ህዝቦችን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ህዝቦችን ለማዋሃድ እንጂ መሬትን ለማዋሃድ ያልቆመ ነው። ፌዴራላዊ ስርዓታችን ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለአንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት እውን መሆን ይተጋል። ስርዓቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ለህዝቦች የተጠናከረ ውህደት ነው። ይህም መሰረቱ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን የሚሰራውም ህዝብን ማዕከል አድርጎ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ርግጥ ባለፉት ዓመታት የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ እንዲሆኑ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ማንም አይክድም፡፡

በአሁኑ ወቅት በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋግጦላቸዋል፡፡

ርግጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ ነው። ይህን እውነታ የተገነዘበው ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የሀገሪቱ መንግሥትም ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ ነው።

የህገ-መንግስቱ ውጤትም ህዝቦች በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነው ማናቸውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ዕውን ማድረግ አስችሏል። ይህ ፍላጎታቸው እንደ መላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዓይነት መድረኮች ይንፀባረቃል። ይህን መሰሉ መድረክ ደግሞ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫ መሆኑን ከውድድሩ ተሳታፊዎች የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ስብጥር ለመገንዘብ አያዳግትም።  

እርግጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፡ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው፡፡ ይህ እውነታ በተሟላ ሁኔታ ሊገለፅ የሚችለው ልዩነትን በሚያቻችለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እናም ለሀገራችን ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል እንደሆነም አማራጭ የለውም።

ፌዴራላዊ ስርዓታችን በድቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አይደለም። ጠንካራና ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው። በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መፈቃቀድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሁም የህዝቦች አንድነት የሚገለፅበት ስርዓት ነው። ይህን የፌዴራሊዝም እሳቤን በየዓመቱ ከሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአብሮነት ማሳያ በዓል አንዱ መገለጫ ነው።

ዛሬ በሀገራችን ውስጥ የአናሳ ብሔሮች ማንነት በሁሉም መስኮች እንዲጎላና እንዲታወቅ እየተደረገ ነው። እርግጥም በሀገራችን በሁሉም መስኮች የአናሣ ማንነቶች ተሳትፎና ውክልና እያደገ መጥቷል።

ቁጥርን መነሻ ሳይደረግ ሁሉም ማንነቶች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና እንዲያገኙ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት እያንዳንዱ ማንነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ድምፁ እንዲሰማ እድል በመስጠት ከሌሎች ፌዴሬሽኖች የላቀ ርቀት የሄደ ነው ማለትም ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ በቁጥራቸው ማነስ ምክንያት በተወካዮች ምክር ቤት ሳይወከሉ ሊቀሩ ለሚችሉ አናሣ ማንነቶች እድል ለመስጠት በማሰብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሃያ  የማያንስ መቀመጫዎች ተጠብቆላቸዋል። የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎችም አናሣ ማንነቶች በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች እንዲወከሉ አድርገዋል።

ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ብዝኃነት የአብሮነትና የዕድገት ዕድል ሆኗል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ መኖር የሚችሉበትን ባህል እያዳበሩ መጥተዋል።

ታዲያ እዚህ ላይ አንድ እውነታን መገንዘብ ይገባል። እርሱም ፌዴራላዊ ስርዓቱ አልጋ በአልጋ ዕውን እየሆነ የመጣ ነው ማለት አይደለም። ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶች እንዲሁም በስርዓቱ ውስጥ የሚፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በአፈፃፀም ሂደቱ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ አሻራ ማሳረፋቸው አይቀርም።

ይሁንና እኛ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ራሱን በራሱ እያረመና እያስተካከለ የሚሄድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የሚገነባ እንዳልሆነ ሁሉ፤ እዚህ ሀገር ውስጥም የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው ነባራዊ ሃቅ ነው። እናም በሥርዓት አገነባቡ ሂደት ውስጥ ስንክሳሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ስንክሳሮች በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው።

በመሆኑም በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባሪያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሥርዓት መፍጠር ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል።

ሥርዓቱ አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያደረገ ይመስለኛል። በእኔ እምነት የኢፌዴሪ መንግስት የታገለለትንና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቶ ዛሬም ሆነ ነገ በፅናት የሚያምንበትን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማይገሰሱ መብቶች ላይ ከቶም ቢሆን ድርድር የሚያውቅ አይመስለኝም። ባለፉት 26 ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራቶች ስንቃኛቸው የሚያሳዩን ዕውነታዎች ይህንኑ ነውና።

የብሔረሰቦች መብት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለትና ለተግባራዊነቱ ህዝቦች በሙሉ የተረባረቡበት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ ገዥው ፓርቲም ይሁን የሀገራችን ህዝቦች ያላቸው አቋም የሚዛነፍ አይመስለኝም። ስርዓቱን ዕውን ለማድረግ ሲሉ የወደቁ የህዝብ ልጆችን መርሳት ስለማይቻል ነው። ከዚህ ውጭ ስርዓቱ በልዩነት ውስጥ ላለ አንድነት ዋስ ጠበቃ ሆኖ ይቀጥላል።

ፌዴራላዊ ስርዓታችን በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወቱና አንድነትን ከማጠናከር አኳያም ረጅም ርቀት መጓዙን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም ስርዓቱ የተመሰረተው በህዝቦች እንደመሆኑ መጠን እየሰራ ያለው ማናቸውም ተግባሮቹ ህዝብን መሰረት አድርጎ ስልሆነ ነው። ይህ የስርዓቱ ህዝብን መሰረት ያደረገ አሰራር የሀገራችን ህዝቦች እስካሉ ድረስ የሚቀጥል መሆኑን ማንም ሊጠራጠር አይገባም።