ዛሬም ነገም ምንጊዜም ክብር ለባንዲራው!

ዮናስ

ሁሉም የዓለም ሃገራት መለያቸው ነው፡፡ቅርፅ እና ቀለማቱም የየራሳቸው ትርጓሜ አላቸው፡፡ ከጅማሬው አንስቶ መሠረቱ መለያ ሆኖ ክብሩ ለዘመናት የኖረ ጥንታዊ የታሪክ ሚስጥር ይዞ በሰዎች ዘንድ ልዮ ስሜትን ሲፈጥር የኖረ አንዳች መግነጢሳዊ ሃይል ያለው እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ለህዝቦች ሃገራዊ ስሜት ማነቃቂያ ለብሄር ብሄረሰቦች ማድመቂያ የእርስ በርስ የመንፈስ ተወሃዶ ቁልፍ ፤ተከብሮ ክብርን የሚያጎናፅፍ ከምሰሶ ከቆመው ዘንግ አናት ላይ ተሰቅሎ የሚውለበለብ ሳቢና ውብ ባንዲራ ሰንደቅ አላማ፡፡

የሰንድቃላማ ቀን በሃገራችን ለአራተኛ ጊዜ«ሰንደቅ ዓላማችንና የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ኩራታችን ናቸው»በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡በዓሉን በድምቀት ከማክበር ባሻገር ለባንዲራው ክብር፣ለታሪካዊ መዘክር፣ለሚኖረው ሃገራዊ ፋይዳና እና ለሚያመጣው የብሄራዊ ተግባቦትና ፍቅር ስርፀት ልብ ብሎ ላተኮረበት ልዩ ስሜትን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ወኔን ያስታጥቃል ፣ታታሪነትንና የአልበገር ባይ ስሜትን ያጎናፅፋል፡፡ ከምንም በላይ ለባንዲራው ክብር ሲባል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ተከፍሎ ስንመለከት ምንኛ ውስጣዊ ስሜትን ኮርኩሮ ለተግባር እንደሚያነሳሳ ሊካድ የማይቻለው የባንዲራው ፍቅር ሃቅ ነው፡፡

ሃገራችን ከጀግንነቷ ጀርባ ባንዲራዋ አርማዋ ሆኗል ፡፡ ጀግኖች አትሌቶቻችን ለአሸናፊነት ሲበቁ ቀዳሚ ተግባራቸው የሃገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ባይናቸው እያማተሩ መፈለግ ነው፡፡ ካገኙትም በኃላ ባንዲራንውን በኩራትና በጥልቅ ስሜትና ፍቅር ተከናንበው ስቴዲዮሙን እየዞሩ ባንዲራውን እያውለበለቡ በመሮጥ ለሚመለከታቸው የዓለም ህዝብ ማሳየት ነው ፡፡ ይሄ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ ዛሬ ላይ ወደ ባህል  ወይም ልማድነት ተሸጋግሯል ፡፡ ሚስጥሩም የሃገር ክብርን ፈላጊነት፣የሃገር ፍቅርን ግለት ፣የማንነትን ተግባር አስመስክሮ ለማሳወቅ የሚደርግ ክዋኔ ነው፡፡

ስመጥር ጀግኖች አትሌቶቻችን ድል አድርገው የሃገራቸውን ባንዲራ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በሃገራቸን ብሄራዊ መዝሙር ታጅቦ ወደ መስቀያው አናት ሲያሻቅብ ሲመለከቱ የደስታ ሳግ ተናንቋቸው የእንባ ዘለላቸውን ከጉንጫቸው የሚያፈሱ ስፖርተኞችን መመልከት ብቻ የባንዲራን ስሜት ኮርኳሪነትና ኃያልነት መመስከር ያስችለናል፡፡

እያንዳንዳችን ያለንን የባንዲራ ፍቅር የሃገራዊ ስሜታችንን የመኖር ሚስጥር በምን ሀኔታ ስንሆንና በሁነቶችም ባንዲራችንን በምናስተውልበት ወቅት የሚኖረንን የስሜት መለዋወጥ አስተውልን ይሆን? እስቲ በሰከነ ሁናቴ እራሳችንን እንመልከት ባንዲራ ለኛ ምንድን ነው? የባንዲራንና የሃገር ፍቅር ቁርኝትን የምንገልጽበት በምን ዕሳቤ ይሆን? ለባንዲራው የምንሰጠው ክብር እስከምን ድረስ ነው? እራሳችንን በእነዚህና በመሰል ጥያቄዎች እየገመገምን የታዘብኩትን ከባንዲራ ጋር የተያያዙ ስርዓቶችን መጠቆም ወደደኩ ፡፡

ድሮ ድሮ ልጆች ሆነን በተለይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳለን ጠዋት በሰልፍ ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙራችንን እየዘመርን የባንዲራውን አወጣጥ ስርዓት እንፈፅማለን ፡፡ መዝሙሩ እየተዘመረ ባንዲራው እየተሰቀለ ማንም ሰው መንቀሳቀስ አይችልም ፡፡ ባንዲራውን የመስቀልና የዝማሬው ስርዓቱ ከተከናወነ በኃላ ነው በአከባቢው ያለው ሰው ወደተለመደው ህይወት መስተጋብሩ መንቀሳቀስ የሚጀምረው፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ጮክ ብለን ብሄራዊ ዝማሬያችንን ማዜም ትልቅ ክብር አድርገን ነው የምንቆጥረው ፡፡ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኃላም የሰንድቃላማ የማውረድ ስነስርዓት ይከናወናል፡፡ ያኔም ልክ እንደጠዋቱ ፊሽካ ተነፍቶ ባንዲራው ሲወርድ ማንም ሰው ከእንቅስቃሴው ይታቀባል፡፡ ለአፍታ ያክልም በዝምታ ድባብ አከባቢው ይዋጣል፡፡ ከዚያም ባንዲራው ወርዶ ካስተጣጠፉ ጀምሮ የሚቀመጥበት ስፍራ ምቹነት ልብ ብሎ ላስተዋለው ምን ያክል ከበሬታ እንደተጎናፀፈ ያሳየናል፡፡ ዛሬስ?

ባንዲራ ከሃገርና ሕዝቦች መለያነቱ ጎን ለጎንም ለአገር ሉአላዊነትና ክብር ብለው ለተሰው ሰማእታት አባቶቻችንና ቅድመአያቶቻችን በመታሰቢያነት ቀንና ማታ እነሱን ለመዘከርና ለማክበር የባንዲራ ስነስርዓት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ግና ዛሬ ላይ ሆነን በተለይ በወጣቱ ዘንድ የባንዲራውን ፅንሰ ሃስብ እና ስርዓተ ክዋኔውን በውል ያለመረዳት ችግር ከየት መጣ? ስንቶቻችን ነን አባቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው ላቆዩልን የሃገራችን ባንዲራ ተገቢውን ክብር የምንሰጥ? የሃገራችንን ብሄራዊ መዝሙር ጠንቅቀን መዘመር የምንችለውስ ምን ያህሎች እንሆናለን?  በመንግሥታዊ ተቋማትና ቢሮዎች የጠዋትና የማታ የባንዲራ አወጣጥና አወራረድ ስርዓት እንዴት እየተካሄደ ነው? የሚለውም ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የተሰቀለው ባንዲራ በፀሃይና በቁር አርጅቶና ነትቦ እንዲያም ሲል ተቀዶ ልናይ እንችላለን ፡፡ እያንዳንዳችን ከባንዲራው በስተጀርባ ያሉትን ሚስጢራት አውቀን ለትውልድ የማስተላለፉ ባህላችን ምን ድረስ ነው? ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡

እውን ልጆቻችን ስለባንዲራ ትርጉም ቢጠይቁን መልሶቻችን ምን ይሆን? ስንቶቻችን አፍታተንና አብራርተን የተሟላ መልስ እንሰጣለን ? እራሳችንን እንፈትሽ!

እኔ በበኩሌ አባቴ የባንዲራን ፍቅር ያገር መውድድ ስሜትን ይበልጡን እንዲያድርብኝ ገና በለጋ እድሜዬ ነበር የሚተርክልኝ፤ እናም ባንዲራ በጣም እንደሚከበር ስለገባኝ ማንም እንኳን ለቤቱ መጋረጃና የጠረጴዛ ልብስ ሊያደርገው ቀርቶ በእጁ እንኳን የሚነካው የተመረጠ ሰው ይመስለኝ ነበር፡፡ ይሄ የጨቅላ አይምሮዬ ያመነጨው ሃሳብ ምናልባት በየመንገዱ አልፎ አልፎ አንዳንድ ችግረኞች ምፅዋት እንዲሰጣቸው ከሚማፀኑባቸውና ከሚጠሯቸው የታቦት፤ የሰማዕታት እና የአማልዕክት ስሞች ተርታ “አረ ባባንዲራው” የሚል የመለመኛ ቃል ማዳመጤም ለሰንደቃላማ ያለኝን ክብር ካሳዱጉት ሁኔታዎች መካከል የራሱ ድርሻ አለው፡፡ አንዳንደ ጊዜ ደግሞ ዝም ብዪ ሳስበው ባንዲራ መከበሪያ ነው እንጂ መለመኛ መሆን አለበትን በሚል ጥያቄ አምሮዬን ፋታ አሳጣዋለሁ፡፡

ያም ሆነ ይህ በኔ ዘንድ ለባንዲራ ያለኝ ፍቅር አባቴ በጥልቀት ስላስረዳኝ ክብሩን የመጠበቅና የማክበር ሃላፊነቴን እንድወጣ አስችሎኛል ማለት ነው፡፡ ግና እድሜዬ ለአቅመ አዳም ሲንደረደር የባንዲራው ክብር እሳቤዬ እንደበፊቱ ቀጥሏል ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር ይከብደኛል፡፡ ለዚህ አንዱ መንስኤ የሚመስለኝ  የትምህርት ቤቶች ቸልተኛ መሆን ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ሳለሁ ልክ እንደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቴ በጠዋት ሰልፍ ላይ “ከንዳ፣አውርድ፣አሳርፍ ፣ተጠንቀቅ የአትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ለመዘመር 1, 2, 3” የሚል ትዕዛዝ ስጠብቅ ለካንስ ይሄ ልምድ አንዳንዶች ዘንድ ያዝ ለቀቅ አለያም በብዙዎች ዘንድ ጭርሱኑ ቀርቷል ፡፡ ሥነ-ስርዓቱ በዘልማድ እንደዋዛ ተትቷል፡፡ የተጠነቀቀውም ያልተጠነቀቀውም፣የከነዳወም ያልከነዳውም፣ቢፈልገው ተቃቅፎ ቢፈልገው የግል ወሬውን እየኮመኮመ ከቴፑ ድምፅ ማጉያ የተለቀቀውን ብሄራዊ መዝሙራችን ተጠናቆ ባንዲራው ከተሰቀለ በኃላ ወደ የክፍላችን መግባት የዘወትር ተግባራችን ሆነ፡፡ ልማድም ሆኖ ቀጠልንበት፡፡ የብሄራዊ መዝሙራችን ስንኝ እንደ መዝሙረ ዳዊት ሳነበንበው የነበርኩ ይባስ ብሎ መዝሙሩ ሊጠፋኝ ሲዳዳኝ ስመለከት ራሴን ወቀስኩት፡፡ ግን  ለምን የሚለው ጥያቄዪ ለአመታት ዘለቀ ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥያቄዪ ተገቢውን መልስ እያገኘ የልጅነት የባንዲራ ፍቅሬን ተመልሶ ዛሬ ላይ ላገኘው ችያለሁ፡፡

ለዚህም መንግስት በየዓመቱ የባንዲራ ቀን እንዲከበር መደረጉ ለኔ ትልቅ ግምት የመሰጠው ነው እላለሁ፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ሁኔታ የአገራዊ ስሜቴን እንደገና ቀስቅሶታል፡፡ የባንዲራን ፍቅርና ክብር ይበልጥ እንድረዳው የሚያደርግ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡

በተለይም መንግስት ባንዲራ የሃገርና የሕዝብ ክቡር አንዱ ክቡር መገለጫና መለያ ስለመሆኑ ለማሳወቅ የደነገገው ህግ ተፈፃሚ መሆኑ ይበልጡን ሕዝቡ ስለባንዲራዉ ምንነት ለማወቅና በተለምዶ አለያም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የባንዲራን ክብር ከሚጻረር ተግባር እንዲቆጠብ የሚያግዝ ሁነኛ መፍተሄ ነው፡፡ ባንዲራችን የማንነት መገለጫችን፣የሃገር ኩራትና ሞገሳችን ፣የህልውናችንና የክብራችን ከሁሉም በላይ የሉአላዊነታችን መገለጫ አንደመሆኑ ልዩ ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአብሮነታችንና የአንድነታችን ተምሳሌት፤ የብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ እሴቶቻችን እና የማንነት መገለጫችንና አርማችን መሆኑን አውቀን በሃገራችን  ለአራተኛ ጊዜ የሚከበረውን የባንዲራ ቀንን በተለዬ ድምቀት ልናከብረው ልናወድሰው የሚገባ ሆኖ፤ በዚህም ስለክብሩ ብለው የተሰው ሰማዕታትን  የምንዘክርበትና ክብር የምንሰጥበት ዕለት ሊሆን ይገባል፡፡
የዘንድሮውን የሰንደቅ አላማ ቀን ስናከብርም ሃገራችን የተያያዘችውን የልማት ውጥን ለማሳካትና ፈጥነን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ እያደረግነው ያለውን ጥረት አጠናክረን የመቀጠል ቃል ኪዳናችንን በድጋሚ የምናድስበት እለት ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይም የአምስቱን ዓመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከዚህም ጋር  የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን በማድረግ በላያችን ላይ ተንሰራፍቶ የቆየውን አሳፋሪ የድህነት ሸማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አውልቀን ለመጣል ደግመን ደጋግመን ቃል የምንገባበትና በሁሉም ዘርፍ  በቁርጠኝነትና በአንድነት መንፈስ ለሥራ የምንንቀሳቀስበት ጊዜ እንደሆነ የምናበስርበት አጋጣሚ ነው፡፡