ዴሞክራሲና ልማት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ…

በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በጋራ ሆነው በርካታ መከራንና ስኬቶችን  አሳልፈዋል። ህዝቦችን መለየት በማይቻልበት ሁኔታ  ተቀላቅለው አንዱ አንዱን መስሎ ሳይሆን ሆኖ የሚኖርባት አገር ናት።  ይሁንና  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ   የህዝቦችን አንድነት ለመናድ የሚደረጉ  ሩጫዎችን ከውጭም ከውስጥም  እየተመለከትን ነው።  መንግስትን የሚመራው ኢህአዴግ በራሱ ጭቆና የወለደው የትግል ግንባር ነው። ይህ ፓርቲ የሚታወቀው በውስጠ ዴሞክራሲያዊ አሰራሩና ልዩነቶችን አቻችሎ  ማስኬድ  በመቻሉ ነው። ኢህአዴግ ደርግን  ለመጣል በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል  ስኬታማ የሆነው በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ አካሄዱና አባላቱ ለድርጅቱ መርህ ያላቸው ተገዢነት  ነው። የኢህአዴግ ታጋዮች  በትግል ወቅት  በፈንጅ ላይ ለመረማመድ  እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም  የሚባባሉበት አንዱ ለሌላው  ልሙት  የሚልበት  ድርጅት ነው።  እነዚያ ህዝባዊነት የተላበሱ የህዝብ ልጆች  የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለው ለዛሬው  የዕኩልነትና  የነጻነት ቀን አድርሰውናል። ዛሬ ያ ህዝባዊነት በኢህአዴግ ውስጥ አለ ይሆን?  ይህ  ርዕሰ  ጉዳይ  የዛሬ ጽሁፌ  ጉዳይ  ባለመሆኑ  እዚህ ላይ ላቁመው።
በአዲሲቷ  ኢትዮጵያ ጥያቄው የልማትና የመልካም አስተዳደር መስፈን  እንጂ  የዕኩልነትና ዴሞክራሲ እጦት  አይደለም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ማንም ከማንም አይበልጥም፤ በተመሳሳይ ማንም ከማንም አያንስም።  ሁሉም ክልሉን እያስተዳደረ በጋራ ቤታቸው በሆነው  የፌዴራል መንግስት ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  እኩል ውክልና እንዲኖራቸው ተደርጓል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን አይቻልም።  በምስራቅ  ኤዥያ  ልማትና ዴሞክራሲ በእኩል ማራመድ አልቻሉም።    በኢትዮጵያ  ግን  ሁለቱ  ሊነጣጠሉ አይችሉም።  ምክንያቱም ኢህአዴግ  በራሱ  ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ  የታገለ  ፓርቲ ነው።  የኢትዮጵያ እና የቻይና ነባራዊ ሁኔታ እጅግ የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።
የኢፌዴሪ መንግስት የህዝቦችን የመልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችል ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ  መንግስት  መተግበር ብቸኛው አማራጭ አድርጎ ወስዶታል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ዴሞክራሲው ወይም ልማቱ  ተነጣጥለው ሊተገበሩ አይችሉም።  መንግስት እየተከተለው ያለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አገሪቱን በተጨባጭ የለውጥ ምህዋር ውስጥ እንድትገባ አስችሏታል። በእርግጥ የአገራችን ዴሞክራሲ ስርዓት  መጎልበት ይጠበቅበታል።   ይሁንና  ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓታችን  የዜጎችን  ሰብአዊና  ዴሞክራሲያዊ  መብቶች አስጠብቋል።  አምስት አገራዊ ምርጫዎችን በማካሄድ ይሆኑኛል ይበጁኛል ላላቸው ተወካዮች ድምጹን በነቂስ ወጥቶ በነጻነት ሰጥቷል።  ህዝቦች በተወካያቸው መተዳደር፣ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ፣  ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በነጻነት መጠቀምና ማሳደግ እንዲሁም  በአገራዊ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብታቸውን አረጋግጠዋል። ቀድሞ በህዝቦች መካከል ይታይ  የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማረም መተማመንና መከባበር የሚያስችል ስርዓት ተፈጥሯል።
ተሃድሶ ተካሂዶ  በነበረበት ወቅት መረዳት እንደተቻለው ህብረተሰቡ እንዲረጋገጥለት የሚፈልገው “ልማት” ብቻ ሳይሆን “ፈጣን ልማትን” ነው። በቀድሞ ስርዓት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያልነበራቸው አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲ፣ የጠጠር መንገድ ያልነበራቸው አካባቢዎች የአስፋልት መንገድ፣ ወዘተ በመጠየቅ  ላይ ናቸው። ይህ የህብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ጊዜው የፈጠረው የመለወጥ ፍላጎት ነው። ይህን ለማሳካት መንግስትና ህዝብ እጅግ ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል።  
አንድ አገር እንደአገር ልትቀጥል የምትችለው የህዝቦቿን ጥያቄዎች መመለስ እንዲሁም ፍላጎታቸውን  ማሳካት ስትችል ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ በእኛ አገር ጎልቶ የሚታይ  ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ  ስርዓትን ለማስፈን ለዘመናት መሰዋዕትነት ከፍለዋል። በርካቶች ውድ ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረዋል። ዛሬ የብሄር ጭቆና አለብኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይችልም። እያንዳንዱ ክልል፣ እያንዳንዱ ዞንና እያንዳንዱ ወረዳ  ልማቱን ለማፋጠንም  ይሁን ልማቱን  ለመጎተቱ  ማመስገንም ይሁን  ማማረር ያለበት በቅርብ ያሉ አስተዳዳሪዎቹን  ነው።  
አገራችን  ባለፉት 26 ዓመታት  ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ዕድገት የሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎችና ጎጦች  ድምር ውጤት ነው።  በሁሉም የአገራችነ ቀበሌዎች ለውጥ ተመዝግቧል።  ምናልባት የለውጡ  ስፋትና ጥልቀት ወጣ ገባ ይሆን እንደሆን እንጂ  በየትኛውም የአገራችን ኮርነር ተጨባጭ  ለውጥ አለ።   በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት  ዓለምን ያስደመመ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በዜጎች ህይወት ተጨባጭ ለውጦች ታይቷል።  የድህነት መጠኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረበት ከ44 በመቶ  በግማሽ ዝቅ  ማድረግ ተችሏል። በርካታ ማህበራዊ መገልገያዎች ተገንብተዋል። መንግስት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተመጣኝ  ልማት እንዲኖርና  በህዝቦች መካከል ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲሰፍን  የሚያደርጋቸው ጥረቶች በተጨባጭ ለውጥ አሳይተዋል። አገራችን መሰረታዊ  የመንግስታቱን ዘላቂ ግቦች በተለይ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ  ማሳካት ችላለች።  
ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ መንግስት የተከተለው ግብርና መር የኢኮኖሚ ቀመር ፈጣን ልማት ከማረጋገጡ ባሻገር በአገራችን ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል  እንዲኖር አግዟል የሚል ዕምነት አለኝ።  ምክንያቱም  የግብርናው ዘርፍ  በአገራችን በርካታውን የሰው ሃይል ያቀፈ  ዘርፍ ነው።  በዚህ ዘርፍ የተመዘገበው  ለውጥ በእያንዳንዱ አርሶና አርብቶ አደር ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ችሏል። የአገራችን ለውጥ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን   በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ጭምር የታየ ነው።
በአንዳንዶች ኢትዮጵያ   በኢኮኖሚው ዘርፍ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችውን  ያህል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ ዕምርታ አላመጣችም የሚል ክርክር ሲያነሱ ይደመጣሉ። እንደእኔ እንደኔ ግን ለኢትዮጵያ ፈጣን ልማት መመዝገብ ትልቁን ሚና የተጫወተው የዴሞክራሲያዊው ስርዓት መጎለበት መጀመሩ እንደሆነ ይሰማኛል።  ኢትዮጵያ ፍጹም አምባገነን ከሆነ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአንዴ የተሸጋገረች አገር ናት። ይህ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል።  የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ልምድን የሚጠይቅና በሂደት የሚጎለብት ነው። መልካም የዴሞክራሲ  ስርዓት  ጅምሮቻችንን በማጎልበት ደካማ ጎናችንን ማረም  ይጠበቅብናል።  
ለአገራችን ሰላም መሰረት የሆነው  ህገመንግስታችን ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  አንዳንድ ኢ-ህገመንግስታዊ የሆኑ አካሄዶችን እየተመለከትን ነው።  ዜጎች በብሄራቸው ወይም በሌላ ልዩነታቸው  ብቻ ተለይተው  በጠራራ ጸሃይ  የሚጠቁበት አካሄድ አግባብነት የጎደለው  ድርጊት ነው። መንግስትና ህዝብ   ይህን አይነት አይን ያወጣ ድርጊት ማስቆም፣ ይህን ድርጊት የሚፈጽሙትንም  ወደ ህግ ማምጣት አለባቸው።    ኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶች የሚንጸባረቁባት አገር ናት። ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚያስችል የፖለቲካ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስርዓት መከተል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።
አዲሲቷ ኢትዮጵያ  በህዝቦች መካከል የሚስተዋሉ የሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ የፖለቲካ ፍላጎቶች፣ ወዘተ አጣጥማ መጓዝ ካልቻለች መጪውን ነገር መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም። አሁን እንደቀድሞው ጊዜ ነገሮች አለባብሶ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ረግጦ በማስፈራራት ወይም በመሸንገል  ማስተዳደር አይቻልም። ጊዜው ተለውጧል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ናቸው። ህብረተሰቡ ልማት እንዲፋጠንለት  መልካም አስተዳደር   እንዲሰፍንለት ሲጠይቅ  ጸረሰላም ሃይሎች ደግሞ  የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ ለማድረግ  በአናሳዎች ላይ  ጥቃት በመሰንዘር ላይ ናቸው።  ይህ አካሄድ ለፌዴራል ስርዓታችን መልካም አይደለምና ሁሉም  በአጽንዖት ሊመለከተው  ይገባል። ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ስርዓት ለኢትዮጵያ  ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።