የስኬቶቻች መሠረት ህገመንግሥታችን ነው

ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሰረት ያደረገ  ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግስት  መገንባት በመቻሏ ዘላቂነት ያለው  ሰላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ በተለይ በቀንዱ አካባቢ እንዲሰፍን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች። ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና ተጫውታለች፤ በመጫወትምላይ ነች። የቀድሞው አምባገነንና አህዳዊ ስርዓት ተደምስሶ ያልተማከለና የህዝቦች  ዴሞክራሲያዊና ሰባዊ መብቶችን የሚያከብር ህገመንግስታዊ ስርዓት ከተቋቋመ ጀምሮ  ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን ዓቀፍ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ነች። በተለይ ባለፉት 14 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነች።

አገራችን ትላንት ትታወቅበት የነበረው ረሃብና ጦርነት ዛሬ የለም። በሃምሳ ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታቅ ድርቅ አገራችንን ለተከታታይ ሁለት ዓመት  ቢመታትም ወደ ረሃብ እንዳይቀየር ዜጎች ከአካባቢያቸው እንዳይፈናቀሉ ማድረግ ተችሏል። አሁን ላይ የአገራችን ገጽታ እጅጉን ተሻሽሏል። ህዝቦች ተፈቃቅደው፣ ተቻችለውና ተሳስበው አንዲት ጠንካራ  ህገመንግስታዊ አገርን መመስረት ችለዋል።

እንደእኔ ለኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት መከተል ብቸኛና ትክክለኛ ምርጫ ይመስለኛል። የፌዴራል ስርዓታችን ምንም እንከን የለበትም ባይባልም መሰረታዊ የአገራችንን ችግሮች መፍታት አስችሏል። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ  ማግኘት የቻሉት ቋንቋን መሰረት ባደረገው የፌዴራል ስርዓት ሳቢያ ነው። ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እንዲዳኙ፣ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ፌዴራሊዝም ስርዓቱ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይህ ስርዓት  በህዝቦች መካከል መተማመን፣ መቻቻልና መከባበር  እንዲጎለብት በማድረጉ የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ሆኗል።

አገራችን በተከተለችው የፌዴራል ስርዓት  በሰፈነው ዘላቂነት  ያለው ሰላም  ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ዓለምን ያስደመመ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ ከመቻሏ በተጨማሪ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችንም ማረጋገጥ ተችሏል። ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ  በአፍሪካ ሆነ  በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ እያደገ የመጣው በአገር ውስጥ እያስመዘገበቻቸው ካሉ ስኬቶች ነው።  

አገራችን በተባበሩት መንግስታት ያላት ተሰሚነትም ሆነ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም የመነጨው ከትክክለኛው የውጭ ግንኙነት ፓሊሲያችን ነው። ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመትና ዘንድሮ አገራችን በተባበሩት መንግስታት ሁለት ትላልቅ ስኬቶችን አስመዝግባለች። የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆንና የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኗ መመረጧ የዲፕሎማሲ ስኬታችን ውጤት ነው።    

አገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ዋንኛው  ስኬት ተደርጎ የሚወሰደው  በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ለውጥ ነው። መንግስት የተከተለው  ግብርና መር የኢኮኖሚ  ቀመር አገራችንን በስኬት ላይ ስኬት እንድትረማመድ አድርጓታል። አሁን ላይ ደግሞ ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያደርግ  መንግስት በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው። መንግስት  13 ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና 17 የግብርና ውጤቶችን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን   በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዋች በመገንባት ላይ ነው። የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማጠናከር በርካታ  የሃይል ማመንጫ ግድቦችን በመገንባት ላይ ነች።
ኢትዮጵያ አህጉሩን እየመራች ያለችው  በኤኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ይታይ የነበረውን ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ መፍትሄ በማፈላለግ ጭምር ነው። ኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ በፀረ ሽብር ትግሉ  አጋር ነች። በሶማሊያ ያለው የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው ጽንፈኛ አልሸባብ በአካባቢው አገሮች እያደረሰ የነበረውን ጥፋት በመመከተ ረገድ አገራችን እያሳየች ያለውን ጥረትና እየመጣ የለው ለውጥ  የሚደነቅ ነው። ለአልሸባብ መዳከም  የኢትዮጵያ ጥረት ወሳኝ ነው። በደቡብ ሱዳን ላለው ቀውስ መወገድ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና በመጣወት ላይ ነች።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት የጎረቤት አገሮችም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከ850 ሺህ በላይ ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን  ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጭምር ሙገሳን ተችሯታል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያላቸውን ውሱን ሃብት ለእንግዶች በማካፈል አፍሪካዊ አጋርነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ ስናስታውስ የአገራችን እንኳን ለሌሎች አገር ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦች በጦርነትና በረሃብ ሳቢያ የትውልድ ቀያቸውን  ጥለው የሚሰደዱባት ነበረች።  አሁን ላይ ሁኔታዎች ተለውጠዋል።  ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ህዝቦች  መጠጊያ መሸሺያ ሆናለች።  ከ850 ሺህ በላይ ስደተኞችን ማስጠለል የሚፈጥረው ማህበራዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከባድ ቢሆንም አገራችን አቅም በፈቀደ ሁሉ ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው እያደረገች ትገኛለች። በተግባር የተረጋገጠ ህዝባዊነት ይህ ነው።

ከጸጥታ ጉዳዮች ባኛገር አገራችን ከጎረቤት አገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲጎለብት በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነች። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል  የንግድና የባህል ግንኙነቱ እንዲጠናከር ትልቅ ጥረት በማድረግ ላይ ነች። በቀንዱ አካባቢ ያሉ አገራት ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት  አሁን ላይ የአንዳቸው ስኬትም ሆነ ውድት ለጎረቤቶቻቸው የሚተርፍ መሆኑን በመረዳታቸው ትስስሩና መረዳዳቱ  እየጠነከረ መጥቷል።

ለአብነት ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጠነከረ ግንኙነት መመስረት በመቻላቸው ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና  ማህበራዊ ጉዳዮች ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር ችለዋል። ጅቡቲ  የባህር በሯን ለኢትዮጵያ  በማከራየት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለጅቡቲ  በማቅረብ ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ችላለች። ሁለቱ አገራት የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት የህዝቦች ግንኙነትን በማጠናከር ላይ ናቸው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ  ከኬንያ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን  የሚያገናኙ ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ በአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣  የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ በማካሄድ ላይ ነች። ጅቡቲና አዲስ አበባን የሚያገናኝ በአፍሪካ  በዘመናዊነቱ የሚጠቀስ የኤሌክትሪካ የባቡርም የግንኙነት ምዕራፉን ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያሳድገው መገመት አይከብድም።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብም በቀንዱ አካባቢ  የሃይል አቅርቦት ትስስሩን ያጠናክረዋል።  ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መሰረት ስትጥል አገሪቱ ያለባትን ከፍተኛ የኃይይ አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እንዲቻል እንዲሁም በተመጣጣኝ ክፍያ ለጎረቤት አገሮች ኃይል በማቅረብ የቀንዱ አካባቢ  አገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ ከየትኛውም የጎረቤት አገራት የተሻለ የሃይል ማመንጨት አቅም እንዳላት ይታወቃል። ይህን ሃብት በመጠቀም የአካባቢው አገራትን በኢኮኖሚያዊ ጠቅም ለማስተሳሰር እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ የአካባቢው አገሮች ሰላም ዘለቄታዊነት እንዲኖረው በምጣኔ ሀብት ጥቅም እንዲተሳሰሩ እያደረገች ያለው ጥረት ስኬት እየታየበት ነው።   

በሰላም ማስከበር ረገድም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትልቅ አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ነች።  በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ አብዬ የሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ  ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊቷን በማዋጣት  ለየአካባቢዎቹ ሰላም መስፈን የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ነች።

ኢትዮጵያዊያን ሰላም አስከባሪ ኃይሎችም በተሰማሩበት አገር ሁሉ በህዝብ የተወደዱና ምስጋና የተቸራቸው ናቸው። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት ከአገራችን ህገመንግስት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። በመሆኑም ህገመንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።