በትናንትናው ዕለት በኤርትራ መዲና አስመራ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ 28 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው የተለያዩ የዜና አውታሮች እየዘገቡ ይገኛሉ ።
የአገሪቱ የተቃዋሚ ኃይሎች ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ድርጊቱን እጅግ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ ነው ።
በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ማክሰኞ ዕለት በአስመራ ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን ተከትሎ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ኤርትራ ጉዞ እንዳያደርጉ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ማስተላላፉ ይታወሳል ። ኢምባሲው ባወጣው ጽሑፍ እንዳስታወቀውም በአስመራ ከተማ የተኩስ ድምጽ መሰማቱንና በተለይ ተቃውሞ ባለባቸው አካባቢዎች የአሜሪካ ዜጎች እንዳይንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርቧል ።
የቀይ ባህር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንደጻፈው “ በትናንትናው ዕለት በአሥመራ ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ 28 ዜጎች ህይወታቸውን መስዋዕት ማድረጋቸውንና 100 የሚሆኑት መቁሰላቸውን ” ተናግሯል ። ድርጅቱ ድርጊቱን በጽኑ በማውገዝም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በግድያው እጃቸውን ያስገቡትን በሙሉ ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል ።
በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉት ኤርትራውያን ለአልጀዚራ እንደተናገሩት ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ለተካሄደው የተቃውሞ ሰለፍ መነሻ የኤርትራ መንግሥት ዲያ በተባለ የሙስሊም ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ውስጥ ሂጃብን መልበስንና የሐይማኖት ትምህርትን መሥጠት በመከልከሉ ነው ብለዋል ።
በአስመራ ከተማ 3ሺህ ሙስሊሞችን ከሚያስተምረው ትምህርት ቤት የተነሳው የተቃውሞ ሰለፍ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች መዛመቱ ፍጹም ተቃውሞ በማይፈቀድባትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚካሄድባት ኤርትራ ትልቅ ትንግርት መሆኑ አስተያያት ሠጪዎች እየተናገሩ ይገኛሉ ።
የኤርትራ መንግሥት የአል ደያ የእስልምና ትምህርት ቤትን የህዝብ ትምህርት ቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ በስውዲን የምትገኘው የኤርትራውያን ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሞሮን እስጢፋኖስ ለአልጀዚራ ተናግራለች ።
የአል ዲያ ትምህርት ቤት ፕሬዚደንት ሃጂ ሙሳ በፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋል በአሥመራ ከተማ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ይበልጥ እንዳባባሰው ተገልጿል ።
በትምህርት ቤቱ ውስጥ የገቡት የኤርትራ የፀጥታ ሃይሎች ተማሪዎችን ከመደብደባቸውም በላይ በማዕከላዊ አስመራ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱትን ዜጎች በሃይል ለመበተን ተሞክሯል ።
የኤርትራው ፕሬዚደንት ቃል አቀባይና የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል የተቃውሞ ሰልፉን በትዊተር ገጻቸው ያስተባባሉ ሲሆን በአንድ ትምህርት ቤት የተነሳ ተቃውሞ በራሱ ትልቅ ሰበር ዜና መሆኑ ያስገርማል ብለዋል ።
ሌላዋ ነዋሪነቷ በእንግሊዝ ለንደን ከተማ የሆነው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ሰላም ኪዳኔ እንደምትገልጸው የኤርትራ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለመጋፋት የሚወስዳቸው ሠይጣናዊ እርምጃዎች እጅግ ዘግናኝ ናቸው ብላላች ።
ዜጎች የትኛውንም መንገድ በመጠቀም አደገኛ ሁኔታዎችን በማለፍ ጭምር ኤርትራውያን ወጣቶች አገራቸውን በመልቀቅ ላይ ይገኛሉ በማለት ሰላም አስተያየቷን ለአልጀዚራ አስተያያቷን ገልጻለች ። ( ምንጭ: አልጀዚራ)