ለኢምክንያታዊ ትችቶች ቦታ የማንሰጥበት ጊዜ ላይ ነን

 

 

ሰሞኑን መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ ህገ መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው ይኼ አዋጅ፣ የማስፈጸሚያ ደንብና መመርያም ወጥቶለታል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑ የተለያዩ ክስተቶችም ስለመኖራቸው በመንግስት በኩል በስፋት ተብራርቷል፡፡ እነዚህ ክስተቶችም የሚጠቃለሉት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና ሃገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥልና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማያስችል መሆኑ ላይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አዋጁን አሁንም የተለያዩ ስያሜዎች እየሰጡ ሃገሪቱ ወደባሰ ቀውስ እንድትገባ፤ በተለይ በውጭ የሚገኙ የኒዮሊበራል ሃይሎች በመትጋት ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም፣  የአዋጁን ምክንያቱን በጥልቀት መመልከት ጠቃሚ ይሆናል። ከምልከታው አስቀድሞ ግን የሚሹትን ሁሉ ለማግኘት በሩ የተዘጋባቸው ሃይሎች ከሰጧቸው እይታዎች ጥቂቶቹን መመልከት ስለአዋጁ አፈጻጸም ዋነኛ ለሚሆነው የህዝብ ተሳትፎ በተመሳሳይ ጠቃሚ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  በእስር ላይ የሚገኙ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ደህንነት አደጋ ውስጥ እንደከተተ መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው ሪፕሪቭ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም  የጉዳያችን የመጀመሪያው ማጠየቂያ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 29/2009 በመላ ሀገሪቱ የደነገገው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሀገሪቱ ለገባችበት ችግር መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ምሁራን መናገራቸውን የተመለከተው የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ዘገባም ተከታዩ እና ስለሂሳችን በማሳያነት የተወሰደ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሀገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊያባብስ ይችላል ሲል በሃገራችን ላይ በሚሰጠው በማይታክት መግለጫው የምናውቀው ሂውማን ራይትስ ዎችም ዋነኛ ማጠየቂያችን ነው።

 

ሰላም ከሁሉም በላይ መሠረታዊ ከሚባሉና ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው። ሰላም ከሌለ ልማትና ዕድገት አለመኖራቸው አያከራክርም፡፡ በህይወት የመኖርና ከአካላዊ ደኅንነት የተያያዙ ይልቁንም የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው ሊያገኙ የሚገባቸውን እና ማንም ከልካይና ነሺ የማይሆንባቸው መብቶች ሁሉ የሚደፈጠጡ መሆኑም አያጠያይቅም፡፡  ላሳለፍናቸው በርከት ያሉ ወራት ባጣነው ሰላምና መረጋጋት  የዜጎች ህይወት መጥፋቱን እና ያለነውም የደኅንነት ስጋት ገጥሞን የነበረ መሆኑን ማን ይክዳል? ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊ መብቶች መነጋገር የምንችልባቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃራኒ ሆነው ያላጨናነቁት ዜጋስ ማነው? በአገራችን ያጋጠሙ ችግሮችን ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለመቅረፍ የሚያስችል ሁኔታስ ነበር ወይ? የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖችን ጨምሮ ተዉ የሚል ዜጋ ሁሉ ሲወርድበት ለነበረው ዱላና ዛቻ መፍትሄው ምን ነበር?  

በቅርቡ በተለያዩ ሥፍራዎች በደረሱ የሕይወት መጥፋቶች፣ የአካል ጉዳቶችና መጠነ ሰፊ የአገር ሀብት ውድመቶች ምክንያት አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ሥጋት ውስጥ መውደቋን ስለምን ይካዳል? በዚህም ሳቢያ መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡ ከዚህ አዋጅ መደንገግ በኋላ በአንፃራዊ ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት መታየቱስ የአዋጁን ትክክለኝነት እንዴት ጥያቄ ላይ ይጥላል?

በእርግጥ መነሳት ካለበት ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን የተመለከተ እና ከልዩ ጥንቃቄ ጋር የሚያያዘው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሃላፊነቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የህዝብም መሆኑን ማመን እና  በሚያደርገው መጠነ ሰፊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ጥያቄውን ያቀለዋል። ይህ ደግሞ የተሳካ እንዲሆን አስቻይ የሆኑ እሴቶች ባለቤት በመሆናችን ሊያስጨንቀን አይገባም። የሃገራችንን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን ስናየው፣ በህዝባችን ውስጥ ለዘመናት የሚታወቁት አኩሪ የጋራ እሴቶች ለሰላም ትልቁን ሚና ይጫወታሉና፡፡ በህዝባችን ውስጥ የሚታወቁት በሰላም፣ በፍቅርና በመተሳሰብ የመኖር ዘይቤዎች ችግሮቻችንን ለመቅረፍም ሆነ አዋጁ የታለመለትን ግብ መቶ ወደነበርንበት እንመለስ ዘንዳ ትልቅ ግብዓት ናቸው፡፡ ልዩነቶችን አክብሮ በመተሳሰብ መኖር፣ ግጭቶችን በሽምግልና መፍታት፣ በአርቆ አሳቢነትና በሆደ ሰፊነት ትዕግሥት ማሳየትና ጥልቅ የሃገር ፍቅር ስሜት የህዝባችን መገለጫዎች ስለመሆናቸው ከላይ የተመለከቱት የአዋጁ ነቃፊዎች ሊገነዘቡልን ይገባል፡፡  

በቅርቡ ያየናቸው ባለቤት አልባ ነውጦች ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ጭምር አጋልጠውን ለአስከፊ ውድመቶች መዳረጋቸውን ዝም ብሎ ሲመለከት ከቆየ በኋላ አዋጁን ማጣጣል ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሆናል፡፡ በነዚህ ነውጦች ምክንያት የህዝቡ ሰላምና ፀጥታ በመደፍረሱና ደኅንነቱ ለአደጋ ሲጋለጥ መንግስት ማድረግ የነበረበትን ሁሉ አድርጎም ስጋቱ ወደሃገር ህልውናም በተጠጋ ጊዜ ምን ሊያደርግ እንደሚጠበቅ ራሳቸው ነቃፊዎቻችን ቢናገሩት ጥሩ በነበር ፡፡

 እንዲህ ዓይነት ቀውስ ያጋጠማቸው ብዙ ሃገራት መፈራረሳቸውን እና ዜጎቻቸው እንደቅጠል ሲረግፉና ለስደት ሲዳረጉ የተመለከቱ ሃይሎች አዋጁን ቢያብጠለጥሉ አላዋቂ ሳሚ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ሞት ጮቤ ረጋጭ ያሰኛቸዋልም፡፡ ከላይ የተመለከቱት ነቃፊዎች የሚያውቋቸው ሃገሮቹ ዳግም ወደነበሩበት በማይመለሱበት ደረጃ ወድመዋል፡፡ ችግሮቻቸውን ገና በእንጭጩ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ቢችሉና ካልቻሉም እኛ የተከተልነውን እና ሰሞኑን ባስገኘልን ፋታ የተረጋገጠውን መንገድ ቢከተሉ ኖሮ ይኼ ሁሉ መዓት የማይወርድባቸው የነበረ መሆኑም አያከራክርም፡፡ ነቃፊዎቻችን የተቀመጡባቸው አውሮፓውያን እስኪንገሸገሹ ድረስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶሪያ ስደተኞች ሕይወታቸውን ለከፋ አደጋ አጋልጠው ቀዬአቸውን ለቀው አይሰደዱም ነበር፡፡  የሰላም ዋጋ ይኼንን ያህል ነው በማለት ለመተመን የሚከብደው እና አዋጁን ለማውጣት ያስፈለገን በዚህ ምክንያት መሆኑን እነርሱ አመኑም አላመኑ እኛ ግን አስፈልጎን አውጥተናል፤ ውጤቱንም በማግስቱ አይተነዋል፡፡

በሃገራችን ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት እና ነውጥ ዋነኞቹ ተጎጂዎች ወጣቶች ቢሆኑም፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጉዳቱ መጋለጡን አውሮፓ እና አሜሪካ የከተሙ ሃሳዊ መሲሆች ሊመሰክሩልን አይቻላቸውም፡፡ ከዜጎች መሞት፣ የአካል ጉዳትና የሥነ ልቦና ስብራት በተጨማሪ፣ በሃገር ሀብት ላይ የደረሰው ውድመት በርካቶችን ለሥራ አጥነት ማጋለጡን እኛ እንጂ እነርሱ የት አይተውልን ነው? በሃገራቸው ሠርተው ለመለወጥ በከፍተኛ ፍላጎት ሀብታቸውን ያፈሰሱ ዜጎች ንብረቶቻቸው ወድመው ለተስፋ መቁረጥ መዳረጋቸውን ሰምተው እንዳልሰማ ሰብአዊ መብት ጂኒ ቁልቋል ቢሉን አይገባንም፡፡ ሊያውም እኮ አዋጁ  ሰብአዊ መብት እንዳይጣስ የሚያስችል ስርአት እና አሰራርን ባካተተበት አግባብ ነው ነቀፌታው።

የሃገሪቱን ሰላምና ደኅንነት በመተማመን ባህር አቋርጠው የመጡ የውጭ ባለሀብቶች መደንገጣቸውን በይፋ ለአለም ተናግረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር ባለፉት አሥር ዓመታት በታየው የኢኮኖሚ መነቃቃት ብዙ የተባለለት የአገሪቱ የዕድገት ጅማሮ ፈተና የተጋረጠበት ሁኔታ ስለመፈጠሩም የነቃፊዎቻችን እህት ኩባንያዎች ሳይቀሩ መስክረዋል፡፡ ይህ አገርንና መላውን ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ያስከፈለ የአገር ገጽታ ግንባታ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲናድ ማን ነው ተጠቃሚው? በአንድ ወቅት የነበረ መንግሥት፣ ትውልድና የአኗኗር ዘይቤ ይቀየራል፡፡ ቋሚና ዘለዓለማዊ የሆነችው አገር ግን ለመጪዎቹ ትውልዶች ትቀጥላለች፡፡ ይህ ትውልድ በታሪክ ተጠያቂ የሚሆንበትን ሳይሆን፣ ለታሪክ ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መነጋገር ሲችል ነው፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውይይትና ድርድር እንዲኖር ደግሞ አዋጁ ቅድመ ሁኔታና ማመቻመቻ ነው፡፡

ሰላምና የህግ የበላይነት ሲኖሩ ለጠብ፣ ለጭቅጭቅ ብሎም ለግጭት የሚዳርጉ ጉዳዮች በሰላማዊ ውይይትና ምክክር መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ወገን ህግ ማክበር ይኖርበታልና አዋጁ ዘግይቷል መባል ሲገባ ነቀፌታው ተራ ምልከታ ይልቁንም የትርምስ ናፍቆት የወለደው ነው፡፡ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥት የያዛቸው መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ የህግ የበላይነት መረጋገጡ አያጠያይቅም፡፡ ፍትህ መስፈኑና እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት መኖሩም በተመሳሳይ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዴሞክራሲ በተግባር ይታያል፤ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ይለመዳል፤  ከአሉባልታ፣ ከሐሜትና ከጥላቻ የፀዳ ምክንያታዊ ትውልድ ይፈጠራል፡፡ ልዩነትን ያከበረና የአስተሳሰብ ደረጃው የዳበረ ማኅበረሰብ ውይይትን ያስቀድማል፡፡ ኃይልና አፍራሽ ድርጊቶች የኋላቀርነት ማሳያ ሆነው እንዲቀሩ ደግሞ በመረባረብ ላይ ነኝ የሚል መንግስት እንዲህ አይነት ነውጥ በገጠመው ጊዜ ተረጋግቶ መልስ መስጠት የሚያስችለውን የጸጥታ እድል መፍጠር ተግባሩና ግዴታው ነው፡፡       

ስለሆነም ሃገሩን የሚወድ ዜጋ በሙሉ በሃገሩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲፈጠርና ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚኮሩባት አገር እንድትኖር ከአዋጁ ጀርባ ተጠልሎ ነቃፊዎቹን ከመታገል ጀምሮ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ማበርከት አለበት፡፡ በአገር ጉዳይ አያገባኝም ሳይሆን ለዘለቄታው ሰላምና እኩል ተጠቃሚነት ሲባል ለሃገር አለሁ ማለት ያስፈልጋል፡፡  አስተማማኝና መሠረት ያለው ሰላም እንዲገኝ፣ ትክክለኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት የመንግሥት አሠራር እንዲኖር፣ በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥት መቀያየር እንዲለመድ፣ ለብጥብጥና ለግጭት በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮች ቦታ እንዳይኖራቸው፣ ከሐሜትና ከአሉባልታ ይልቅ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ሞጋች ትውልድ እንዲፈጠር፣ የሃሳብ ልዩነትን በማክበር ዴሞክራሲን የሚያለመልም ሥነ ምግባር ያለው ማኅበረሰብ እንዲገነባ፣ ዜጎች ለአደጋ የማይጋለጡባትና የአገር ሀብት ውድመትን የማትቀበል ዴሞክራሲያዊት አገር በጋራ ትገነባ ዘንድ ካስፈለገ አዋጁን መቀበልና ለተግባራዊነቱም በመረባረብ መንግስት በአዋጁ ያገኘውን ፋታ ተጠቅሞ የቀረቡለትን ጥያቄዎች በየደረጃቸው እንዲመልስ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ከመንግስትና ከጸጥታ ሃይሉ የሚጠበቀው ህገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ያሠፈራቸው ነጥቦች  መከበራቸውን መከታተልና ማረጋገጥ ነው፡፡ አዋጁ ተግባራዊ ሆኗልና አጥፊ በሚባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚወሰዱ ተመጣጣኝና ሕጋዊ እርምጃዎች መኖራቸው አያከራክርም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እነዚህን እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠር ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ ከራሱና ከሕግ ባለሙያዎች ከተውጣጡ አካላት አቋቁሟል፡፡ ይህ ቦርድ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲፈጸም የሚከታተልና የሚቆጣጠር ነው፡፡ ዜጎች በዚህ መሠረት አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ ሲቀርብላቸው ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል፡፡ በአፈጻጸሙ ሂደት የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሆኑ መልካም አጋጣሚዎች ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ በኩልም ቦርዱ ሊዘናጋ አይገባም፡፡