ሀገራችን በውጭ የዜና አውታሮች እይታ

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሐን ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰፊ ዘገባዎችን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሀገራችን በኢንቨስትመንት፤በቱሪዝም፤ በሀገራዊ የልማት እድገትዋ በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን፤ በአሕጉራዊና አለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ስራዎችዋ በአፍሪካ ቀንድ እያደገ በመጣው ተጽእኖ ፈጣሪነትዋ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ስምሪት በመቀበል  በአለምአቀፍ ግዳጅ የተወጣቻቸውንና በመወጣት ላይ የምትገኘውን ኃላፊነት በተመለከተ  ሰፊ ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡  
አክራሪ የእስልምና ኃይሎች በአሸባሪነት ተሰማርተው የሚፈጽሙትን ኢሰብአዊ ድርጊት በመዋጋት ረገድ የተወጣቻቸውን ግዳጆችና ሌሎችንም ጉዳዮች በተመለከተ አለምአቀፉ ሚዲያ ሰፊ ሽፋን በመስጠት በበርካታ አጋጣሚዎች ዘግቦአል፤ ዛሬም በመዘገብ ላይ ይገኛል፡፡
በአብዛኛው ኢትዮጵያ በሀገራዊ የልማትና የኢኮኖሚ ስኬት ደረጃ እያደገች በመሄድ ላይ መሆንዋን የሚያጎላና የሚያረጋግጥ ነው፡፡ አጠቃላይ የአለም አቀፍ ሚዲያው ዘገባ ሲታይ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴ ላይ የምትገኝ ሀገር መሆንዋን አጉልተው ያሳያሉ፡፡ ይህም ሀገራችን በውጭውአለም ቀደም ሲል የነበራት ስም ዛሬ ላይ ባስመዘገበቻቸው ፈርጀ ብዙ የኢኮኖሚ ድሎችና ስኬቶች እየተለወጠ ለመምጣቱ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡
አለምአቀፉ መገናኛ ብዙሀን ትኩረቱን በኢትዮጵያ ላይ ማድረጉን ወደፊትም በስፋት ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ዛሬም ነገም በመመዝገብ ላይ ያሉ ታላላቅ ሀገራዊ የመሰረተ ልማት ስርነቀል ለውጦች የኢኮኖሚ እድገቶች የልማቱ ቀጣይነት ለውጭ ኢንቨስተሮች ተመራጭ ሀገር መሆንዋ ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው የሚዲያውን ቀልብ የሚስብ ስለሆነ ነው፡፡

ወርልድክረንች ድረ-ገጽ (www.worldcrunch.com) በዘገባው ቻይና በኢንዱስትያል ፓርክ ግንባታ በሰፊው መንቀሳቀሷ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወደ ፓርኮቹ መግባታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶች ቁጥራቸው በመጨመር ላይ እንደሚገኝ ለዚህም ማሳያው የአዋሳው ኢንዱስትሪያል ፓርክ በፍጥነት እያደገ መምጣቱ፤ ባለፉት አምስት አመታት 279 የቻይና ኩባንያዎች 550ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ፈሰስ ማድረጋቸውን አስፍሮአል፡፡
የቻይናው የዜና ወኪል ዢንዋ “ግሎባል ሪሰክ ኮንሰልተንሲ” የተሰኘን ተቋም ዋቢ በማድረግ ኬንያና ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚያቸው እያገገመ ቢሆንም አሁንም ስጋት እንዳንዣበባቸው ዘግቦአል፡፡ አያይዞም፣ በ2009 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት 20 በመቶ አድገት ማሳየቱን፤ በዚሁ መሰረትም በተጠናቀቀው የ2009 የበጀት ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ መሳቧን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሐይሉን ጠቅሶ ዢንዋ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን መንግስት የውጭ ንግዱን ለማሳደግ እንዲሁም በርካታ የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ በዘርፉ ተስፋ ጥሎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፤ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በተለያዩ መንገዶች የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ሌት ተቀን እየሰራች መሆኗን የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባንቲሁን ገሰሰ ገልፀዋል ሲል ይሄው የቻይና ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል፡፡  
ኢትዮጵያ በምርጥ አፈፃፀም የተሻለች ሀገር መሆኗን አሳይታለች ያለው ዘገባው እ.ኤ.አ በ2016 ኢትዮጵያ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 3.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሳብ የቻለች ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም በአማካኝ 10 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ስታስመዘግብ ቆይታ ባለፈው አመት የኢኮኖሚ እድገቷ 6.5 በመቶ መሆኑን በመጠቆም ምክንያቱም በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ከጎሣ እና ከብሔር ጋር መተሳሰሩ ስጋት ሳይሆንባት አልቀረም ሲል ገልጾአል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን (UNHCR) ዋቢ በማድረግ የዘገበው ዢንዋ ኢትዮጵያ 72ሺህ 890 ስደተኞችን በስምንት ወር ጊዜ ውስጥ ተቀብላ ማስተናገዷን እና 44,000 ከደቡብ ሱዳን፣ 17ሺ ከኤርትራ እንዲሁም 6ሺ 400 ከሶማሊያ መቀበል መቻሏን በቅርቡ ያስተናገደችውን 72ሺ 890 ስደተኛ ጨምሮ በአጠቃላይ እስካሁን 852ሺ 721 ስደተኞችን ተቀብላ ያስተናገደች በመሆኗ ከአፍሪካ ስደተኞችን በመቀበል በሁለተኛ ደረጃን አስቀምጧታል በማለት የዩኤንሲኤችአር ኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ክሱት ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል ሲል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገ/ማርያምን ዋቢ በማድረግ የዘገበው ብሉምበርግ አየር መንገዱ ከዛምቢያ፣ ቻድና ኮንጎ አየር መንገዶች ድርሻ በመግዛት የተለያዩ የበረራ ማእከላትን ለመመስረት ድርድር ላይ መሆኑን መግለፃቸውን ይህም አየር መንገዱን በደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን ከዛምቢያ መንግስት ጋር በቀጣይ ሕዳር ወር የስምምነት ፊርማ እንፈደሚፈፀም ስራ አስኪያጁ መግለፃቸውን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ የፀጥታ ጥብቃ ም/ቤት ፕሬዝዳንትነትን ኃላፊነቷን  በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መቀበሏን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢፌዲሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት አምባሳደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ በኒውዮርክ በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸውን፤ ኢትዮጵያ የአሁኑን ጨምሮ ለሦስት ጊዜ ያህል የፀጥታ ም/ቤቱ አባል ሆና መሥራቷን በመግለጽ የም/ቤቱን የፕሬዝዳንትነት ኃላፊነት በስኬት ለመወጣት ጥረት ታደርጋለች ማለታቸውን የተመድን ድረገጽ በማጥቀስ የውጭ እና የአገር ወስጥ ሚዲያዎች በሰፊው ዘግበዋል፡፡
በጋና መዲና አክራ ውስጥ በተካሄደው ሁለተኛው የጋና ብሔራዊ የአቪየሽን ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሦስት ሽልማቶችን ማሸነፉን በዚህም አየር መንገዱ የዓመቱ ምርጥ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሽልማት፣ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማት እንዲሁም ምርጥ የአየር መንገድ ሥራ ሽልማቶችን ጠቅልሎ መውሰዱን ጋና ኒውስ ኤጀንሲ  ዘግቧል።
የእንስሳት እና የዓሣ ሃብት ሚኒስቴር ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በመጪው በጀት ዓመት የበግ፣ የፍየል፣ የከብት እና የግመል ዝርያን እና የውልደት ቀንን የመለየት እና የመመዝገብ ሂደት ሊጀምርሩ መሆናቸውን እና ይህ የእንስሳቱን ዝርያ እና የውልደት ቀንን መለየት እና መመዝገብ ያስፈለገው፣ የእንስሳቱን ሞት እና የሌሎች ችግሮች ተጋላጭነትን  በመቀነስ እና ውጤታማ በማድረግ ወደ ውጭ የሚላከውን የሥጋ ምርት ለማሳደግ መሆኑን ካፒታል ጋዜጣ በዘገባው አስፍሮአል፡፡
የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ የ15 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መለገሱን እና እርዳታውም በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ እና ረሀብ ለመከላከል እንደሚውል የቻይናው ቆንስላ ሃላፊ Liu Tao እና የኢትዮጵያ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር አቶ አብረሃም ተከስተ በአዲስ አበባ ቻይና ኤምባሲ በተፈራረሙበት ወቅት ገልፀዋል ሲል ዢንዋ  የዜና ወኪሉ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በ2009 በጀት ዓመት ከለጋሽ ሀገራትና ከአጋሮቿ 3.4 ቢለዮን ዶላር በብድርና በድጋፍ መልክ ማግኘቷን፤ የተገኘው ገንዘብ በሒደት ላይ ላሉ እና ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሐጂ ኢብሳ መግለጻቸውን፤ የውጭ እርዳታና ድጋፉ የ2009 ዓ.ም በጀትን 18 በመቶ ይሸፍናል ማለታቸውን የቻይናው ዢንዋ ገልጾአል፡፡ ሀገሪቱ ከግብርና ከታክስ የበጀቷን 80 በመቶ ለመሸፈን መጠነ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የገለጸው ዢንዋ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ገቢ በታቀደው መልኩ አለመጓዙ  በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ረገድ ክፍተት መፍጠሩን ገልጾአል፡፡