የፀረ ሙስና ትግሉ በተጠናከረ የህዝብ ተሳትፎ ውጤታማ ይሆናል

ኢህአዴግም ሆነ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ባሳለፉት 26 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከገጠሙን ከባድ ፈተናዎች ሁሉ አንዱ የሆነው ፈተና የሚመነጨው መንግስታዊ ስልጣን በእጃችን ከመግባቱ ጋር ተያይዞ ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል፤ በተለያዩ ድርጅታዊና መንግስታዊ ሰነዶቻቸውም ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይህን ሲሉም እንደኛ በመሰሉ ያልበለፀጉ አገሮች ትክክለኛው የሀብት መፍጠሪያና የብልፅግና መንገድ እጅግ ጠባብ በመሆኑ የመንግስት ስልጣንን መያዝ በአቋራጭ ለመክበር እጅግ የተመቸ ሆኖ የመገኘቱን የፖለቲካዊ ሳይንስ አመክንዮ በመጥቀስ ነው፡፡ በእርግጥም በአፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ማክተም በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት አፍሪካውያን መሪዎች ይህን ስልጣን ዋነኛ የመክበሪያ መንገድ እንዳደረጉት በብዙ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ነው፡፡ መሪዎቹ በአንዳች አጋጣሚ በእጃቸው ያስገቡትን ስልጣን ኪራይ ለመሰብሰብ ስለተጠቀሙበት አገራቸውን አዲስ ሀብት ከመፍጠር ጎዳና አውጥተው አስቀድሞ የተፈጠረችውን ትንሽ ሀብት በመቀራመት ድህነትን የሚያባብሱ ሆነው መገኘታቸውም በተለያዩ አግባቦች ተረጋግጧል፡፡

ይህን አደገኛ አካሄድ ገና ከጠዋቱ የተገነዘበው መሪ ድርጅቱና መንግስት “መንግስታዊ ስልጣንን የጥቂቶች መክበሪያ ወይስ የብዙኀን መጠቀሚያ ማድረግ ይገባል” በሚለው ጉዳይ ላይ ግልፅና የማያሻማ አቋም በመያዝ ስራውን ስለመጀመሩም በተለያዩ ድርሳናቱ ይተርካል። ስለሆነም መንግስታዊ ስልጣን እጅግ ከፍተኛ አቅም በመሆኑ፣ ይህንኑ የጥቂቶችን ሳይሆን የብዙኀንን ብልፅግናና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መጠቀም ከተቻለ፣ ያለማቋረጥ ማደግና መመንደግ እንደሚቻል፣ በአንፃሩ ይህን ስልጣን የጥቂቶች መክበሪያና መጠቃቀሚያ አድርጎ በመቀጠል ጥፋትና ውድመት እንደሚያስከትል ከድርጅቱም ሆነ ከመንግስት አስቀድሞም የተሰወረ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡  

ሌላው ስለመንግስትም ሆነ መሪ ድርጅቱ ጉዳዩን የተመለከተ ግንዛቤ ማረጋገጫና ማሳያ ሊሆን የሚችለው ጉዳይ ድርጅቱም ሆነ መንግስት ባለፉት 26 ዓመታት በመንግስት  ስልጣን ራሳቸውን ለመጥቀም የሚሽቀዳደሙ ሰዎች ሳይሆን የህዝባቸውን ልማታዊ አቅም ለማሳደግ አስቻይ ሁኔታ የመፍጠር ቅኝት ያላቸው ሰዎችን ለመፍጠርና ለማበራከት የመረባረቡ እውነታ ነው፡፡  

 

ያም ሆኖ ግን አሁንም በየደረጃው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ህዝባዊና አገራዊ ሃላፊነታቸውን በመዘንጋት፣ በያዙት ስልጣን የራሳቸውን ጥቅም ሲያስቀድሙ እየታየ እና እየተረጋገጠ ነው፡፡  ይህ የሆነው ደግሞ ይህንኑ የመንግስት ስልጣን አገር የመገንቢያ መሳሪያ የማድረግና ያለማድረግ፤ በዚህ መሳሪያ ጥቂቶችን ወይም ብዙኀንን ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎትና ቁርጠኝነት የመኖር ወይም ያለመኖር አቅጣጫዎች ያስከተሉት ልዩነት ነው፡፡ ይህም ሆኖ መሪ ድርጅቱ መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው ግዙፉን የመንግስት ሃይል በተለምዶ ከሚታወቅበት የዘራፊነት ባህሪው በማላቀቅ ወደ ልማት ሃይልነት መቀየር በመጀመሩ ያለፉትን 26 ዓመታት ሂደትና የተገኘውን መልካም ውጤት የወሰነ ሌላ ቁልፍ ጉዳይ የነበረ መሆኑም ጉዳዩን ጉራማይሌ ያደርገዋል፡፡

በጥቅሉ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የተሃድሶ መስመሩ የህዝብ መስመር ሆኖ፣ ይህን መስመር በሚያቀነቅን ፓርቲና መንግስት እየተመራ አስገራሚ የሚባል ለውጥ እየተመዘገበ ቢመጣም፣ በመስመሩ ሰነዶች ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የመስመሩ ዋንኛ አደጋ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አለመደፈቁ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት በአጭሩ ያለአግባብ የመጠቀም አመለካከትና ተግባር ነው፤ በአቋራጭ የመክበር። አስተሳሰቡና ተግባሩም በግለሰብም ሆነ በቡድን የሚንፀባረቅ ነው። ህግና ስርአትን ተከትሎ ሰርቶ ከመበልፀግ ይልቅ ህግና ስርአትን በመናድ ጥቅሞችን እያግበሰበሰ፣  የአቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም ህገ-ወጥነትን ያነግሳል። በሂደትም ዜጎች በስርአቱ ላይ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል። ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይልቅ የአንድ ወገን ተጠቃሚነትን ያጎለብታል። ይህም  ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ስርአተ አልበኝነትን በማስፈን በስርአቱ ውስጥ ትናንሽ መንግስታትን ለመፍጠር ይሞክራል። ኪራይ ሰብሳቢነት የስርአቱ አደጋ ነው የሚባለውም ስለዚህ ነው። 

የህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆዎች በተመለከተበት የህገ መንግስታችን ምእራፍ 2 አንቀጽ 12 የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ለሕዝብ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝቡም በማንኛውም ተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ በማንኛውም ጊዜ ሊያነሳው መብት እንዳለውና የዚህ ሁሉ መነሻው በዚሁ ምእራፍ አንቀጽ 8 የተመለከተው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶች ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ መሆኑ አያጠያይቅም።  ይህ የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም የማዋል ፈተና ከባድ የሆነበት ስርአተ መንግስት ከቀደሙት ሕገ-መንግስታት በተለየ ሁኔታ ስልጣን የሚመነጨውም ሆነ ጥቅም ላይ የሚውለው ከህዝብና ለህዝብ መሆኑንና ማንኛውም ባለስልጣን ከህዝብ በታች እና በህግም ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ የሚያረጋግጥ ህገ መንግስታዊ ስርአት ባለቤት መሆኑ በራሱ ምናልባት ተስፋ አያስቆርጥ ይሆን እንጂ በዚህ አይነት ወርቃማ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችም ውስጥ ተሁኖ መንግስታዊ ስልጣንን ከለላ ያደረገው ዘረፋ እየከበደ ስለመሄዱ ሰሞኑን በሚገባ ተመልክተነዋል።

 

ስለሆነም ይህን ፈተና ለማለፍ በዋናነት ሊያዝ የሚገባው ነጥብ ተጠያቂነትና የሕዝብ አሳታፊነትን እንደምታና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተመለከተው ጉዳይ ነው። በጥልቅ ተሃድሶው መጀመሪያ ላይ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን አስመልክቶ የያዘው አቋም በሕዝብ ተሳትፎ አመለካከትን መቀየር የሚለው አጀንዳ የሆነበት ምክንያትም ስለዚህ ነው። አሁን የተያያዝነውን የጸረ ሙስና ዘመቻ ተከትሎ ግለሰቦችን በመቀየር ወይም በማሰር  ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ይቻላል የሚል አስተሳሰብ እንደ አቋም ከተያዘ ጦሱ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። 

 

ከሰሞኑ ዘመቻ ጋር ተያይዞ የዘመቻው ዋና አካል እንዲሆኑ የሚጠበቁ አብዛኞቹ ወገኖች የተጠያቂነት አሰራር ግለሰቦችን በማሠር ተጀምሮ በማሠር የሚጠናቀቅ ተግባር አድርገው እየተመለከቱት ነው። ይልቁንም  አንዳንዶች ደግሞ በዘመቻው በታሰሩ ሰዎች  የመደሰት ወይም ተጠርጣሪዎች እንዲያዝኑ በማድረግ  ለመርካት የሚሞክሩበትና ከመሰረታዊ ግቡ የተፋለሱበት አካሄድም እየተስተዋለ ነው። በዚህ ዘመቻ ላይ ህብረተሰቡ ሊይዘው የሚገባው ዋናው ጉዳይ የተያዙት ተጠርጣሪዎች መጠየቅ ያለባቸው ናቸው ወይስ አይደሉም ከሚለው ይልቅ ትላልቅ ባለስልጣናት ናቸው ወይስ አይደሉም የሚል እና፤ በተመሳሳይም የተጠረጠሩበት ገንዘብ ትንሽ ነው፣ ትልቅ ነው፤ የታሳሪዎቹም ብዛት ትንሽ ነው፣ ብዙ ነው፤ ወደሚል አቅጣጫ ያዘነበሉ አስተያየቶችን በስፋት እየሰማን መሆኑ ከግቡ ጋር እንዳንጋጭ ያሰጋል። ከዚህ ይልቅ አገር የምታድገው የአሳታፊነትና የተጠያቂነት አሠራር ሲሰፍን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ትግል ማድረግ ነው የሚገባው። ሙስና በተመዘበረው የገንዘብ መጠን የሚለካ ቢሆንም ዋነኛው አደጋ የሚከሰትበት አግባብ እና ዘርፍ መሆኑንም ማጤንና በዚያው ቅኝት የትግሉ አካል መሆን ያስፈልጋል።

 

ሰሞኑን የተጀመረውን በሙስና ተግባር ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን፣ ሰጪዎችንም፣ ተቀባዮችንም፣ አገናኞችንም በቁጥጥር ስር ማዋልና ለህግ ማቅረብ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባራት ወይም የአሠራር ችግሮችን ከመፍታት አንፃር እንደ አንድ የማስተካከያ እርምጃ ብቻ የሚታይ  እንጂ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ በዚህ መንገድ የማይመጣ የመሆኑን እውነታም መቀበል ግድ ይላል። የፀረ – ኪራይ ሰብሳቢ ትግሉ ስኬት የሚሆነው ምን ያህል ሕዝብን አሳትፏል፣ ህዝቡስ ምን ያህል ከመንግሥት ጎን ቆሞ ትግሉን ተቀላቅሏል፤ የሚለው መሰረታዊ  ጉዳይ ነው።  ይህም ከአመለካከት ለውጥ ውጪ ሊመጣ እንደማይችል ማጤን የሚገባ ሲሆን ከሁሉ በላይ ግን የህዝብ የባለቤትነት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

 

ስለዚህ አጀንዳ ሁነኛ የሆነ አስረጅ መጥቀስ እንችላለን። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመቆጣጠር መንግሥት ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ በርከት ያሉ ተመሳሳይ እርምጃዎች መውሰዱ ይታወቃል፡፡ ስርዓቱ ከላይ በተመለከተው አግባብ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የተጋረጠበት እንደሆነ በመገንዘብ ከመጀመሪያው ዙር ተሃድሶጀምሮ ለአስራ አምስት አመታት ያህል በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ማለፉም ይታወቃል፡፡ ይህ መሰረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያመቹ አረንቋዎች ጨርሶ አልተወገዱም፡፡ በተጨማሪም በነባራዊው ሂደትና ራሳቸው ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች በሚፈጥሯቸው ቀዳዳዎች የተነሳ ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢ አዝማሚያና ተግባራት መበራከት ለም አፈር ሆነው የሚያገለግሉ ችግሮች እየበዙ እንጂ ሲቀንሱ አይስተዋሉም። በዚህ የተነሳ ትላንት ከትላንት ወዲያ ከነበረውም በላይ በፋይናንስ አቅሙና በጥገኛ መረቡ የጠነከረ ኪራይ ሰብሳቢነት አሁንም የስርዓቱ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ብቻ ሳይሆን ስርዓቱንመ በመፈታተን ላይ ያለ ይገኛል፡፡

 

በሁለተኛው ዙር የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ላይ ይፋ እንደሆነው ስርዓቱን የሚፈታተነው ኪራይ ሰብሳቢነት እንደአመቺነቱ በልዩ ልዩ መልኮች የሚከሰት ነው፡፡ አንዳንዴ በግብር ስወራ፣ ሌላ ጊዜ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሞኖፖል አቅጣጫን ተከትሎ ሸማቹን በመዝረፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ መሬት በማግበስበስ ይከሰታል፡፡ ወይም ደግሞ የመንግስትን ፕሮጀክቶች ባልተገባ የጥገኛ መረብ ታግዞ ማግኘትና ጥራቱ የተጓደለ የፕሮጀክት አፈፃፀም በማሳየት ከህጋዊው በጀት በላይ ከመንግስት ገንዘብ በመውሰድና በመሳሰሉት መልክም የሚገለጽ እንደሆነ ሰሞንኛ ከነበሩት ተጠርጣሪ ባለስልጣናቱ እና ደላሎቹ መገንዘብ ችለናል፡፡

 

ጉዳዩ ሲፈተሽ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ትግሉ ሲዳከም ዝንባሌው እየሰፋ፣ ከላይ በተመለከተው አመለካከትን በመቀየር ቅኝት፤ ትግሉ ሲጠናከር ደግሞ ዝንባሌው እየቀነሰ የሚታይበትን ሁኔታ አይተናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለተወሰኑ ዓመታት በትግሉ ውስጥ በታየው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል አንፃራዊ መዳከም ምክንያት ዝንባሌው ተጠናክሮ በብዙ መስኮች ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም በተመሳሳይ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ስለሆነም በተጠናከረ የህዝብ ተሳትፎ ዝንባሌው እንደገና በቁጥጥር ስር የሚውልበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ ይህ ሰሞኑን የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ ዳር እንዲደርስ ምክንያታዊ የሆነና መረጃን መሰረት ያደረገ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም፡፡