ፕሬዚደንት ፈርማጆ ከሳውዲ አረቢያው ንጉስ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ጋር ተወያዩ

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ከሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን አብዱልአዚዝ ጋር  በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በሪያድ መክረዋል፡፡

በተለይም  በአራቱ የባህረ ሰላጤው ሀገራትና በኳታር መካከል የተከሰተውን ውጥረት ለማርገብ ሶማሊያ የሚኖራትን ገለልተኛ ሚና  በተመለከተ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ነው የተነገረው፡፡

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በሳኡዲ አረቢያ ያካሄዱት የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ሶማሊያ በወቅታዊው የገልፍ ሀገራት ውዝግብ ላይ ገለልተኛ አቋም እንዳላት ማስታወቋን ተከትሎ የተካሄደ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ ሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክርና ውጤታማ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ምክክር ማድረጋቸውን ነው የበርናማ ዶት ኮም ዘገባ ያመለከተው፡፡

ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ከሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን አብዱልአዚዝ ጋር ሰፊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፥ ልዑኩ ከዚህ በተጨማሪ በልዑል ሞሃመድ ቢን ሰልማን ከተመራ የሳዑዲ ባለሃብቶችና የስራ ሃላፊዎች ጋር በኢኮኖሚያዊ ትስስር ዙሪያ በጅዳ መክሯል፡፡

ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስና ባህሬይን እኤአ  ከሰኔ 5 ቀን ጀምሮ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው ይታወሳል።

አገራቱ የዲፕሎማሲ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ከማቋራጥ ባለፈ ወደ ዶሃ የሚደረጉ የአየር በረራዎች እና የባህር ትራንስፖርቶችን በክልልቸው እንዳይደረጉም አግደዋል።

ከሀገራቱ ኳታር ሽብርተኝነትን በገንዘብ ትደግፋለች፤በተለይም እንደ እስላሚክ ስቴት ያሉትን አለምአቀፍ አሸባሪዎችን ሳይቀር በተለያየ መልኩ ስትደግፍ ቆይታለች የሚል ውንጀላ ቢሰነዘርም ኳታር ይህንን በተደጋጋሚ አጣጥላለች፡፡

የግብፅና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኳታር ሽብረተኞችን የመደገፍ የቆየ ታሪክ እንዳላት በማንሳት፥  ከኢራን ጋር ለወደቀችለት ፍቅርም ዋጋ እንደምትከፍል ሲዝቱ ከርመዋል፡፡

አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትም ይህን ውዝግብ ተከትሎ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

ለአብነትም ቻድ በኳታር የሚገኙ አምባሳደሯን ጠርታ ያናገረች ሲሆን፥ሴኔጋል በበኩሏ ከቋሚ መልእክተኛዋ ጋር ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ሊኖራት ስለሚገባ ሁሉን አቀፍ ግንኙነት መክራለች፡፡

በቅርቡ በግብፅ ካይሮ በተካሄደው የአረብ ሊግ አገራት ጉባኤ  ላይም ኳታርብ ባገለሉ የባህረ ሰላጤው አገራት ተወካዮች መካከል የነበረው የቃላት ጦርነትም  በባህረ ሰላጤው ሀገራትና በኳታር መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ስለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይጠቅሳሉ፡፡