የወጣቱን ተስፋ የሚያለመልም ዓመት

መጪው አዲስ ዓመት ዓመት ለወጣቱ ይዞ የሚመጣውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዩች በርካታ ናቸው። በፖለቲካው ረገድ ወጣቱ መንግስት ባመቻቸው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ መሳተፍ ይችላል፣ በኢኮኖሚው ረገድም መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በሚወስዳቸው ርምጃዎች ላይ በንቃት መሳተፍ የሚያስችለው እንዲሁም በማህበራዊ መስክ ወጣቱ ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ቀና የትብብር መንፈስ የሚፈጥርበት ነው። አዎ! አዲሱ ዓመት ለመላው ህዝብ በተለይም የህዝባችን 70 በመቶ ለሚሆነው ወጣት የተስፋ ፀዳልን የሚያይበት ዓመት ነው።

መጪውን አዲስ ዓመት በብሩህነቱ “ማለም” ዛሬን በተስፋ ውስጥ ሆነን እንድንኖር ያደርገናል። ይሁንና “ህልሙ” በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያለን ዕውነታ የሚያመላክት፣ ከወዲሁ የሚታይና የሚዳሰስ እንጂ፤ በህልምነቱ የምናውቀውን የማታውን ዓይነት እውነተኛ ህልም መሆን የለበትም።

በመሆኑም የመጪው አዲስ ዓመት “ህልም” ተጨባጭ መሆን አለበት። ከወዲሁ አሸንዳን የመሳሰሉ ባህላዊ እሴቶችን ስናከብር እንዲሁም “እዮሃ አበባዬ…” ብለን አዲሱን ዓመት ስንቀበል፤ በግለሰብ ደረጃ የምናቅደው አዲሱ “ህልማችን” የሚደረስበትና ሰላማዊ መሆን እንዳለበት መዘንጋት አይኖርብንም። የትናንት የሁከትና የብጥብጥ ችግሮቻችንን የምንክስበት ዓመት ሊሆን ይገባል። የሰላምን ፀዳል የምንላበስበት መሆኑም እንዲሁ።

የማይደረስበትና ሰላማዊ ያልሆነ “ህልም” ቅዠቱ አያስተኛም። ውስጣዊ ቀውስንና ጥፋትን እንጂ ዕድገትንና ብልፅግናን አያመጣም። በመሆኑም በ2006 ዓ.ም የምናልመው “ህልም” ልኬቱና ስኬቱ ማግኘት የምንችለውን ብቻ ነው መሆን ያለበት። በፖለቲካው፣ በማህበራዊውም ይሁን በምጣኔ-ሀብቱ መስክ የሚታሰቡ ጉዳዮች የስኬት ልኬታቸው የነገ ሰው የመሆን ህልምን ማንፀባረቅ ይኖርባቸዋል።

“ወደፊት የማይሄድ፣ ወደ ኋላ እየተራመደ ነው” እንደሚባለው፤ በ2009 ዓ.ም ከነበርንበት ቦታ ወሳኝ በሆኑ ሜትሮች ወደ ላይ ከፍ ማለት ይኖርብናል። በትናንቱ ቦታ ፈፅሞ መገኘት አይኖርብንም። የነበረን አመለካከት በአዲሱ ዓመት በአዲስ ሰላማዊና የተጠቃሚነት መንፈስ መቀየር ይኖርበታል። ለምሳሌ በ2009 ዓ.ም በፖለቲካው ረገድ በወጣቶች ዙሪያ የታዩ የለውጥ ስራዎች በ2010 ዓ.ም ይበልጥ መጎልበት ይኖርባቸዋል።

ርግጥ አንድ ሰው አዲሱን ዓመት ሲቀበል ራሱን ሰላማዊ ባልሆነ፣ በማይጨበጥና ከገሃዱ ዓለም ዕውነታ ጋር የማይገናኝ ጉዳይን “ካለመ” ከጉዳቱ ባሻገር የከፋ መዘዝንም ሊቀበል ይችላል። እናም መጪው አዲስ ዓመት መንግስት የጀመረው የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙስናን አመለካከትና ተግባር በመዋጋት ረገድ እያደረገ ያለውን ጥረት ማገዝ ይኖርበታል። ጉልህ ሚናም መጫወት አለበት። ተግባሩንም መፀየፍ ይኖርበታል።

ርግጥ እዚህ ላይ አንድ ወዳጄ ያወጋኝን እውነተኛ ታሪክ ማንሳት ይህን አባባሌን ይበልጥ የሚያሰረዳልኝ ይመስለኛል። ነገሩ እንዲህ ነው።…የታሪኩ ባለቤት የሆነው የወዳጄ ባልንጀራ ተጨማሪ ገቢ የሌለው የመንግስት ሰራተኛ ነው። በወር ደመወዝ ብቻ የሚተዳደር። ይህ ሰው በአሮጌው ዓመት መገባደጃ ላይ በሚቀጥለው ዓመት ሃብታም መሆን አለብኝ ብሎ ይወስናል።

እንግዲህ ይታያችሁ!…በወር ደመወዝ ብቻ የሚተዳደር ሰው ሌላ የመበልፀጊያ ዘዴ ከሌለው በስተቀር በምን ዓይነት ሁኔታ ሃብታም ሊሆን ይችላል ትላላችሁ?…ያም ሆነ ይህ ግን ግለሰቡ ሃብታም የመሆን “ህልሙን” አጠናክሮ በመያዝ ወጉን ለነገረኝ ወዳጄ፤ “አዲሱ ዓመት ሲመጣ ታየኛለህ፣ የእኔና የአንተ የአፍሪካና የአሜሪካ ያህል ልዮነታችን ይሰፋል!” በማለት የአዲሱን ዓመት መግባት በናፍቆት መጠባበቅ ይጀምራል።…

አዲሱ ዓመትም ገባ።…መስከረምም ጠባ።…የዓመቱ መባቻ ተከታታይ ቀናት ውስጥ የወዳጄ ጓደኛ ከመስሪያ ቤቱ ተሰወረ።…ቢሮው ብቅ አላለም።…ግና ከእነ አካቴው አልቀረም። በወሩ አጋማሽ ላይ ግለሰቡ ለወዳጄ ስልክ ይደውላል። የስልኩ መልዕክትም “እስከ መስከረም 20 ቀን ድረስ ሃብታም ሆናለሁ” የሚል ነበር።

ነገሩ ግራ ያጋባው ወዳጄ ስልኩ የተደወለበትን ቀን ለማወቅ እጆቹን ወደ ካላንደሩ ላካቸው—መስከረም 15 ቀን ይላል። በአምስት ቀን ውስጥ ጓደኛው እንዴት ሃብታም ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰል ጀመረ—ምንም ነገር ግን ሊገለፅለት አልቻለም። እናም መስከረም 20ን እርሱም በተራው ይናፍቅ ጀመር።…ዳሩ ምን ያደርጋል?!—ጓደኛው መስከረም 20ን እንደናፈቃት ቀርቷል።እንዴት?…ነገሩ ወዲህ ነው።…

ይህ ሰው የሚያውቀው የመስሪያ ቤታቸው ገንዘብ ያዥ ለስራ ጉዳይ አምጥቶ ካዝና ውስጥ ያስገባውን ገንዘብ በወዳጄ ጓደኛና በግብረ-አበሮቹ ተዘረፈ። ግና ፖሊስ ባደረገው ጥብቅ ክትትል ዘራፊዎቹ ተይዘው ዘብጥያ ወረዱ። የወዳጄ ጓደኛም የሃብታምነት “ህልሙን” ደግሞ ደጋግሞ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲያየው ተገደደ።…“ይህ ሰው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት በመሆኑ፣ የቤተሰቦቹን የአዲስ ዓመት ተስፋ ይዞ ነው እስር ቤት የገባው” ሲል በምሬትና በፀፀት ወዳጄ አውግቶኛል።

እናም ከዚህ ክስተት ማንም ሰው ነገ አገኘዋለሁ ብሎ የሚያልመው ስኬት በራሱ ወዝና ላብ ጥሮ ግሮ የሚያገኘው የድካሙ ዋጋ ነው መሆን ያለበት። የሀገርንና የህዝብን ሃብት በመቀማት ወይም የራስ ያልሆነን ሃብት በአንድ ቀብ በአቋራጭ ለማግኘት መሞከር አደጋው ህይወትን እስከ ማጣት ድረስ ሊያደርስ ይችላል።

በአዲስ ዓመት “ማለም” ያለብን ነገር በአሮጌው ዓመት የነበሩብንን ችግሮች የሚያቃልል፣ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እንዲሁም በሰላማዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ እውነታን እንጂ በአቋራጭ መበልፀግን ሊሆን አይገባም። በአቋራጭ ለመበልፀግ መሞከር ሀገርንና ህዝብን ከመጉዳቱም በላይ በራስና በቤተሰብ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ከላይ የጠቀስኩት አብነት ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።

በመሆኑም በአዲሱ ዓመት ያልተገባ ጥቅምን ወይም ኪራይ ሰብሳቢነትን በማውገዝና ሰላማዊ ሆነን ሀገርንና ህዝብን በማይጎዳ ተግባር ላይ በመዋል አዲስ ተስፋን መሰነቅ አለብን። በተለይም ሙስና “በነገ ሰውነታችን” ላይ ጉልህ የጥፋት አሻራ የሚያሳርፍ እንዲሁም የህዳሴ ገዟችንን የሚያዘገይ በመሆኑ ልንኮንነውና በቁርጠኝነት ልንታገለው ይገባል።

ኪራይ ሰብሳቢነት ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮት ጀምሮ የብዙ ዓመታት ታሪክ ያለው ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ሙስና በመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ከአይሁዳውያን ሊቃውንት ጀምሮ እስከ እየሱስ ክርስቶስ ሃዋሪያት ድረስ ለነበሩ መንፈሳውያንም ፈተና ነበር።

በዚያን ዘመን መንፈሳውያኑ ገንዘብ ያታልላቸው ነበር፤ መለማመኛም ከምዕመኖቻቸው ይቀበሉ እንደነበር ይነገራል። የአስቆሮቱ ይሁዳ 30 ዲናሩንም ይሁን አሳልፎ የሰጠውን የኢየሱስ ክርስቶስን መጨረሻ እንኳን ሳያይ ራሱን ግራር ላይ ሰቅሎ ተገኝቷል። የሐጢያቱ መጨረሻም አላማረምና ክርስቶስ በትንሳኤው ሌሎች ሃዋሪያትን ሲያነፃ፣ ይህን ዕድል ለአስቆሮቱ ይሁዳ አልሰጠውም። ይህ ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር፤ የዛሬው ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ከምድራዊ ተጠያቂነት ባለፈ ሰማያዊ ቁጣም ጭምር ያለበት መሆኑን ነው።

የዚህ ክፉ ደዌ አስተሳሰብና ተግባር በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደ ቫይረስ እየተስፋፋ፣ ድሃውን እያቆረቆዘ፣ ጥገኛ ባለሃብትን የሚያበለፅግ መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል። በሀገራችንም እየፈጠረ ያለውን ቀውስ ሰሞኑን በሙስና ተግባር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች ለመረዳት አይከብድም። እናም የአደጋውን ክብደት ወጣቶች ሊገነዘቡት ይገባል።

በጥቅሉ መንግስት በመጪው ዓመት የወጣቱን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱና ተስፋን የሚያለመልሙ በርካታ ውጥኖችን ይዟል። እነዚህን ውጥኖች በአግባቡ መጠቀም ይገባል። ወጣቱ ከመንግስት የሚያገኘውን ገንዘብ ለተገቢው ዓላማ በህጋዊ መንገድ መዋሉን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን መዘንጋት አይኖርበትም። ወጣቱ በተከፈተለት ብሩህ መንገድ እየተጓዘ የሀገሩና የህዝቡ መድን መሆን ይጠበቅበታል እላለሁ።