አሜሪካ በቬኑዝዌላ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች

አሜሪካ የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮና ምክትላቸውን ጨምሮ በ15 የተለያዩ የቬንዙዌላ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች፡፡

የፕሬዚዳንት ማዱሮ አስተዳደር ቬንዙዌላን ወደ ሁከትና ብጥብጥ መርቷል በማለት ነው ዋሽንግተን ማዕቀቡን የጣለችው፡፡

በማዕቀቡ ፕሬዚዳንት ማዱሮና ሌሎች ባለስልጣናት በአሜሪካ ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስና የተወሰኑት ባለስልጣናትም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡

ማዕቀቡን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ማዱሮ ዕገዳው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለእኔ ያላቸውን ጥላቻ ከመግለፅ ያለፈ ፋይዳ የለውም ብለው ነበር፡፡

አሁን ደግሞ ዋሽንግተን ከማዱሮ ጋር ግንኙነት አላቸው በምትላቸው የቬንዙዌላ ባለስልጣናት ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጀች መሆኑ ነው የተሰማው፡፡

በማዕቀቡ ውስጥ የሚወድቁ ባለስልጣናት ሀብታቸውን ከማንቀሳቀስ ከማገድ በተጨማሪ አሜሪካውያን አብረዋቸው እንዲሰሩ አይፈቀድላቸውም፡፡

በአዲሱ ማዕቀብ የሚካተቱት የቬንዙዌላ ባለስልጣናት ማንነት ለጊዜው ግልፅ አለመደረጉን ሮይተርስ ሁለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ማዱሮ ባካሄዱት የብሔራዊ ሸንጎ ምርጫ ካለፉት አባላት ጋር ባለፈው አርብ በቀጣዩ ሂደት ዙርያ መምከራቸውን ተከትሎ አሜሪካ ማዕቀቡን ለመጣል መወሰኗ ነው የተነገረው፡፡

ብሔራዊ ሸንጎው ለፕሬዚዳንት ማዱሮ ተጨማሪ የሥልጣን ዕድሜን በሚያራዝም መልኩ ህገ መንግስቱን ዳግም ለመከለስ እየተዘጋጀ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረትና በቬንዙዌላ ጎረቤት አገራት ሳይቀር የተተቸው የቬንዙዌላ የብሔራዊ ሸንጎ ምርጫ አሁንም በአገሪቱ ውጥረቱ ነግሶ እንዲቀጥል ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ እንዳላመጣ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

በተያያዘ ዜና የመረጃ መረብ በርባሪዎች የፕሬዚዳንት ማዱሮ አስተዳደር ድረ ገፅ ላይ ያነጣጠረ የመረጃ መረብ ጥቃት ማድረሳቸው ተሰምቷል፡፡

ራሳቸውን ዘ ቢናሪ ጋርዲያንስ እያሉ የሚጠሩት መረጃ በርባሪዎቹ ጥቃቱን ለማድረስ የተነሳሱት ለፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች ያላቸውን ድጋፍ ለማንፀባረቅ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በቬንዙዌላ በተነሳ ሁከትና ብጥብጥ ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡

በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር 2017 የተጀመረው ተቃውሞ በተፈጥሮ ነዳጅ ሃብት የታደለችውን የቬንዙዌላን ኢኮኖሚ እያደቀቀው ይገኛል፡፡ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት በ700 በመቶ መናሩም ነው የተመለከተው፡፡