የኮሌራ ወረርሽኝ በሱዳን የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑ ተገለጸ

የኮሌራ  ወረርሽኝ በሱዳን የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑ ተገለጸ ።

ወረርሽኙ ባለፈው አመት 940 ሱዳናዊያንን ለሞት መዳረጉም ይታወሳል፡፡

በሰሜናዊ ሱዳን በኮሌራ ወረርሽን የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ያሻቀበ ሲሆን አራት ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ ሌሎች አስራ ሁለት ሰዎችም በበሽታው መጠቃታቸው ተረጋግጧል፡፡

ወረርሽኙ በተለይም አብሪ እና ኤል ማሃስ በተባሉ የሴሜናዊ ሱዳን አካባቢዎች ላይ በስፋት የተስተዋለ ሲሆን በዚሁ አካባቢ በ4 ቀናት ውስጥ ብቻ በርካታ ጉዳት አድርሷል፡፡

አስራ ሁለት ሰዎች ላይ ወረርሽኙ እንዳለባቸው መረጋገጡን ተከትሎ በአልመሃስ ሁለት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡

በኤልታግሚ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆችም  ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይሄዱ ማገዳቸውም ነው የተነገረው፡፡

የአካባቢው ዝነኛ የሆነው ሳድናፌንቲ ትምህርት ቤት ግን ወረርሽኙ በአካባቢው መከሰቱ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ መዘጋቱም ተመልክቷል፡፡

የኤል ማሃስ አካባቢ ትልቁ የሆነው ኤል ቱራ ሆስፒታል ለኮሌራ ህክምናው ሙሉ ትኩረቱን ማድረጉ በሌላ በሽታ ለተጠቁ የሆስፒታሉ ታካሚዎች ሌላ የራስምታት ሆኖባቸዋል፡፡

በኤል ቱራ ሆስፒታል አራት ተጨማሪ በኮሌራ የተጠቁ ሰዎች የተለዩ ሲሆን አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላልም ተብሏል፡፡ በአብሪ አካባቢ ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ አስራ ስምንት አሻቅቧል፡፡

ይህ ወረርሽኝ በማዕከላዊ ዳርፉርም የተከሰተ ሲሆን 2 ሰዎችም በኮሌራ መጠቃታቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህን ተከትሎም  በአካባቢው የተጠቂዎች ቁጥር ሰላሳ ዘጠኝ ደርሷል፡፡

ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በአባይ ተፋሰስ ሃገራት አካባቢ በተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ ሃያ አራት ሺህ ሱዳናዊያን በወረርሽኙ የተጠቁ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የ940ው ህይወት ማለፉን ሃገሪቱ ይፋ ያደረገችው መረጃ አመልክቷል፡፡

የሃገሪቱ ባለስልጣናት ወረርሽኙን ኮሌራ በሚለው መጠሪያ ስም ከመጥራት ይልቅ ውሃ ወለድ በሽታ ማለትን የሚመርጡ ሲሆን በሃገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የሚዲያ ተቋማት ኮሌራ በሚለው መጠሪያ እንዳይጠቀሙም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡( ምንጭ: ከራዲዮ ዳባንጋ)