የሞምባሳ-ናይሮቢ ፈጣን የባቡር መንገድ ክፍለ አህጉሩን ለማስተሳሰር ሚና አለው-ሩዋንዳ

አዲሱ የኬንያው  ሞምባሳ-ናይሮቢ  ፈጣን የባቡር መንገድ ምስራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር የላቀ ሚና እንደሚኖረው ሩዋንዳ ገለጸች

በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የኬንያው ሞምባሳ-ናይሮቢ ፈጣን የባቡር መስመር ምስራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ያሉት የሩዋንዳው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስተር ክላቨር ጋቴቴ ናቸው፡፡

ጋቴቴ ኪጋሊ በሚገኘው ቢሯቸው ውስጥ ለሺኖዋ በሠጡት መግለጫ “በጣም ስኬታማ ፕሮጀክት ነበር፣ ለዚህ ስኬት ደግሞ የቻይና መንግስት ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷልና ልናመሰግነው ይገባል” ብለዋል፡፡

የባቡር መንገዱ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የቻይናው ፕሬዚደንት ልዩ መልዕክተኛ ዋንግ ዮንግ በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

“በእውነቱ ኬንያ ያሳካችው ሁላችንም ሊያኮራን ይገባል፣ የቀጣናው ሃገራትም በጋራ ተጠቃሚ በምንሆንበት መንገድ ዙሪያ ጠንክረን አየሰራን ነው” ብለዋል ጋቴቴ፡፡

480 ኪሎሜትር የሚሸፍነውና 3.8 ቢሊዮን ዶላር የፈሰሰበት የሞምባሳ-ናይሮቢ ፈጣን የባቡር መንገድ በቻይናው የመንገድና ድልድይ ኮርፖሬሽን ሲሆን 90 በመቶ ወጪው በቻይና የተሸፈነ ነው፡፡

እንደ ጋቴቴ ገለጻ ምስራቅ አፍሪካን ለማዋኸድ ሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በቀጣይም የሩዋንዳ መዲና ኪጋሊን ከሞምባሳ ጋር በባቡር መስመር በማገናኘት 21 ቀን ይወስድ የነበረውን መንገድ ወደ 5 ቀን ማሳጠር እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ህዝቦች በነጻነት ካንዱ ሃገር ወደ ሌላው እንዲዘዋወሩና የሥራ እድሎችን እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራትን ለማከናወንም አጋዥ ነው ብለዋል ጋቴቴ፡፡ 

ሚኒስትሩ አያይዘውም ሃገራቸው ሩዋንዳ ከቻይና ጋር በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት እንዳላትም ገልጸዋል፡፡ 

“ከቻይና ጋር በልማት እና ቴክኒካል ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እየሰራን ነው፡፡ በዚህም ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡ 

በአለም አቀፍ የትብብር ደረጃ ካየነው በእኛና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ለተቀረው አለም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነውም ብለዋል ጋቴቴ፡፡

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በቤጂንግ ተገናኝተው የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነታቸውን ለማሳዳግ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

ባለፉት አስርት አመታት ሩዋንዳ በአማካይ የ8 በመቶ እድገት አስመዝግባለች፡፡

በፈረንጆቹ 1995 ዓም 79 በመቶ የነበረውን የድህነት መጠን እኤአ በ2014 ወደ 39 በመቶ እንዲወርድ ማድረግም ችላለች፡፡    

ሃገሪቱ ላስመዘገበችው ስኬት የካጋሜ አመራር የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድም ጋቴቴ ጠቁመዋል፡፡     

ሩዋንዳ ከሙስና የፀዳ መንግስት ካሏቸው ሃገራት ተርታ ትመደባለች፡፡