ከናዳው ለማምለጥ የምናደርገውን ሩጫ ያጨነገፉብን ሃይሎችን ……

በሃገራችን የኢኮኖሚ  እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ታምኖባቸው ከተያዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን መካከል ያዩ ዩሪያ የማዳበሪያ ፋብሪካ አንደኛው ነው ።መንግስት በ1999 ዓ.ም ቻይና ኮምፕላንት በተባለ የውጭ ድርጅት የያዩ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካን የአዋጭነት ጥናት ባስጠናው መሰረት ፋብሪካውን ለመገንባት አራት ዓመት ጊዜ የሚፈጅ ወይም ደግሞ በመጀመሪያው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን እንደሚጠናቀቅ ተገልጾ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ያም ሆኖግን የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጥናቱን በመከለስ የፋብሪካውን ግንባታ በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሀሳብ በማቅረቡ ኮርፖሬሽኑ ግንባታውን በ2004 ዓ.ም ጀምሮ በ2006 ዓ.ም ለመጨረስ በ2004 ዓ.ም ውል የፈጸመ ቢሆንም ስራው አሁን ድረስ ከ42 በመቶ በላይ ሊንፏቀቅ አልቻለም።

ሃገራችን ከተያያዘችው ልማት አንጻር፤ ሰፊ የተማረ የሰው ሃይል እየፈራ ባለበት በዚህ ሰዓት፤ ታላቁ መሪ ድህነታችን እንደቀድሞው በአለት ላይ ሳይሆን በአሸዋ ላይ የተገነባ ነው እንዳሉት ከመሆኑ አንጻር፤ ክቡር አፈ ጉባኤያችን እያንቀላፋንም ቢሆን ፕሮጀክቶቻችንን እንፈጽማለን ሲሉ ከመናገራቸው አንጻር፤ ከልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አመክንዮ አንጻር ጉዳዩን ሰሞንኛ ከነበረው የዋና ኦዲተር ሪፖርት አኳያ ተነስቶ መፈተሽ ተገቢ ነው ። የዚህ ፅሁፍ አቢይ መነሻና መድረሻም ሪፖርቱን እና መንግስትን ከተያያዝነው የጸረ ድህነት ዘመቻ አኳያ ማሄስ ነው።

እንደፌደራሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት የያዩ ጉድ የሚጀምረው የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቻይና ኮምፕላንት ከተባለው የውጭ ድርጅት ከወሰደው ጥናት ጋር ባልተገናዘበ ወይም ሁለቱ ጥናቶች እንዲጣጣሙ ሣይደረግና በእርግጥም ይህ የሚቻል መሆኑ ሣይረጋገጥ ስራውን መውሰዱና እንዲጀምር ከተሰጠው የመንግስት ውሳኔ ነው።

ከዚህ የመነጨው መሰረታዊ ስህተት እስከ መጋቢት 2009 ዓ.ም ድረስ በሶስቱ ዩኒቶች ማለትም የዩሪያ የማዳበሪያ ዩኒት 28.05%፣ የተርማል ፓዎር ፕላንት 11% እና የድንጋይ ከሰል 3.05% አጠቃላይ አፈጻጸም 42.31% ለሆነ ዝቅተኛ አፈጻጸም ፕሮጀክቱን ዳርጎታል። እንግዲህን ችግሩ የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። ለዚህ የወረደ አፈጻጸም እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 21 ቀን 2016 ድረስ ከአጠቀላይ የፕሮጀክቱ የውል ዋጋ ብር 11,084,850,000.00 (አስራ አንድ ቢሊየን ሰማንያ አራት ሚሊየን አምስት መቶ ሺ) ብር ውስጥ ብር 5,653,273,500.00 ወይም የውሉ 60% ለሥራ ተቋራጩ  ተከፍሏል ይለናል የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት። የባሰው አደጋ ደግሞ ቀጥሎ ይመጣል። አፈጻጸሙ ዝቅተኛና በዕቅዱ መሰረት ያልተከናወነ ከመሆኑም በላይ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ኮርፖሬሽኑ ከባንክ ለተበደረው ብድር ወለድ እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም ድረስ ብቻ ብር 1,826,513,172.20 (አንድ ቢሊዮን ስምንት መቶ ሃያ ስድስት ሚሊየን አምስት መቶ አስራ ሶስት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ከሀያ ሳንቲም) የተከፈለ መሆኑና ፕሮጀክቱ በተራዘመ ቁጥር ምንም ገቢ ሳይመነጭ ለባንክ የሚከፈለው ወለድ በከፍተኛ መጠን ሊያድግና በፋብሪካው ዘላቂነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር መቻሉን የተመለከተው የዋና ኦዲተሩ አመክንዮአዊ ስጋት ነው ከባዱ አደጋ። ይህ በሚሆን ጊዜ ለአመቱ ከተያዘው ሃገራዊ በጀት እዳ መክፈል ግድ ይለናልና ስራ ፈጠራዎች ይቅሩና ሌሎቹንም ፕሮጀክቶች ውሃ ሊበላቸው ዘንድ ግድ ይለናል ማለት ነው።

በውሉ መሰረት የስራ ተቋራጩ ለእያንዳንዱ የፕሮጀክት ስራ የተተነተነ ዝርዝር የትግበራ መርሃ ግብር በወቅቱ እያወጣ ሊያቀርብና ተግባራዊ ሊደረግ ይገባ የነበረ መሆኑን የሚያወሳው የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት፤ ተቋራጩ ለሚያከናውነው ለእያንዳንዱ የፕሮጀክት ስራ የተተነተነ ዝርዝር ዕቅድ፣ የስራ ዓይነቶችን (activities)፤ እያንዳንዱን የስራ ዓይነት ከጠቅላላ የፕሮጀክት ስራ የሚይዘው ክብደት፤ የስራዎቹ የገንዘብ መጠን፤ ስራዎቹ የሚሰሩበት ጊዜ እና የስራዎቹን አፈጻጸም በጊዜ በመከፋፈል በጊዜ መርሃ ግብሩ መሰረት በሚፈለገው ደረጃ አጠቃሎ የማያቀርብ መሆኑ ለዚህና ግና ለሚከፋው የአደጋ ቀጠና ውስጥ የከተተን መሆኑን ያብራራል።

የማሽነሪዎች ዝግጅት በአገር ውስጥ በሚገኙት የሥራ ተቋራጩ እህት ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች አማካኝነት እየተዘጋጀ የሚገኝ ቢሆንም የሥራው አፈፃፀም ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ክንውን ጋር የማይጣጣምና የዘገየ መሆኑም ሌላውና ወደፊት የሚጠብቀን ተግዳሮት ነው። እንዲሁም የፕሮጀክቱ ወሳኝ ዕቃዎችን የግዢ፣ የማምረትና የማቅረብ ስራ በጣም የዘገየና በታቀደለት ጊዜ እየተከናወነ አለመሆኑ፣ በግንባታ ቅደም ተከተል መሰረት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ተለይተው ያልቀረቡ መሆኑ፤ ከዕቃዎች ምርት ጋር በተያያዘ ከውጭ አገር የሚመረቱ ዕቃዎች ውል በመፈጸም ስራ ያልተጀመረ መሆኑ፣ በመሬት ውስጥ የሚቀበሩ ቱቦዎችና መሳሪያዎች የማምረትና የመግዛት አቅርቦት የዘገየ መሆኑ እንዲሁም ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ምርት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም ሩብ ዓመት ያልተመረተና ልዩነት ያልታየበት መሆኑም ግና ዋጋ የሚያስከፍለን እንደሆነ በዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ተመልክቷል።

ምንም እንኳን እነኚህ ጉዳዮች በመጀመሪያው ጥናት ውስጥ መካተት ቢኖርባቸውም ተቋራጩ ተጨማሪ ስራዎችን ማለትም የድንጋይ ከሰልን በዓመት የማምረት አቅም ከ1.2 ወደ 1.8 ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድረግ፣ በፕሮጀክቱ ሳይት መቀያየር ምክንያት፣ ለፋብሪካው ለመጠጥ፣ ለፕሮሰስ፣ ለመሳሪያዎች ማቀዝቀዣ ለሚያስፈልግ የውሃ ግድብ ስራ፣ ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚጓጓዙ የማምረቻ መሳሪያዎች የሚከፈል የትራንስፖርት ወጪ፣ ለሰብስቴሽን ማቋቋሚያ ግንባታ ስራ እና የAsh & Slag Handling ስራ አመቺ በሆነ መልኩ ለመገንባት ተጨማሪ ብር 3,415,150,000 (ሶስት ቢሊዮን አራት መቶ አስራ አምስት ሚሊዮን አንድ መቶ ሀምሳ ሺ) የጠየቀ ቢሆንም ኦዲቱ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በፕሮጀክቱ ባለቤት ውሳኔ ያልተሰጠው መሆኑን የተመለከተው የዋና ኦዲተር ሪፖርት በአሸዋ ላይ ከተገነባው ድህነታችን ጋር ተያይዞ በጎርፍ ልንጠረግ መቃረባችንን ይጠቁማል።

ይህን ስልአጀንዳችን ማሳያ እንዲሆነን አነሳነው እንጂ ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት ሪፖርት የፋይናንስ ሕጋዊነትንና የክዋኔ ኦዲትን የተመለከቱና ከህልሞቻችን ጋር ተጻራሪ የሆኑ ግኝቶችንም አቅርበዋል፤ ጥቂቶቹን እንመልከት። የጥሬ ገንዘብ አያያዝና አጠባበቅን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብቻ 144ሺ 716 ብር ጥሬ ገንዘብ ጎድሎ ተገኝቷል፡፡ በሒሳብ መግለጫ ሪፖርት በተደረገውና በቆጠራ የተገኘው ጥሬ ገንዘብ መካከል በአምስት መሥሪያ ቤቶች ቆጠራ ከመዝገብ ጋር ሲነፃፀር 379.4 ሚሊዮን ብር ጉድለት መገኘቱም በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት ሪፖርት የስድስት መሥሪያ ቤቶች ሒሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ የተገኘው 284ሺ 971 ብር ብቻ ነበረ፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ 190/2002 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሒሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ፣ በ113 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 5.2 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ያልተወራረደ ሒሳብ ተገኝቷል፡፡

ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪዎች በገቢ ግብር፣ በቀረጥና ታክስ፣ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ ሕጎች ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ብቻ 1.13 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡

ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ደግሞ 4.1 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገቢ መኖሩን ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አረጋግጠዋል፡፡ ደንብና መመርያ ያልተከተሉ 91 መሥሪያ ቤቶች 98.7 ሚሊዮን ብር ከፍለው መገኘታቸው፤ የግዥ አዋጅ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዥዎችን በተመለከተ በ79 መሥሪያ ቤቶች 324.9 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ ግዥ መፈፀማቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበ 36 ሚሊዮን ብር፣ የማማከር ፈቃድ ሳይኖር ያላግባብ ተረጋግጦ የተፈጸመ 260.9 ሚሊዮን ብር የግንባታ ክፍያ መኖሩም በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን፤ ሪፖርቱን ያዳመጠው ፓርላማም ለመጨረሻ ጊዜ ወደ እንቅስቃሴ እንደሚገባ፣ የወንጀል ይዘት የታየባቸው የኦዲት ግኝቶችም ወደ ዋና ዓቃቤ ሕግ እንዲላክ ወስኗል፡፡ (ግን ደግሞ አምናና ካቻምናም ተመሳሳይ ውሳኔዎች የተሰጡ ቢሆንም ምንም ባለመፈጠሩ የአሁኑ ብሶ መገኘቱ ባይገርምም ያሳስባል።) ከናዳ ለማምለጥ በሚያስችል ፍጥነት መሮጥ በሚጠበቅባት ሃገር ይህ መሆኑ ከማንቀላፋትም በላይ ነውና ጉዳዩ ሁላችንንም ያሳስበናል።

ነገሩ ከማንቀላፋትም በላይ ለመሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ከዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ላይ ወስደን እንመልከት። በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳዳር ደንብ ቁጥር 190/2002 ከአንቀጽ 32 እስከ 35 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ113 መ/ቤቶችና በ28 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 5ቢሊዮን 262ሚሊዮን 275ሺ 550.73 በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ብር 375ሚሊዮን 557ሺ 284.38 በ6 መ/ቤቶች እና 6 ቅ/ጽ/ቤቶች ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተመዘገበ፤ ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ሊቀርብለት ያልቻለ ሂሳብ በመሆኑ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ ተሰብሳቢ ሂሳብ ተገኝቷል፡፡

በወቅቱ ያልተወራረደው ተሰብሳቢ ሂሳቡ በዕድሜ ወይም በቆይታ ጊዜው ሲተነተን፤ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ብር 134ሚሊዮን 153ሺ 964.72፤ ከአንድ ዓመት በላይ እስከ አምስት ዓመት ብር 3ቢሊዮን 174ሚሊዮን 764ሺ 464.42፤ ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አሥር ዓመት ብር 372ሚሊዮን 936ሺ 870.76 እና ከአሥር ዓመት በላይ ብር 196ሚሊዮን 565ሺ 227.12 ሲሆን፤ ቀሪው ሂሳብ ብር 1ቢሊዮን 442ሚሊዮን 465ሺ 210.85 የቆይታ ጊዜው በግልጽ ለመለየት አልተቻለም፡፡ ከዚህ በላይ ከናዳ ለማምለጥ በማያስችል ሁኔታ ውስጥ መገኘታችንን የሚያመላክት ማሳያ ከቶ ከወዴት ይገኛል?

በእርግጥ የዋና ኦዲተሩ የክዋኔ ሪፖርት የፓርላማ አባላቱን ጭምር ያስደነገጣቸው መሆኑ አንድ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች ቢኖሩም፤ ከዚህ በኋላ በዚህ መንገድ መቀጠል የማይቻል መሆኑን የተገነዘበው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የማያዳግም እርምጃን ናዳው ይፈነክተናል፤ ከዛ የተረፍንም ያለነው አሸዋ ላይ ነውና በጎርፉ የምንወሰድ መሆኑ አያጠያይቅም።  

የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተሰጠውን ተልዕኮ የሚፈጽም የፓርላማው ቀኝ እጅ እንደሆነ ከመሰከሩት የፓርላማ አባላት መካከል አንደኛዋ፤ ዋና ኦዲተሩ የሚያቀርቡትን ሪፖርት እንደ መረጃ ወስዶ በአስፈጻሚው አካል ላይ ዕርምጃ በመውሰድ፣ የሕዝብ ሀብትና ንብረትን ከብክነት ማዳን አለመቻሉን በቁጭት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ክቡር አፈ ጉባዔ ይህ ጨዋታ ማብቃት አለበት፤›› ሲሉ በአፅንኦት የገለጹት እኚህ አባል ‹‹ዋና ኦዲተር ሥራውን በድፍረትና በልዩ ሁኔታ ሲሠራ እኛ ሥራችንን እየሠራን አይደለንም፡፡ የሚመለከተውን አካል ተጠያቂ ማድረግ አለብን፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባዔ ሕዝብ ይጠይቀናል፤›› ሲሉ ማሳሰባቸውም የጉዳዩን የአደጋ ጥልቀት የሚያመላክት ነው፡፡

ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ነፃነቱን ጠብቆ እንደሠራ ማረጋገጥ የሚቻለው ሪፖርቱ በድፍረት ባስቀመጣቸው ግኝቶች መሆኑን የተናገሩት ሌላኛው የህዝብ ተወካይ ደግሞ፤ በየዓመቱ ደንብና መመርያ የማያከብር፣ የግዥ ሥርዓት የማይከተል ባለሥልጣን ‹‹ማነው የሚቀጣኝ እያለ ነው?›› በማለት የህዝብ ሃብት በምን ያህል ስፋት እየባከነ መሆኑ ያሳደረባቸውን ስጋት አመላክተዋል፡፡ ‹‹በየዓመቱ ተመሳሳይ ነገር እየደገምን መሄድ የለብንም›› ያሉት እኚህ ተወካይ ‹‹ዕርምጃ መውሰድ መጀመር አለብን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ሌላኛው አስተያየት ሰጪም በተመሳሳይ ባነሱት ሐሳብ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕርምጃ ለመውሰድ ቃል የገቡ በመሆኑ በ2010 ዓ.ም. ዕርምጃ ተወስዶ ፓርላማው ሪፖርት ሊቀርብለት ይገባል” ያሉ ሲሆን፤‹‹ዋና ዓቃቤ ሕጉ የፓርላማ አባል በመሆናቸውና አሁንም በመሀላችን የሚገኙ ስለሆነ፣ ለጉዳዩ አፅንኦት እንደሚሰጡት እምነቴ ነው›› ሲሉም ተስፋቸውን ዋና አቃቤ ህግ ላይ ጥለዋል፡፡

ባጠቃላይ፣ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መርሆ ሰፋፊና ግዙፍ  በሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች የግል ባለሃብቱ እጅ ስለሚያጥረው መንግስት ተሳታፊ መሆኑ አይቀሬ ነው። በመርሁ አግባብ ታዲያ እዚህ ጋር የህዝብ ሃብት ለምዝበራ ተጋላጭ መሆኑ ይታወቃልና የተጠናከረ የቁጥጥርና የክትትል ስራ የመንግስት ቁልፉ ተግባር ሊሆን ይገባዋል። ከላይ የተመለከተው የዋና ኦዲተሩ ግኝት ደግሞ ከናዳ ለማምለጥ በሚያስችል አግባብ መሮጥ ግድ የሚላት ሃገር የሚጠበቅ ሳይሆን ለዓመታት በተኙ ሃገራት ነው። ስለሆነም የድህነታችንን ልክ አንቀላፍተን የምንቋቋመው ሳይሆን ከናዳው ለማምለጥ ከሚያስችል አግባብም ከፍ ባለ ደረጃ መሆኑን አውቀን ከላይ ለተመለከተው ብክነት የዳረጉን ሃይሎች ላይ ሁሉ እርምጃ መውሰድና ለህዝብ ይፋ በማድረግ ትክክለኛ ወደሆነው መስመር መግባት ይጠበቅብናል።