ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃገራችንን ከድህነት የሚያወጣ፣ የአፍሪካ ቀንድ አገራትንም የሚጠቅም ነው

እስካሁን ድረስ ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የተነገረለት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አሁን 60 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱ ተረጋግጧል። ይህ የተገለጸው ባሳለፍነው ሳምንት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ  ምክር ቤት ዘጠነኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ነው። ይህን ያረጋገጡት ደግሞ የብሔራዊ ምክር ቤቱ  ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን  ጨምሮ የምክር ቤቱ አባልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል  ናቸው። በጉባኤው ላይ ተገኝተው የነበሩት የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለም ግድቡ በአሁኑ ወቅት በጥሩ የግንባታ ሒደት ላይ የሚገኝ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ትርክትም የብሄራዊ ምክር ቤቱን አጠቃላይ ሪፖርት መነሻና አስረጅ አድርጎ ፕሮጀክቱ ባሳለፍናቸው 6 የግንባታ አመታት ውስጥ የፈጠራቸውን ብሄራዊ ትሩፋቶች ከግንባታው መጠናቀቅ በኋላም ከሚፈጥረው ሃገራዊ እና አህጉራዊ ተጽእኖ አኳያ መጠነኛ ቅኝት የሚያደርግና መሰረዊ ጉዳዮችን የሚያነሳ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት እለት አንስቶ  የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በሁሉም የሃገሪቱ  አቅጣጫዎች በርካታ የድጋፍ ሠልፎችን ከማካሄድ ጀምሮ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁሩ ድረስ ያለው በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በዕውቀቱ ለመርዳት  ቁርጠኝነቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወቅና ምናልባትም አለምን ያስደመመ እና ይልቁንም ደግሞ ተርጉሙ ሃይል ከማመንጨት በዘለለም በርካታ መሆኑን የሚያጠይቅ ሂደቶችን አሳልፏል፡፡  

የታችኛው ተፋሰስ የሆነችው ሃገረ ግብፅ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ እጇን በማስገባት ኢትዮጵያ ለምትገነባው ግድብ ዕርዳታ እንዳታገኝ ያደረገች ቢሆንም  ሃገራችን እና ህዝቧ ከአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ግድብ ለመገንባት ቁርጠኛ ስለመሆናቸው ያረጋገጡበት አግባብ በመሰረቱ ግድቡ ሃይል ከማመንጨት የዘለለ ብሄራዊ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ የተረጋገጠበት መሰረታዊው ነጥብ ነው፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ እስከ 6,450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም የሚኖረው እንደሆነ በዚሁ ጉባዔ ላይ ያረጋገጡት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ፤ ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘዋን ሱዳን ሳይቀር በሃይል ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም  ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ጉባኤ ላይ የቀረበው የህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤቱ ሪፖርት በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ዙሪያ የመላውን ኅብረተሰብ ተሳትፎ ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎችን ፣ የዲያፖራ ተሳትፎን ለማጠናከር የተከናወኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ሥራዎችን ጨምሮ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን አካቷል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ፣ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት፣ የችቦ መቀባበል ሥነ ሥርዓት፣ የዓባይ ቀን የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ የእግር ኳስ ውድድር፣ የዓባይ ቀን የጎዳና ላይ ትርዒት፣ የብስክሌት ውድደር፣ የሕፃናት የሥዕል ውድድር፣ የሥዕልና የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ፣ ሊቀ ናይል የጥያቄና መልስ ውድድር፣ የስድስተኛ ዓመት አከባበር በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራባቸው መሆኑን የሚጠቅሰው ሪፖርት ግድቡ እየተገነባ ባለበት ሂደት ውስጥ ሆኖም ያስገኛቸውን ውጤቶች ይዳስሳል፡፡መሰረታዊ የሆኑትን እና ሃይል ከማመንጨት ባሻገር ግድቡ በግንባታም ሂደት ውስጥ ሆኖ ያስገኛቸውን ትሩፋቶች እንመልከት፤

የመጀመሪያውና መሰረታዊው ነገር ብሄራዊ መግባባትን የፈጠረ ግድብ መሆኑ ነው። የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት እለት ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም የፖለቲካም ሆነ የሃይማት ልዩነት ሁሉም ከልጅ እስከ አዋቂ ያሳየው ድጋፍ፣ የሃገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያሳዩት ተነሳሽነት እና በግድቡ ዙሪያ የፈጠሩት አንድነት ከመቼውም በላይ እነዲቀራረቡ እና በጋራ እንዲረባረቡ ማድረጉ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር በየትኛውም ዘርፍ ለተያያዝናቸው አጀንዳዎች ትልቅ እና የገዘፈ ብሄራዊ አቅም ፈጥሮልናል፡፡  

ይህን ግዙፍ እና ሰፊ ገንዘብ የሚጠይቅ ግድብ ያለምንም የውጭ ሃገራት ብድር እና እርዳታ መንግስት ሲወስን በመሰረቱ ህዝቡ ስለአባይ ያለውን ቁጭትና ከሃይል የዘለለ ሉአላዊነትን በተመለከቱ ጉዳዮች የማይደራደር እንደሆነ ስለሚገነዘብ መሆኑ አያጠያይቅም። ስለሆነም የመሰረት ድንጋዩ በኖረበት ማግስት ተጨማሪ  ጥሪ ለህዝቡ ሳያስፈልግ በእልህ እና በቁጭት ተነስቷል። በራሳችን ጥረት አባይን እንገነባለን በሚል ወኔ የተነሳው ይህ ህዝብ ለዘመናት ተጠናውቶን የነበረውን የተረጂነት እና የተመጽዋችነት መንፈስ ከጫንቃችን አሽቀንጥረን በመጣል የይቻላል መንፈስን ሰንቀን በተግባርም እንድናረጋግጥ ያስቻለን በመሆኑ፤ ፕሮጀክቱ  በየተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል፡፡

ሶስተኛው ትሩፋቱ ደግሞ የስራ እድል ነው። በግንባታ ሂደት 6 አመታትን ያስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን መጀመር  ተከትሎ ሰፊ የሰው ሃብት በግድቡ ግንባታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመሰማራት የዕለት ኑሮውን እያሸነፈ ነው፡፡ ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ጉልበት ሰራተኛ ድረስ በግንባታው ስራ በመሳተፍ ባጠቃላይ ወደ 11ሺ የሚጠጉ ሰራተኞች እየተሳተፉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ300 በላይ ባለሙያዎች ከተለያዩ ዓለማችን ክፍሎች የመጡ ተቀጥረው የሚያገልገሉ የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡በስራው ላይ በቀጥታ ከተሰማሩትም ውጭ  በንግድ ፣ በምግብ እና ሌሌች ያገልግሎት ዘርፎች በርካታ ዜጎቻችን የስራ ዕድል ይፈጠርላቸው ዘንድ ምክንያት የሆነ ታላቅ ፕሮጀክታችን ነው። 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ የፈጠረው ሌላኛና አራተኛ ሊሆን የሚችለው ትሩፋት የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ነው። በዚህ ግድብ ግንባታ የበርካታ አመታት ልምድ እና ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ያለው የውጭ የግንባታ ድርጅት(ሳሊኒ) ከግማሽ በላይ ኮንትራቱን ወስዶ  ከዚህ ቀደም ያልታዩ ዘመናዊ እና ኮምፒውተራዝድ የሆኑ መሳሪዎችን ይዞ እየሰራ ነው፡፡ ከዚህ ኩባንያ ጋር የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የእውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ልምድ እያገኙ ነው፡፡ቀሪውን ኮንትራት የያዘው ሃገር በቀሉ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንም ያለውን አቅም ይዞ ወደ ስራው በመግባት በተግባር ልምምድ ሰፊ ልምድ ማዳበር እንዲሁም በአለም የታወቁ አማካሪ ድርጅቶችን እያማከረ መስራቱ ሰፊ የክህሎት እና ቴክኖሎጂ ልምድ ለመቅሰም እና አቅሙን ይበልጥ ለማዳበር አስችሎታል፡፡ ይህንንም በተግባር ከመጀመሪያው የግድቡ ዲዛይን ማሻሻል እና በቅርቡ ተርባኖችን በማሻሻል የተገኘው የግድቡ ኃይል የማመንጨት መጠን ከ5250 ወደ 6450 ማደግ የሚያሳየው የተሻለ አቅም ገንብቶ መገኘቱን ነው፡፡ እነዚህ የግድቡን እና የተርባይኑን ዲዛይን ማሻሻል ስራዎች በራሳችን ተቋም በነጻ መሰራታቸው እንጂ በውጭ ተቋማት ቢሆን ኖሮ ብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁን እንደነበርም መዘንጋት የማይገባን የታላቁ ግድባችን ትሩፋት ነው፡፡

ታላቁ የኢትጵያ የህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት የሚገነቡት ኢትዮጵያዊ ግድብ ነው፡፡ ግድቡን ለማየት በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት የተፈጠረ ሲሆን እስከዛሬ ከመላው ሃገሪቱ ከ300ሺ በላይ ዜጎች ግንባታውን ጎብኝተዋል፡፡የግልና የመንግስት ሰራተኞች፣ አርቲስቶች፣ የተለያዩ የሲቪክ እና የሙያ ማህበራት እና አደረጃጀቶች፣ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በቡድን በመሆን በራሳቸው ወጪ ግድቡን ለመጎብኘት ሲጓዙ የሶስት ክልሎችን (አማራ፣ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) ከተሞች እና መልክዓ ምድር በመጎብኘት ስለሃገራቸው ያላቸው እውቀት እና አድናቆት የጨመረ ሲሆን  ይህ ደግሞ  የሃገር ውስጥ ቱሪዝምን መስፋፋት፤ የሃገር ውስጥ የንግድ ፍሰትን እና መነቃቃትን በማስከተል ልማትን ለማፋጠን ያስቻለ ለመሆኑ በእነዚህ ክልሎች ከተሞች እና መንደሮች በታዩት ከፍተኛ ለውጦች ተረጋግጧል፡፡

ቀጥሎ የሚመጣው ትሩፋት ደግሞ አለማቀፋዊ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሃገራችን የህዳሴ ጉዞ ጮራ ፈንጥቋል፡፡ በዚህ ግድብ ላይ ዜጎች መተማመን እና ተስፋ የሰነቁ ሲሆን ግድቡን ለማጠናቀቅ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ግንባታው እንዲደናቀፍ ካለመፈለግም የተነሳ ባንዳንድ ችግሮች የሚፈጠሩ ሁከቶችን ቸል በማለት ሰላሙ እንዳይደፈርስ ሲከላከል መታየቱ ስለዚህ ነው፡፡የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጀመር በዋናነት የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ለውይይት እና ምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እንዲወያዩ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ወንዙን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በጋራ የመጠቀም መርህ በመያዝ በቅንነት በሯን ለዲፕሎማሲ ክፍት አድርጋ አቋሟን በግልጽ ያራመደች ሲሆን ይህ መርህ እየዳበረ ሄዶ በመጨረሻም የተፋሰስ ሃገራቱን ለመርህ ስምምነት አብቅቷል ፡፡ይህ ዲፕሎማሲ ድል የተገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጀመሩ ሲሆን ከአፍሪካ ርቃ የቆየችው ግብጽ ወደ አፍሪካ ኅብረት መምጣት እና ከኢትዮጵያም ጋር ያላት ግንኙነት በመሻሻል ላይ እንዲገኝ በማስቻል አለማቀፋዊ ትሩፋቱም የገዘፈ ውድ ፕሮጀክታችን እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡

የሃገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ክንዳቸውን በድህነት ላይ በማንሳት በስኬት በመራመድ  በዚሁ ፕሮጀት መነሻነት የአድዋን ድል በመድገም ላይ ናቸው፡፡  የሃገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ከዳር ዳር በመነሳት ህብረ ብሄራዊ ክንዳቸውን በማስተባበር ለዘመናት ጠላታችን የነበረውን ድህነት  ከጫንቃችን ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል እያደረጉት ያለው ትግል ሌላው በዚህ ፕሮጀክት የተገኘ  አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ግድብ ግንባታ ያለምንም የውጭ ድጋፍም ሆነ ብድር በራሳችን አቅም ተጠናክረን ግድቡን እዚህ ደረጃ ላይ ማድረሳችን ለአፍሪካም ሆን በዓለም በማደግ ላይ ላሉ ሃገራት በራሳቸው አቅም ህዝባቸውን አስተባብረው ማደግ እንደሚችሉ ያሳየ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክታችን ነው፡፡