ለልማታችን መፋጠን የህዝብ ግንኙነት ሚና ወሳኝ

በዮናስ ያስችለዋል

የሕዝብ ግንኙነት ሙያ በሳይንስነቱ ታውቆ በተግባር መዋል የጀመረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ በአለም ሀገራት ይህንን ሙያ ለልማታቸው ማሳደጊያና ለዜጐች የግንኙነት አግባብ ስልታዊ ማዳበሪያ በማድረግ በትምህርት ደረጃ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ሙያ ባደጉት ሀገራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ዕዉቅና በመሰጠቱ ሳይንሳዊ እሳቤውን ይዞ ሙያው የሚከበርበትና ለምርትም ሆነ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት  አስተዋጽኦው የላቀ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

መንግስታትም ሆነ የተለያዩ የግል ተቋማት ለሙያው ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ ምክንያቱም የሚያስገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ ለተቋሞቻቸው ምሰሶ ወይም የጀርባ አጥንት እንደሆነ በመግለጽ ሙያውን ሲያሞካሹት ይደመጣሉ፡፡

በእኛም ሀገር ስንመለከት የሙያውን ከበሬታና የሚያስገኘውን ውጤት በመመልከቱ ረገድ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለሙያው ትኩረት መስጠት መጀመሩ በሁሉም መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና የማስፈፀሚያ መሣሪያዎች እንዲሟሉ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከሞላ ጐደልም የሕዝብ ግንኙነት ሙያ ፅንሰ ሃሳብ በሕዝቡ ዘንድ ለማስረጽ ጭምር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች  እየተስተዋሉ ነው፡፡ ባለሙያውም የተሰጠውን የሙያ ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኝነቱን እያሳየ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ደግሞ በሀገራችን ከአስተሳሰብ ስራ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው የሕዝብ ግንኙነት ስራ በመሰራቱ ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት መመዝገብ መቻሉ ነዉ፡፡

ከቃሉ ፍቺ ስነሳ የህዝብ ግንኙነት ሁለት ቃላትን አጣምሮ የያዘ ሲሆን የመጀመሪያው “ሕዝብ” ነው፡፡ ሕዝብ ማለት በአንድ አካባቢ በብዛት የሚገኙ ወይም የሚኖሩ ሰዎች በአጠቃላይ ማለት ሲሆን፤ ”ግንኙነት ” ደግሞ የተለያዩ ወገኖች ለተለያዩ ዓላማዎች ሲሉ በመካከላቸው የሚፈጠረው የቀረቤታ ስርዓት እንደሆነ የአማርኛ መዝገበ ቃላታችን ያስረዳናል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት እንደሙያ ሆኖ ሳይንስነቱ ተረጋግጦ ለስራ ከመዋሉ በፊት በተለያዩ መጠሪያዎች ስያሜ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ ፕሮፖጋንዳ፣ ፖሊሲ ማውጫ፣ የማስታወቂያ ስራ እና የመሳሰሉት ቃላት በተለያዩ ዘመናት መጠሪያዎቹ ነበሩ፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ሙያ ሳይንሱ ከመዳበሩ በፊት የሚከተሉትን ደረጃዎችን እንዳለፈ ምሁራን ያብራራሉ፡፡ እነዚህም የእድገት ደረጃዎች ጥንታዊው የሕዝብ ግንኙነት፣ የፕሮፖጋንዳ ደረጃ የሕዝብ ግንኙነት፣ ቀዳሚው የሁለትዮሽ ግንኙነትና የዳበረ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማለት በተዋረድ ተቀምጠዋል፡፡  የህዝብ ግንኙነት እድገት ሶስት ደረጃዎችን አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያለፈበትን መንገድ መቃኘት እና በአጻራዊነት ለመመልከት ያስችለናል፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያዉ የህዝብ ግንኙነት ጅማሬ ጥንታዊ የህዝብ ግንኙነት ይባላል ፡፡ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1800አ.አ በዛሬይቱ ኢራቅ በአርኬኦሎጂስቶች አማካኝነት የድንጋይ ላይ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡ ጽሁፎቹም ስለ ሰብል አሰባሰብ እና ሰለ እህል አዘራር የሚናገር መረጃ እንደነበር ይጠቁማል ከዚያም አለፍ ብሎ በአሜሪካ ከ1787 እስከ 1789 ድረስ አሜሪካንን ነጻ መዉጣት የሚደግፉ 85 ደብዳቤዎች የተሰራጩበትና ሚዲያዎችም የተስፋፉበት ዘመን ነበር ፡፡ጆረጅ ዋሽንግተን በ1800 የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ቀጥሮ የህይወት ታሪኩንና የወቅቱን ሁኔታ እንዳጻፈ ታሪክ ይነግረናል ይሄም የህዝብ ግንኙነትን ጅማሬ አመላካች ሊሆን እንደሚችል ያሳያል በሁለተኛ ደረጃነት ደግሞ የፕሮፖጋንዳ ደረጃ ነዉ፡፡ እ.ኤ.አ ከ1830 ጀምሮ የጋዜጦች ስርጭት በሀገረ አሜሪካ መስፋት ጀመረ፤ በዚህም ድርጅቶች ሊገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጠረ ፡፡

ሙያዉ ሊሰፋ የቻለዉ በዚህ ዘመን የፕሮፖጋንዳ እና የቅስቀሳ ቢሮ በ1906 በቦስተን ተከፍቶ ስለ  ነበር ይሄም የተለያዩ ተቃዉሞችን የማረጋጋት ሚና ነበረዉ በዚህ ደረጃ የሕዝብ ግንኙነት በአንድ አቀጣጫ ብቻ ነበር የሚፈሰዉ ሶስተኛዉ ደረጃ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይባላል ይህም ማለት ከመንግስት ወደ  ሕዝብ  ከህዝብ ወደ መንግስት  ግንኙነቱ የዳበረ የሁትዮሽ ሆኖ እናገኛዋለን፡፡ይህ ዘመን ከአንደኛዉ የአለም ጦርነት በኃላ ያለዉን ጊዜ ሊያሳይ ይችላል፡፡  ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ቴክኒካዊ በሆኑ ሳይንሳዊ መንገዶች የዳበረና እንደሙያ ተቆጥሮ የተለያዩ ሀገራትን  እውቅናና ተቀባይነትን ማግኘቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የሁለትዮሽ አሰራር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበትና በዘመኑ ከሚፈበረኩ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂዎችና አስተሳሰቦችም ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ተፈላጊነቱም የዚያኑ ያህል ሊጨምር ችሏል፡፡የመጨረሻዉ ና በዛሬዉ እርከን ላይ የደረሰዉና የዳበረዉ የሁለትዮሽ ግንኙነት ጥበቡ እየሰፋ እና ተቀባይነት እያገኘ መምጣት ቻለ ለሙያው አስተዋጽኦ ካደረጉት ክስተቶች መካከልም የመገናኛ አውታሩ ዘመናዊነትና በስፋት መሰራጨት፣ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ መፈጠር፣ የመረጃ ፍሰት እየጨመረ መሄድ፣ የተለያዩ ተቋማት መስፋፋትና ቁጥራቸው ማሻቀብ ለእድገቱ ምክንያት እንደሆኑ ይታሰባል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ዓላማ የተቋሙን ስኬታማነት አስጠብቆ ለማስጓዝ ሙያዊና ሰትራቴጂያዊ ስልቶችን ቀይሶ በተገልጋዩ ዘንድ በጎ እይታ በተቆሙ ላይ እንዲኖረዉ ለማስቻል ይጥራል፡፡ ህዝብ ግንኙነት የተግባቦትን ሚና ስለሚጫወት ለደንበኛዉ እዉነታዉን እና ተጨባጭ  ክስተቶችን የሚያስመዘግብ ነዉ ፡፡   ከሌሎች ተቀማት ጋር በጋራ ጉዳዮች በእዉነታ ላይ የተመሰረተ ተግባር ዉስጥ ገብቶ የጋራ ተግባቦትን የመፍጠርን አላማ ሰንቆ የሚንቀሳቀስ ነዉ፡፡ በመሆኑም የህዝብ ግንኙነት ስራ የዲሞክራሲ ስርአት እና በልማት ዉስጥ አላማዉን ቀርጾ ሰራዉን በእቅድ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ የመተግበር አቅምን አዳብሮ የአስተሳሰብ ስርጸት የሚከዉንበት የሙያ ዘርፍ ነዉ፡፡ መንግስት እና ህዝብን በማገናኘ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ጠቅለል አድርጐ ለማስቀመጥ ያህልህዝብ ግንኙነት የተለያዩና በርካታ አላማዎች በአንድ ድርጅት ወይም በግለሰብና በሕዝብ መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር የጥቅም ግጭቶችን በጋራ የመፍታት ዓላማ የሰነቀ ሙያ ነው፡፡ ባለሙያው ከተቋሙና ከደንበኞቹ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲፈጠርና የጋራ ጥቅም በትክክለኛ ደረጃ ላይ እንዲመሰረት በማድረግ ተጠቃሚው ከአገልግሎት ሰጪ አካሉ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህንንም ሲተገብር የተለያዩ ስልቶችን በመዘርጋት የግንኙነት አግባቦቹን ተመራጭና ሳቢ በማድረግ መ/ቤቱ ይዞት ከተነሳው ዓላማ የተቀዳ አስተሳሰብ የማስረጽ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ባለሙያው ስራውን ሊከውን ከሚችልባቸዉ መሳሪያዎች ውስጥ ለአብነት የሕትመት ሚዲያ፣ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፣ የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲዘጋጁ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ በአላትን መሠረት በማድረግ እና በሌሎችም ስልቶች በመጠቀም የሚፈልገውን የማሳመን ስራ ሊያከናውንበት እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ በመሆኑም ባለሙያው በተለይም ከተቀጠረበት መ/ቤት  ከበላይ አመራሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ተፈላጊውን አስተሳሰብ በመቅረጽ በእቅድ ተደግፎ አስፈላጊውን ውጤት ማስገኘት ይቻላል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት የዴሞክራሲ ስርዓት መገንቢያና በተወሰነ እንቅሰቃሴና ፖሊሲ አማካኝነት በሕዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ልማታዊና ሰላማዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚረዳና የአመራር ኃላፊነትን እና የመስሪያቤቱን አጠቃላይ ጓዳ የሚረከብ የሙያ ዘርፍ በመሆኑ፤ ይህ ሙያ የእድገት ጐዳናን ለማፋጠን ሚናው የላቀ መሆኑ ሊታመን ይገባል፡፡

ባለሙያዉ ስለሙያው ምንነትና ለመ/ቤቱ የሚያበረክተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በጥልቀት በመረዳት አዋጭነቱንና ተመራጭነቱን ተቀብሎ ለሙያው ከበሬታ በመስጠትና በማስፈፀሚያ መሳሪያዎቹ ላይ ትኩረት በማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ተቋማት ይዘው የተነሱት ዓላማ ይፈፀም ዘንድ የአስተሳሰብ ስራዎች መከወን ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ  የሕዝብ ግንኙነት ሙያና ባለሙያዎች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ታውቆ ትኩረት ያሻዋል የሚል መልዕክቴን እያስተላለፍኩ ጽሑፌን በዚሁ ላብቃ ሰላም!