ከንቱ ህልም

አባት ባዬ

“ኩኩሉ! አለ ዶሮ ፣ ምን ይሰማ ይሆን ጆሮ፣ ዘንድሮ፡፡“ አለች አቀንቃኟ፡፡ አሁን …አሁን ምን የማይሰማ ነገር አለ ብላችሁ ነው፡፡ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አይደለም ነገሩ፡፡ የምን ጉድ ሊነገረን ነው ብላችሁ ብዙ ነገር ታስቡ ይሆናል፡፡ እናንተ ዘንድ ምንም ጉድ የለ፡፡ ጉዱስ እዚያው ከጉዶቹ ዘንድ ነው ያለው ፡፡

አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ሲተካ ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ጓደኛ ሁሉም ከየብጤው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ይለዋወጣል፡፡ አንደኛው ለሌላኛው መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡ ያደለው እንዲህ ነው፡፡ ያላደለውስ እንዳትሉኝ፡፡

በአዲሱ ዘመን መባቻ ላይ ሆነን ሀገራችንን ይባርክልን፣ ከክፉ ይጠብቀን፣ የሰላም፣ የደስታ፣ የመተሳሰብ፣ የፍቅር ዘመን ይሁንልን፡፡ አሜን! የማይልና የማይባባል የለም፡፡ ሁሉም በየፊናው መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ ይኼ እንግዲህ ላደለው ነው፡፡

እኔን የገረመኝ የነዚያ የጉዶቹ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸው አሁንም ያው የእሪያ እጥበት (እሪያ ማለት ቢያጥቡት፣ ቢንከባከቡት መልሶ እዚያው ከቆሻሻ ቦታ የማይጠፋ አውሬ ማለት ነው) መሆኑ ቢያስደንቀኝ ሳልወድ በግድ ብዕሬን አነሳሁ ፡፡

በዚያን ሰሞን የመድረክ አመራሮችና ደጋፊዎች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ መግለጫ ይሰጣሉ ሲባል ስሰማ ‘’እሰየው ዘንድሮ ልብ ሳይገዙ አልቀረም፣ ከመንግስት ምህረትን፣ ከህዝብ ይቅር ባይነትን ለምነው ከወገናቸው በይበልጥም በቅድሚያ ከራሳቸው ህሊና ሊታረቁሳይሆን አይቀርም’’ ብዬ ገምቼ ነበር፡፡

ይህ ብቻም አይደለም “በመንግስት የተነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ከዚህም ጋር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብስራት አስደስቷቸው ይቅር ለሀገሬ ማለት ፈልገው ይሆናል’’ ስልም አሰብኩ፡፡ ምናልባትም ደግሞ ያ ያሳለፉት ዘመን ቢጤዎቻቸው ላይ ላዩን ሲያዩአቸው ርግብ ውስጣቸው ግን እባብ ሆነው የከረሙበት፣ በደጋፊዎቻቸው ፊት ጻድቅ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ደግሞ ኃጥዕ ሆነው የታዩበት፣ አንዳንዶችም ማንነታቸው እና እነሱነታቸው በንጹኃን ደም የተጨማለቀበት፣ በማንኛውም መንገድ ሀገራቸውን ያስከፉበት ዘመን መሆኑ ገብቷቸው ከልብ ተፀፅተው ይቅር በሉን ሊሉ ፈልገው ይሆን? ስልም ተጠራጥሬያለሁ፡፡

ምን መጠራጠር ብቻ እኩይ ድርጊታቸው አክትሞ መጪው ጊዜ አዲስ “ሰው’’ የሚሆኑበት ሊሆን ይገባል ይሄን ካደረጉ እሰየው! በማለት ከልብ ተመኘሁላቸው እንጂ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ “ያን ሁሉ አረመኔያዊ እኩይ ድርጊታቸውን በምን ይክሱ ይሆን? መጠበቅ ነው እንግዲህ ሰናይ ነገር ካሰቡ በማለት በሀሳቤ ሳወጣ ሳወርድ የመሰባሰባቸው ምስጢር እኔ እንደጠበኩት ሳይሆን ያው የተለመደ የእሪያ እጥበት ሆኖ አገኘሁት፡፡ እኔስ ሞኝ ነኝ እንጂ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቄ፡፡

የአዲሱ ዓመት አዲስ መዝሙር አድርገው የቋጠሩት ስንኝ ደግሞ “…….. ሽብርተኛ መባል የአርበኝነት ሜዳሊያ ሆኗል፣ አዲሱ ዓመት በስልጣን ላይ ያለው ዘረኛ ተወግዶ ነፃና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትገነባበት እንድትሆን…’’ የሚል ሆኖ አገኘሁት፡፡ “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም’’ እንዲሉ የመዝሙሮቹ አቀንቃኝ በሽብርተኝነት ክስ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በባዕድ ሀገር በየሰው ታዛ እየተዘዋወረ የሚዘላብደው ራሱን ግንቦት 7 ብሎ የሰየመው ተቃዋሚ ድርጅት መሪ ነኝ ባዩ ግለሰብ መሆኑን ሳውቅ “ነገሩ ለካስ ወዲህ ነው….” ብዬ ሳላስበው “ኧረ ወዳልኝ!” አልኩ ለራሴ፡፡

“ምኞትን ተመኘው እንጂ የምኞትህ ባሪያ አትሁን’’ እንዳለው አንድ ምሁር ‘’2004 የኢትዮጵያ ወጣቶች የለውጥ ዓመት ይሆናል’’፡፡ ብለው ተመኝተዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ እነሱ “ለውጥ’’ ብለው የሚሉትን አባባል ያየው፣ የደረሰበት፣ እኩይ ድርጊቱን የታዘበውና የገፈቱ ቀማሽ ሆኖ ያለፈበት እንደሆነ ጠንቅቆ ያወቀዋል ፡፡ ምን ያውቀዋል ብቻ በእነሱ አባባል “ለውጥ’’ ሲሉ “ነውጥ’’ ማለታቸው መሆኑን ቀድሞ ተረድቶታል፡፡

እነሱ አልገባቸውም እንጂ የወጣቱ ፉከራ፣ ቀረርቶና እንጉርጉሮ አንድና አንድ ብቻ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ልማት! ልማት! ልማት! አሁንም ልማት! በቃ ለዚህ ሀገር ደዌ ፍቱን መድሃኒቱ ሌላ ምንም እንዳማይሆን ተገንዝቧል፡፡ ልማት! ብቻ፡፡

በመሆኑም ወጣቱ በሀገሪቱ የተጀመረው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ ልክ እንደ ዓይኑ ብሌን ጠብቆ ከዳር ለማድረስ በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት ውስጥ ሆኖ የነውጥ አቀንቃኞቹን ያረጀና ያፈጀ እሮሮ ለማዳመጥ ጊዜ የለውም፡፡ ከ97ቱ እኩይ ድርጊታቸውም ብዙ ተምሯል፣ በብዙም ተማሯል፡፡

በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ራዕይ ሰንቆ ብሩህ ዘመንን ከሩቁ እየተመለከቱ ወደዚያ የሚያመራውን ጎዳና ተከትሎ በአዲስ መንፈስ መጓዝ፣ ያለፉትን ደካማ ጎኖች ተመልክቶ የሚቃኑበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ውጤታማና ፍሬያማ የሆኑ ተግባራት ይበልጥ የሚጎለብቱበትን መንገድ መሻት፣ እድገትና ብልጽግናን መመኘት ለዛሬው ወጣት የአውድ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ ወግ ነው ፡፡

ከጥንት ጀምሮ ብዙ ትውልድ በዚህች ምድር ላይ ተመላልሷል፡፡ ወጥቷል፣ ወርዷል አልፏል፡፡ ዘመን ሲያልፍ፣ ዘመን ሲተካ ሰው ሲያልፍ፣ ሰው ሲተካ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የለገሰችውን የቅብብሎሽ ህግ ተቀብሎ ሲተካካ ኖሯል፡፡ ወደፊትም ይኖራል፡፡ በዚህ ሂደቱ ደግሞ መልካሙን እየሻተ ክፉውን እያስወገደ ሰላምን አየዘመረ እድሜና ጤናን እየተመኘ መጥቷል ፡፡ ዛሬ ላይም ደርሷል፡፡ የእነዚህ የጉዶቹ ግን ለየት ያለ ነው፡፡

በአዲስ ዓመት አዲስ ሰው መሆን ማለት ደግሞ ያለፈ ዘመንን ክፉ ሥራ መተው ነው፡፡ በምትኩም ለመልካም ሥራ መነሳሳት፣ የመንፈስና የግብር ፍሬያትን ማፍራት ነው፡፡ የመንፈስ ፍሬዎች ማለት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ራስን መግዛት ናቸው፤አይደል የሚባለው፡፡ የእኛዎቹ ጉዶች ግን ለእኛ የተመኙልን ከዚህና ከዚያ፣ ከውጪና ከውስጥ የሆነና ያልሆነውን እያጣቀሱ የነውጥ መርዝ በመርጨት እርስ በርሳችን እንድንጨፋጨፍ ሁከትና ብጥብጥ በሀገሪቱ እንዲነግስ የመፈለግ ነው፡፡ በዚህም አሁንም ድረስ እንደተጠናዎታቸው ያለው ህገ መንግሥታዊ ሥርአቱን በኃይልና በአመጽ የመደረማመስ ከንቱና ሰይጣናዊ ቅዥት የአዲስ ዓመት ራእያቸውና ለሕዝብ ያቀረቡት ስጦታ ሆኖ ቀርቦልናል፤አለመታደል ይሏችኋል ይህ አይነቱ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ አይደለም?

ባለፈው ድርጊት ተፀጽቶ ከሰሩት ኃጢያት ራስን አፅድቶ ይቅር ባይነትን ተላብሶ አሁን ላለው ወጣት በጎ ድርጊትን በማውረስ ሀገሪቱ ከገባችበት ድህነት የምትላቀቅበትን መንገድ ማሳየት እንጂ የብጥብጥና የሁከት መርዝ መርጨት እንደማያዋጣ የመድረኩ ተዋንያኖች ሊያውቁት ይገባል ባይ ነኝ፡፡

መድረክ የተሰኘው የተቃዋሚ ጎራ ስብሰብ በሰሞኑ መግለጫው በግልፅ ያሰፈረው ጉዳይ የሚያመላክተው እኩይ ድርጊታቸውን ነው፡፡ ይህንኑ አመለካከታቸውንም በወጣቱ ላይ በኃይል ለመጫን ይሻሉ፡፡ መድረኮች እንዲህም አሉ፡፡ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ሕዝቡ ለከፍተኛ ረሃብ፣ ድህነት፣ አፈናና ጉስቁልና ተዳርጓል፡፡ ለህዝብ ሰቆቃና ቸነፈር ከመጨነቅና በግልፅ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ረሃቡን፣ እንግልቱንና እርዛቱን ከዓለምና ከኢትዮጵያ ህዝብ በመደበቅ የዕድገትና የብልፅግና መዝሙር መዘመር መለያ ባህሪያቸው ሆኗል፡፡ የሚያሳዝነው ኢህአዴግ ከቀድሞዎቹ አገዛዞች መባሱና ተገቢውንም ትምህርት ሊቀስም አለመቻሉ ነው፡፡ ከቀደምት አገዛዞች ትምህርት ሊቀስም ብሎም ሊለወጥ ይገባው የነበረው ኢህአዴግ የቀደሙትን የአገዛዝ ዘይቤዎች ተከትሎ እየነጎደ ይገኛል፡፡ በማለት የውስጥ ፍላጎታቸውን ለመተግበር የመፈለግ የተለመደ የሙሾ እንጉርጉሮ ማሰማት ሆኖ አገኘሁት፡፡

ውድ አንባቢዎቼ ይህን የሰሞኑን የመድረክ የሰለቸ ወሬ ልብ አላችሁልኝ? ምን ይዘላብዳሉ እንደምትሉ ይገባኛል፡፡ ለመሆኑ በድርቅ ለተጎዳ ህዝብ ልማትን ማፋጠን ነው? ወይስ በአዲሱ ዓመት ‘ትግሉ ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባር መሸጋገር ይኖርበታል ብሎ ሀገሪቱን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ለማስገባት መሯሯጥ፡፡ የእነሱ ከንቱ ህልም አይሳካላቸው እንጂ ለአዲሱ ዓመት ድንቅ ስጦታ ሊያበረክቱልን የፈለጉት ይህንኑ ነበር፡፡

መንግስት የእድገትና የብልጽግና መዝሙር መዘመር የጀመረው በሀገሪቱ ስር ሰዶ የኖረው ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ተጨባጭ መርሀ ግብር ነድፎ መንቀሳቀስ ስለጀመረ እንደሆነ ሊያወቁት ይገባቸዋል፡፡ ለድህነታችን ወሳኝ መፍትሄው አቁማዳ ተሸክሞ ለልመና መዘጋጀት ሳይሆን በልማት መትጋት መሆኑን ሊገነዘቡት ያስፈልጋል፡፡

መንግስት ከቀደሙት አገዛዞች ትምህርት ሊቀስም ይገባው ነበር ብለው ለሚያዜሙት ደግሞ ምላሹ ግልጽ ነው፡፡ የቀደሙት ያልከወኑትን የህዝባቸውን ችግር ሸፋፈነው ለማለፍ የፈለጉትን ያንን አስከፊ ጊዜ ዳግም ላለማየት ባለው ቁርጠኝነት ልማትን ሰንቆ ፣ ራዕዩን አንግቦ በልማት ጎዳና መረማመድ ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ የተመለከቱት ሀቅ በመሆኑ እየጎመዘዛቸውም ቢሆን ሊቀበሉት በተገባ ነበር ፡፡

መንግስት ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የቅድመ ጥንቃቄ ስራን ከውኖ ተጨማሪ እገዛ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲሻ የአገሬ ተቃዋሚ መሪዎች ምን እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በየኤምባሲዎች ደጅ ተሰልፈው እርዳታ አንዳትሰጡ፣ ለእርዳታው የተገኘውን ገንዘብም ሆነ እህል እኛን ለመውጋት የጦር መሳሪያ ይገዛበታል በማለት ለህዝብ አሳቢ በመምሰል የአዞ እንባ ሲያነቡ መሰንበታቸውን የማናውቅ ይመስላቸዋልን?

“የሚናገሩትን አያውቁምና ይቅር በሏቸው’’ እንዳለው ቅዱስ መፅሐፉ የልባቸውን ተናግረው ሲያበቁ በለበጣ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ህዘብ እንኳን አደረሰህ ለማለት እንወዳለን በማለት ሲሳለቁብንም ሰምተናል፡፡

እናማ እኔና ጓደኞቼ አንዲሁም ሰላም ወዳድ ዎገኖቼ እንደናንተ አይደለንምና ይህን መልካም ምኞት ልንልክላችሁ ወደድን፡፡ ዓመቱ ከወንጋራ ደንጋራ ሀሳብና ከንቱ ዲያብሎሳዊ ቅዥት ወጥታችሁ እንዲያውም ጭራሽ ሽራችሁና በቅድሚያ ከራሳችሁ ታርቃችሁ መልካሙን የሚያስመኛችሁ ዘመን እንዲሆንላችሁ ተመኘን -ሰላም፡፡