ “ለዶክተር ጤና ይስጥልኝ” በሚል ርዕስ በፃፉት አስተያየት ላይ የበኩሌን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡

ቶርባ ጥሩ አድርገው ዶክተሩን ታዝበዋቸዋል፡፡ ጥሩ አድርገውም ገልፀዋቸዋል፡፡ ከተለመደው የጤና ይስጥልኝ ሠላምታ ባለፈ ለዶክተሩ ጤና ይሰጥልኝ ነው ያሉት ፀሐፊው?፡፡ እውነትም ጤና ለነሳው፣ ጤና ላጣውና ጤና ለራቀው ጤና መመኘታቸው ፀሐፊውን ያስመሰግናቸዋል፡፡

የፀሐፊው መነሻ ጭብጥ ዶክተር መረራ ጉዲና በቅርቡ በኢትዮጵያ ተመዘገበ የሚባለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ቤተ መንግሥት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በአገሪቱ የለም ብለው በጭፍን ሊሞግቱ ሲነሳሱ ሳይ በእርግጥ እኔም አፈርኩ፡፡

ስለ ሀቅ፤ ስለ እውነት ለመናገር ዶክተር ምነው ድፍረቱን አጡ፡፡ መቃወም ሲባል እኮ እውነታን ሸርሽሮ ማፈራረስ፣ ሀቅን መሠረተ ቢስ በሆነ የአሉባልታ ወሬ ማድበስበስና ማጥላላት አይደለም፡፡

በደምሳሳው ለመቃወም ሲባል ብቻ በጎ ሥራዎች ላይ ጥላሸት መቀባባት መልካምም አይደል፡፡ ሕዝብም ይታዘብዎታል “ዶክተር መረራን ምን ነካቸው” እያለ፡፡ ባልንጀራዎችዎም ቢሆኑ ቀና ሕሊና ካላቸውና ድፍረቱን ከገለፀላቸው አንድ ማለታቸው አይቀርም፡፡ አዬ የእኔ ነገር! ምን ነክቶኝ ነው አንድ አይደላችሁ? አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነውና ከነተረቱ፡፡

ዶክተር መረራ ልንገርዎና መሠረታዊ የሆነ ችግር አለብዎ፡፡ ከእኔ በላይ አዋቂ፣ የሁሉ ነገር ተንታኝ፣ ተመራማሪ፣ ሊቅ፣ ጠቢብ የለም በሚል የተኮላሸ መንፈስ ተሞልተው በእውር ድንብር ጉዙ አንዱን ሲያነሱ ሌላውን ሲጥሉ ነው እድሜዎን እየገፉ ያሉት – ከእኔ በላይ አዋቂ ላሳር በሚል ዓይነት ስሜት፡፡

የዚህች አገር አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መሪዎች የሚገርሙ ናቸው፡፡ በዚህች አገር ምን የማይታይና ምን የማይሰማ ነገር አለ፡፡

ዶክተር መረራ ስለ ኢኮኖሚ ሲወራ በዚህ መስክ ከእኔ በቀር ማን አለ ብለው ለመሞገት የሚዳዳዎት፣ ጭብጥ በሌለው መከራከሪያ መውተርተር፤ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በመወያያነት ሲነሳም በዘርፉ ተመራማሪ፣ ሊቁ እኔ ብቻ! ስለሆነም የተለየ አስተሳሰብ ያላችሁ ከፊት ለፊቴ ወግዱ ለማለት የሚቃጣዎት፤ ወታደራዊ ሙያን ስለሚጠይቅ ጉዳይ ሲወሳ ፈጥነው እንዲህ ነው ብለው ወታደራዊ ትንታኔ ለመስጠት የሚከጃጅልዎት፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በርዕሰ መወያያነት ሲመከርበትም ኧረ እንዴት ተሁኖ፣ እኔ እያለሁ ሌሎች አርፋችሁ ተቀመጡ ለማለት የሚሻዎት ዓይነት ሰው ነዎት፡፡

ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ራስን ከሌሎች አስበልጦና አግዝፎ ማየት፣ ራስን የሁሉ ነገር ብቸኛ አዋቂና ፈላስፋ አድርጎ ፈርጆ መኮፈስ የኋላ ኋላ የሚያመጣው ጣጣ ሌላ ነው፤ ማጣፊያው ያጥራልና፡፡ ትክክለኛ ሥፍራዎ ይኼ ነው ተብሎ ሲገለፅልዎ እውነታውን ላለመቀበል አሻፈረኝ ብለው ከራስዎ ጋር ተላትመው፣ ለራስዎ የተሳሳተ ትልቅ ግምት ሰጥተው ኋላ ላይ መበለሻሸት እንዳይመጣ፤ አይሆኑ ሆነው ክፉኛ ወድቀው  እንዳይሰባበሩ ሥጋቴ ነው፡፡ ሞት ካልቀረ አሟሟቴን አሳምረው አይደል ያሉት አበው፡፡

አሁን እየሆነ ያለው ግን ይኸው ነው፡፡ በተሳሳተ ግምት ላይ ተመስርቶ ራስን ዝቅ አድርጎ ማየት በአንድ በኩል አደጋ ነው፤ በአንፃሩ የሌለን ስብዕና ለራስ ሸልሞ መኮፈስም የኋላ ኋላ ውድቀቱ የከፋ ነው፡፡

ውድ አንባቢዎቼ! የእንስሳት ሐኪሙን የት አደረስከው? እንዳትሉኝ፡፡ በቃሌ መሠረት ጥቂት ላወጋችሁ ይኸው ቀጠልኩ፡፡ በእርግጥ ይኼ የእንስሳት ሐኪም ጨርሶ አልተበለሻሸም፡፡ ትንሽ ነካ የሚያደርገው በአራዶቹ ቋንቋ “ፉዞ – ቀዌ” የሚሉት ዓይነት ሆኗል፡፡

አለባበሱ የጤና አይደለም፡፡ በጥቁሩ ሙሉ የሱፍ ልብስ ላይ ነጠላ ጫማ (በረባሶ) ተጫምቶበታል፡፡ ይህ መጀመሪያ ተመድቦ ይሰራበት በነበረው አካባቢ የተለመደ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡  ነጠላ ጫማው ከሙሉ ልብስ ጋር መደረጉ ግን እዚህ በመዲናዋ የሰው ዓይን ውስጥ መግባቱ ግድ ይላል – ሙሉ ልብስ በበረባሶ ነጠላ ጫማ፡፡

ከዓይኑ ላይ ጣል ያደረው ነጭ መነፅር መስተዋቱ አንድ ዓይና ነው፡፡ ክብ ኮፍያ ከአናቱ ደፍቷል፡፡ በጣም ጠንቃቃ ነው፡፡ ሰዎች ስለ እኔ ምን ያወራሉ፣ ምን ይላሉ የሚለው የድሮ አመሉ ዛሬም ተከትሎት አለቀቀውም፡፡

ቆብ መድፋቱ ወደ ኋላ የሸሸው ፀጉሩ የእድሜውን መግፋት እንዳያሳብቅበት መከለያ መሆኑ ነው – ከሽምግልና ለመሸሽ፡፡ የአንድ ዓይና መነፅሩ ትርጓሜ ወይም የአገልግሎት ጠቀሜታው ግን አሁንም ድረስ አልገባኝም፡፡

በስታዲየም ዙሪያ ካለች በዚያች ትንሽዬ የመጠጥ ግሮሰሪ ውስጥ ከእንስሳት ሐኪሙ ጋር ዓይን ለዓይን ተፋጠጥን፡፡ ሁላችንንም በየተራ መላልሶ አተኩሮ አየን፡፡ እንተዋወቃለን – እዚያው ክፍለ አገር፡፡

የጠረጴዛውን ዙሪያ ከበን የተቀመጥነውን ስማችንን ከእነ ሙያችን ጭምር እያጣቀሰ አንድ…በአንድ ዘርዝሮ ነገረን – አልተሳሳተም፡፡ እኛም ቢሆን አላጣነውም፡፡ እንዲቀመጥ ጋብዝነው ጠረጴዛውን ተጋራን፡፡ ተናጋሪው እሱ ብቻ ቢሆንም ጨዋታው ደርቷል፡፡ ስለሞቱትና በሕይወት ስላሉት የቀድሞው የጋራ ባልንጀሮቻችን እየተነተነ አረዳን፣  ተረከልንም፡፡

አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ጠየቅነው፡፡ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፋርማኪዮሎጂ መምህር ሆኖ እየሰራ እንዳለም ገለፀልን፡፡ መልስ ሳንሰጥ እርስ በእርስ ተያየን – ተግባባንም፡፡

ወደ መለያያችን አካባቢ ካዛንቺስ ለሚሄድበት የትራንስፖርት ሦስት ብር ስጡኝ ጥያቄ አቀረበ – በዩኒቨርሲቲ የፋርማኪዮሎጂ መምህሩ፡፡ እኛም አላቅማማንም ከጠየቀው በላይ ትንሽ ገፋ አድርገን “ጀባ” አልነው፡፡ ተለያየን፡፡

እሱ ከእኛ ቢለይም ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ግን ቀጥሏል፡፡ ያኔ ክፍለ አገር እያለን በራሱ የተሳሳተ አስተሳሰብ የፈጠረው የበታችነት ስሜት ጤናው ተናግቶም ዛሬም አብሮት እንዳለ ነው – የትናንቱ የእንስሳት ሐኪም የዛሬው የምናብ ዓለሙ የ”ፋርማኪዮሎጂ” መምህሩ፡፡

ገና ከመነሻው የእንስሳት ጤና ሐኪሙ በውስጡ የፈጠረው የበታችነት ስሜት ደቋቁሶት ኖሮ ይኼም ሁኔታ አድጎ ዛሬ ላለበት የጤና ቀውስ ዳርጎታል፡፡ ሰውዬውን በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ላይ ሆኖ ስናገኘው በእርግጥም ከልባችን አዘንለት፡፡

ነገርን ነገር አይደል የሚያነሳው፡፡ ያኔ ክፍለ አገር ሳለን የእንስሳት ሐኪሙ በከተማዋ ጤና ጣቢያ ውስጥ ይሰራ ከነበር አንድ ሐኪም ጋር ምሣ ይጋበዛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ

የሆቴሉ አስተዳዳሪ ስለባለቤቱ ወቅታዊ የጤና ችግር ለማስረዳት ወደ ሐኪሙ ዘንድ ተጠግቶ ያወያያል፡፡

ይኼኔ የእንስሳት ሐኪሙ ተጠያቂው የህክምና ባለሙያ አስተያየት ከመስጠቱ በፊት በፍጥነት ተሽቀዳድሞ መላሽ እሱው ራሱ ሆኖ ተገኘ፡፡ ቀጠለም፤ “አየህ የባለቤትህ የጤና ችግር እንዲህ…እንዲህ ነው” እያለ ካለ ሙያው ገብቶ መዘባረቁን ያስተዋለው የሆቴሉ ባለቤት “ተመልከቱ አይገርምም! ሰው ሐኪም እያለ ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ ለመስጠት የሚሽቀዳደመው የእንስሳት ሐኪሙ ሲሆን ምን ይባላል?” ሲል በአግራሞት ይጠይቃል፡፡

በሆቴሉ ውስጥ ይመገቡ የነበሩ ሌሎች ደንበኞች የሆቴል ቤቱን ባለቤት ንግግር በሳቅ አጀቡት፡፡ የእንስሳት ሐኪሙም ተቆጥቶ ምግቡን አቋርጦ ተሳድቦ ይወጣል፡፡ ድሮውንም የእንስሳት ሐኪሙ ያልሆነውን ሆኖ መገኘት ፍላጎቱ ነበርና በዚህም ብስጭትጭት አለ፡፡      

አንድን ሙያ ከሌላው ጋር እያወዳደረ፣ በምናቡ ደረጃ እያወጣ፣ ይኼ ታናሽ  ያኛው ታላቅ እያለ እየመዘነ በሐሳቡ ሲያውጠነጥን ይውላል – መኝታም ላይ ሆኖ ያብሰለስላል፣ እያብላላም ያድራል፡፡

በራስ ሙያና እውቀት ደስታንና እርካታን ማጣት፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታ የእንስሳት ሐኪም ሆኖ ሳለ በዚህ ሙያው ሳይረካ ቀርቶ የለም እኔ የሰውም ሐኪም፤ አልፎ ተርፎም የሌሎች በርካታ ሙያዎች ሁሉ ባለቤትና ሊቅ ነኝ፤ ተሳስታችኋል ብሎ ራሱን አሳምኖ መደምደም፤ በሌላ ጊዜ በዚህም ሳይረካ ቀርቶ ኧረ እንዴት…እንዴት እኔኮ የፊዚክስ ሙያ አዋቂ በመሆኔ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነትና በተመራማሪነት ነው ማገልገል ያለብኝ ብሎ መወሰን፡፡

በሌላ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ሁሉ ይንቁኛል፤ የውስጥ ባዶነቴንና ግብዝነቴን እያጣቀሱ ያፌዙብኛል እያለ መብከንከን፣ ሰዎች ስለ እኔ ያወራሉ፣ ስህተቶቼን እየለቀሙና እየነቀሱ ይተቹኛል፤ ይተርቡኛል፤ ያሽሟጥጡኛል፤ እያለ ማረርና መክሰል፣ ሰዎች ሁሉ ይከታተሉኛልም ብሎ መጨናነቅ፡፡

ለራስ የተሳሳተና ከሚገባው በታች አነስተኛ ግምት ሰጥቶ አዕምሮን ማናወጥ፤ መጨረሻው ጨርቅን ጥሎ እርቃን መውጣት፤ ውሎ ሲያድርም በየጎዳናውና በየአደባባዩ ሰሚ አገኙም አጡ በባዶው መለፍለፍ፤ ለራስ ብቻ እየተናገሩና ራስን እያዳመጡ አርፍደው ውለው፤ ማምሸትና ማንጋት እለታዊ ትዕይንት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ያልሆኑትን ሆኖ መታየት፤ ከራስ ጋር መጣላት፣ ራስን ሆኖ ያለመገኘት ክፉ ደዌ፡፡

የእንስሳት ሐኪም ሆነው ሳለ እኔ በፋርማኪዮሎጂ ፒ.ኤች.ዲ አለኝ፣ የፊዚክስ አዋቂ ነኝ፣ የሰው የሕክምና ባለሙያ ነኝ … ብሎ መሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር መላተም፡፡

በሰዎች ዘንድ ያልሆነውን ሆኖ ለመቅረብ፣ መስሎ ለመታየት የሚያደርገው መውተርተር በአንድ ጎኑ በሌላው ጎኑ ደግሞ ከእውነተኛ ውስጣዊ ማንነቱ ጋር በተፈጠረ ግጭት ራስን ለሥቃይ መዳረግ፡፡ በምናቡ የፈጠረው ትልቅ የመሆን ፍላጎት ከትክክለኛ ማንነቱ ጋር ሲጣረስ ያሳደረበት የበታችነት ስሜት ይኼኛው ለራስ ዝቅ ያለ ግምት ሰጥቶ በሚፈጠር ቀውስ መጨረሻው አላምር ያለ ወገኔ ነው፡፡

የተከበራችሁ አንባቢዎቼ! ወደ ዶክተር መረራ ልመልሳችሁ፡፡ መቼም ምኞትና ሕልም ማን ከልካይ አለው አይደል የሚባለው፡፡ ዶክተር መረራ ሁሉን ለመሆን ቢመኙ ጥፋቱ ከምን ላይ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡ ልዩነቴ ሁሉን አዋቂ እኔ ነኝ ብለው በባዶ መኮፈሳቸው ነው ጥፋቱ፡፡

ይህ ጉዳይ ዋጋ የሌለው፣ እዚህ ግባ የማይባል፣ ቦታ የማይሰጠው፣ የማይረባ፣ በጣሙን ርካሽ፣ ተራ የአዕምሮ የምኞት ዝግጅትና ቧልት ተደርጎ ባይቆጠር መልካም ነው – ይኼ የሥነ ከዋክብት የትንበያ ዓምድ ዓይነት ጨዋታ አይደለምና፡፡

ዶክተር መረራ መጨበጫና መቋጠሪያ ከሌለው የሀሳብ ፈረስ ኮርቻ ላይ ወርደው ከመሬት ሲያርፉ ከትክክለኛው ቦታ ይረግጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህም የእኔ ብቻ ምኞት ሆኖ እንዳይቀር እፈራለሁ፡፡

ራሳቸው በፈጠሩት የሀሳብ ማዕበል ሰምጠው እየዳከሩ፣ ጨርሶውኑ ሊደረስበት ከማይቻለው ከወዲያኛው የሀሳብ ዓለም ውስጥ ተደብቀው ሊኖሩ ሲጥሩ ይስተዋላሉ – የ”ሐሳብ እሹሩሩ” ዜማን እየኮመኮሙ፡፡

በማይጨበጡና በማይዳሰሱ ምኞቶችና ስሜቶች ተሞልተው በፈጠሩት የብዥታ የሃሳብ ባህር ላይ ሲንሳፈፉ፣ ከገቡበት የቅዥት ዓለም ሊወጡ ሲንደፋደፉ፣ ላለመስመጥ ሲዋኙ፣ ሲዳክሩ፣ መከራቸውን ሲያዩ አዘንኩላቸው – ዶክተሩን፡፡

የእንስሳት ሐኪሙ ወዳጄ ራሱን አሳንሶ፣ ደካማና የማይረባ እንደሆነ አድርጎ  ይቆጥራል፡፡ እንደ እኔ…እንደ እኔ ከዚህ ዓይነቱ ባዶ ሐሳብና ፍላጎት ተላቅቆ፣

ትክክለኛውን ማንነቱን ፈልጎ አግኝቶ፣ ወደ እሱነቱ ተመልሶ በሙያው በተገቢው  ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሪቱን መጥቀም ቢችል እንዴት ደስተኞች በሆን፡፡ ሰውዬው ከህሊናው ታርቆ ቢሆን ኖሮ በእርግጥም በሙያው አንቱ የተሰኘ ሥራ ሊከውን ይችል እንደነበረ እኛ እማኞች ነን፡፡

ዶክተር መረራ እርስዎ በፊናዎ ዓለምን በቁጥጥርዎ ሥር አውለው የግል ሀብትዎ ማድረግን ይቋምጡ ይሆናል፡፡ ሆኖም የሚመኙት የሕይወት አውድና የተጨባጩ ዓለም ነባራዊ እውነታ ለየቅል ሆኖ ሲቸገሩ ታዝቤዎታለሁ፡፡

ራስዎን በጠለቀ ሁኔታ ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለመገንዘብ ቢጥሩ እንዴት ሸጋ በሆነ፡፡ ምኞትዎ እንደ ጤዛ በኖ የውኃ ሽታ ሆኖ ከመቅረቱ በፊት ከገቡበት የቅዥት ዓለም ቢወጡ ምንኛ ተጠቃሚ ባደረገዎ፡፡

በአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አልተመዘገበም፤ ዕድገቱ ያለው በቤተ መንግሥት ውስጥ ብለው ሊሳለቁ ሞከሩ – ፊትዎን በጨው ታጥበው፡፡ በሁሉም ዘርፎች አገሪቱ ወደ ዕድገት ጎዳና ለመሸጋገር የምታደርጋቸውን ጥረቶችም ሊያጣጥሉ ሞከሩ፡፡

ስለ እውነታዎች ለመመስከር አንደበትዎ ተሸብቧል፡፡ በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ ስላሉት መልካም ጅማሮዎች ቃል ላይተነፍሱ ከሸሪኮችዎ ጋር ተማምላችኋል፡፡ ፖለቲከኛ መሆንና አሊያም ፖለቲከኛ ሆኖ ለመታወቅ በቆሎ አዘርተናችሁ የስንዴ ምርት እናሳፍሳችኋለን ማለት እኮ አያስፈልግም፡፡ በቆሎ በቆሎ፣ ስንዴም ስንዴ ነውና፡፡

መላ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ጋር ሊፋቱ ደፋ ቀና እያሉ ባለበት በዚህ ወቅት ጥረቱን ልታደበዝዙ፣ ጉዞውን ልታዘናጉት ትቋምጣላችሁ፡፡ ሊጎመዝዛችሁ፣ ሊቆመጥጣችሁ ይችል እንደሆን እንጂ እውነታውን የግድ ቢመራችሁም ትጎነጯታላችሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ብሩህ ተስፋን ሰንቋል፤ በዕድገት መሰላል ላይ መወጣጣትን ተያይዞታል፤ በመልካምና በጎ ራዕዮች ላይ ተስፋውን ጥሏል፡፡ ሠላሙን አስጠብቆ፣ የተጀመሩት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች እንዳይቀለበሱ ዘብ ሆኖ ሊቆም ቃል ኪዳኑን አድሷል፡፡

መልካም ሂደቶች ጎልብተው ውጤታቸውን በዘላቂነት ሊያጣጥም፤ በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ ያሉት ልማታዊ ተግባራት አዝጋሚ እንዳይሆኑ በፍጹም መነሳሳት ግባቸውን ሊያፋጥን፣ ቅድሚያ የባለቤትነት ድርሻውን ወስዶ ቀጥተኛ ተሳታፊነቱን ሊያረጋግጥ ከመንግሥት ጎን ተሰልፏል፡፡

ለልማትና ብልፅግና የተነሳሱ እጆችን የኋሊት ልትጠፍሩ አትቻኮሉ፤ በዕድገት ጎዳና ላይ ሊረማመዱ በተሰነዳዱ እግሮች ላይ ደንቃራ ለመሆን አትቋምጡ፤ በክፋትና በምቀኝነት መንፈስ ተሞልታችሁ ወደ ኋላ ልትጎትቱት አትጣጣሩ፡፡

ደጋግመን እንነግራችኋለን፣ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እንጮኃለን፣ አዎን አሁንም እናስጋባለን፣ ከጉዟችን ልታደናቅፉን አትሞክሩ አይቻላችሁም ብለን እንነግራችኋለን፣ ደግመን…ደጋግመን እናረዳችኋለን፡፡

መጪው የተሻለ ሕይወት እንደሚሆን ተስፋ ሰንቀናል፡፡ እናም ብትተውን፣ ብንኖርበት ምናለበት፣ የኋሊት ልትጎትቱን አንፈቅድላችሁም፤ አይቻላችሁምና! እናስ ብትተውን ምናለበት? ፀሐፊ ቶርባ ጤና ለራቃችሁ፣ ጤና ለነሳችሁ፣ ጤና ላጣችሁ ጤና እንዲሰጣችሁ ተመኝተዋል፡፡ እኔም እጋራለሁ ጤናውን ይስጣችሁ! – ሠላም፡፡