አህጉራዊ ጥረትን ስሚጠይቁ የቤት ስራዎች / ክፍል ሁለት

አህጉራዊ ጥረትን ስሚጠይቁ የቤት ስራዎች 

ኢትዮጵያን፤ ለሁለተኛ ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የተለዋጭ አባነት መቀመጫ እንድትገኝ ካደረጓት መሰረታዊ ምክንያቶች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው፤ መላው የአፍሪካ ሀገራት ከግብፅ፣ከሴኔጋልና ከኤርትራ በስተቀር) ሁለንተናዊ ሊባል የሚችል የአህጉራዊ ትብብር መንፈስ እጅግ ጎልቶ የተንፀባረቀበትን ድጋፋቸውን የገለፁበት አግባብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ የአህጉሪቷን ህዝቦች ከሚያምሳቸው የሰላም እጦት ለመታደግ ያሳየውን ተነሳሽነት ለሚገነዘብ ሰው አሁን የአፍሪካ ሀገራት በሰጡን ድጋፍ እንብዛም ሊደነቅ እደማይችል ቢገባኝም ፤ዓለም አቀፉ ማህረሰብ እውነታውን አምኖ እንዲቀበልና በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ጤናማ ያልሆነ ግምት ሙሉ በሙሉ እንዲቀይር በማድረግ ረገድ እነ ኤ.ዩ. የተጫወቱት አወንታዊ ሚና ቀላል እንዳሆነ ግን ደፍሮ መናገር ይቻላል ፡፡

እናም የሃተታዬ ትኩረት አድርጌ ያነሳሁት ዲፕሎማሲያዊ ርዕሰ ጉዳይ ስናስብ አብሮ መታሰብ የሚኖርበት ቁልፍ ነጥብ፤ኢትዮጵያ መላው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ባሰደሩባት እምነት ልክ የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል አመርቂ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባት የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት ውስጥ ያገኘችውን የተለዋጭ አባልነት መቀመጫ እንደመልካም ዕድል ተጠቅማ ማከናወን ካለበት ቀዳሚ ተግባር አንዱ ሆኖ የሚሰማኝ፤በተለይም እንደነ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ዓይነቶቹ ጎረቤት ሀገራት ውስጥ የሚስተዋለው አጠቃላይ ቀውስ እኛም ላይ ጭምር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሊያሳድር የሚለውን አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስቀር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አሁን እየተደረገ ያለውን ፈርጀ ብዙ ጥረት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይር ስራ መስራት ነው፡፡

ይህን ስል ደግሞ፤የተጠቀሱትን ሁለት ጎረቤት ሀገራት ጨምሮ፤ሌሎች በየራሳቸው የውስጥ ችግር ምክንያትም ሆነ ከዓለም አቀፋዊ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር ተያያዥነት ባለው ስርዓት አልበኝነት እየታመሱ የሚገኙ አፍሪካውያን ህዝቦችን ከገጠማቸው የሰላምና መረጋጋት ቀውስ እንዲወጡ ለማድረግ ሲባል የሚካሄድ እንቅስቃሴ ሁሉ፤የሚፈለገውን ያህል ፍሬያማ ሆኖ ለማየት እንችል ዘንድ ዓለም አቀፋዊው ማህረሰብ የምር አምኖበት ከጎናችን መሰለፍ አለበት ማለቴ ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያ አሁን የተመረጠችበትን አህጉራዊ ኃላፊነቷን ተጠቅማ የዓለም ማህረሰብ ለአፍሪካ ችግሮች ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ የሚስገድድ ተፅእኖ ማሳደር ይጠበቅባታል ፡፡ 

ይልቁንም ደግሞ የወቅቱ ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢ አደጋ እንደሆነ ለቀጠለው የሽብር ቡድኖች ድንበር ዘለል እቅስቃሴ እጅግ የተጋለጠ ተደርጎ በሚቆጠረው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያጠላበት የስጋት ዳመና ተገፍፎ የምናይትን የዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ዘመን በእጅጉ እንደምንናፍቅ ዓለም አቀፉ ማበረሰብ ይረዳልን ዘንድ ከኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ግንኑነት ተልዕኮ የሚጠበቅ ተጨማሪ ጥረት አለ የሚል ለእምነቴን በዚህ አጋጣሚ  አላልፍም፡፡ ለመሆኑ በኤርትራ ሳገልፅ ህዝብ ላይ የኢሳያስ አፈወርቂ ግፈኛ አገዛዝ እየፈፀመ ያውን ፈርጀ ብዙ በደልስ ዓለም አይቶ እንዳላየ የሚያልፈው እስከመቼ ይሆን?ብሎ መጠየቅም ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ፡፡

ምንም እንኳን በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ውስጥ ስሚስተዋለው እጅግ በጣም አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጉዳይ  ይፋ ያደረገውን ጥናታዊ መረጃ ለአፍሪካ ህብረት መርቶታል መባሉ አንድ ነገር ቢሆንም፤ ያቺ ጎረቤት ሀገር ለዜጎቿ ወደምድራዊ ሲኦልነት ከተቀየረችባቸው ዓመታት መቆጠራቸውን ስናጤን ግን አሁንም፤ ዓለምአቀፋዊው ማህበረሰብ የሰጠው መፍትሔ ውሃ የሚያነሳ አይደለም ያሰኛል ፡፡

አስተዛዛቢው የሴኔጋል ነገረ- ስራ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በመላው አፍሪካውያን ህዝቦች ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጣት ስለመሆኗ ተደጋግሞ ተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም እነ ሴኔጋል የሚገኙበት የአህጉሪቱ ምዕራባዊ ክፍል፤ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያይበት ዓይን ምን ያህልስ የአፍሪካዊ ወንድማማችነትን መንፈስ የተላበሰ ሆኖ እንደሚገለፅ መረዳት የሚቻለው ደግሞ፤ሀገራቱ ከዘመናት የአውሮፓ መንግስታት ቅኝ አገዛዝ ነፃ እየወጡ የየራሳቸውን ልዑዋላዊነት በተቀዳጁበት የታሪክ አጋጣሚ ስራ ላይ ያዋሉት ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሳይቀር ከእኛው፤አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብረ- ቀለማት ጋር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ እዲዛመድላቸው ለማድረግ የሞከሩበት አግባብ መስተዋሉ  ይመስላል፡፡

በአጠቃላይ የድህረ- ቅኝ አገዛዝ አፍሪካ ሀገራት ነፃ መንግስታት፤ኢትዮጵያን ከነጭ አውሮፓውያን የዘመናት ባርነት መላቀቅ የሚቻልበትን የነፃናት ፋና እንደወጋችላቸው ተምሳሌት አድርገው የወሰዱበት ታሪካዊ እውነታ ስለመኖሩም ነው ዓለም አቀፉ ማህረሰብ የሚስማማበት ጉዳይ፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ሀገራችን ለመላው አፍሪካውያን ህዝቦች፤የአርነት ችቦ እንደለኮሰ የሚታመንበትን የዓድዋውን አንፀባራቂ ድል በማስመዝገብ ረገድ የተጫወተችውን ታሪካዊ ሚና ለመላው አፍሪካዊያን ነፃነት መረጋገጥ ባለውለታ የሚያደርጋት መሰረታዊ ታሪክ ሀቅ ስመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

እናም የኢትዮጵያ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎና እንዲሁም ደግሞ የተጋድሎዋ ድምር ውጤት መገለጫ ተደርጎ የሚቆጠረውን የማይገሰስ ነፃነት ታሪኳን ፈለግ እየተከተሉ የየራሳቸውን ሀገር ለዑዋላዊነት በመሻት ረገድ የመሪተዋይት ሚና ተጫውተዋል ተብሎ የሚነገርላቸው የአዲሲቷ አፍሪካ መስራች አባቶች ሁሉ፤ ለዚች አገር ህዝቦች ያቸውን ተገቢ አክብሮት የሚመለክት ወንድማማችነታቸውን የሚያንፀባርቅ ጤናማ ገፅታ የተላበሰ የመንግስት ለመንግስት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነተታቸውን ማጥበቅ ከጀመሩ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ስለማስቆጠረቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካውያን ህዝቦች ነፃነትና ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣፈንታ የፋና ወጊነትን ሚና ለመጫወት የሚያስችል የመንግስታትታሪክ ቁመና አላት ከሚል አንድምታ የሚመነጭ የአህጉሪቱ መሪዎች ዲዲፕሎማሲያዊ ዝምድና እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተለይም ሴኔጋልን የመሳሰሉ አንዳንድ ሀገራት እኛ ላይ በጎ አመለካከት የላቸውም ወደሚል ድምዳሜ የሚገፋፋ አዝማሚያ የሚያሳዩበት ሁኔታ ሲደጋገም ይስተዋላል፡፡

ለዚህ ደግሞ፤በተለይም ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የአህጉሪቷን ህዝቦች የጋራ ዕጣ ፈንታ የተቃና ለማድረግ ሲባል፤ቀደም ሲል በአ.ኤ.ዩ.ከዚያም በኤ.ዩ. አማካኝነት መላው የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት የሚወከሉባቸው የመሪዎች መሰብሰቢያ መድረኮች ላይ፤ኢትዮጵያን የሚመለከት አከራካሪ ጉዳይ በተነሳባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ፤ሴኔጋል ስታሳይ የቆየችውን አሉታዊ አቋም ማስታወስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህልም አንድ ወቅት በተካሄደ የአፍሪካ ሀገራት የመሪዎች መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አልቃዛፊ ፤የህብረቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ  ተነስቶ ወደ እርሳቸው ሀገር መዲና ወደትሪፐሊ እንዲዛወር ለማድረግ ያለመ  ኢትዮጵያን የማጥላላት ዘመቻቸውን በከፈቱብን ጊዜ የሴኔጋ ፕሬዝዳንትና ተከታዮቻቸው ጋዳፊን የሚደግፍ አዝማሚያ እንዳሳዩ አይዘነጋም ፡፡

ይህን ጨምሮ በሌሎችም የአህጉሪቷ መሪዎች የጋራ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያ ለምርጫ የቀረበችባቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ፤በዝርዝር እያነሳን ለማስታወስ ብንሞክር ሴኔጋል አንድም የለየለት ተቃውሞዋን ገልፃለች፤አልያም ደግሞ በድምፅ ተዓቅቦ ነው ያለፈችው ጉዳዩን ደግነቱ ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚነስቴራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በውል የሚወቁበት ዲፕሎማሲያዊ ብቃት ነገሩን ጎልቶ እዳይወጣ በሚያደርግ ዘዴ ይይዙት ዘንድ ረድቷቸው መቆየቱ ነው፡፡ እግዲያውስ የዚህ መጣጥፍ ማጠንጠኛ በሆነው የኒወርኩ የመንግስታቱ ድርጅት ሰሞነኛ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆኖ እንዳትመረጥ መፈለጋቸውን የሚመለክት አሉታዊ ሚና ከነበራቸው አምስት አገራት መካከል ፤የምዕራብ አፍሪካዋ ሴኔጋልም ትገኝበታለች መባሉን ስሰማ ጉዳዩ ኢ-ምንያታዊና መፍትሔ የሚሻ እንቆቅልሽ ጭምር ሆኗል ፡፡

ስለዚህ አስተዛዛቢው የሴኔጋል መሪዎች ነገረ -ስራ ከምን የመነጨ «ታሪካዊ ባላንጣነትን» መሰረት አድርጎ እንደሚንፀባረቅ የሚያስረዳ ዲፕሎማሲያዊነትንተናን የሚጠይቅ ጉዳይ እየሆነ ስለመምጣቱ ፤የኢፌዴሪ መንግስት አግባብ ያላቸው አካላት ልብ ይሉልኝ ዘንድ በታላቅ አክብሮት ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ይሄን የምልበት ምክንያት ደግሞ የነገሩ መደጋግም ሲታሰብ ለመሆኑ ሴኔጋልን ከኢትዮጵያ ጋር በዚህን ያህል መጠንያቃቃራት ተጨባጭ ምክንያት ምንደነው ?የሚለው ጥያቄ አዕምሯችን ውስጥ የሚቃጭልብን ዜጎች በቁጥር ጥቂት እንደማንሆን መገመት አይከብድምና ነው፡፡ ስለሆነም እንደኔ እንደኔ ያቺ ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ለምን ይህን ያህል ጥርሷን ልትነክስብን እንደቻለች፤በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራችን የማያሻማ ማብራሪያውን ሊሰጥበት ይገባልየሚል እምነት ነው ያለኝ ፡፡ በተረፈ ግን ሰላም አይለየን !