በሶማሊያ በደረሱት የቦንብ ፍንዳታዎች 85 ሰዎች ሲገደሉ ከ 250 በላይ ቆስለዋል

በሶማሊያዋ ሞቃዲሾ የቦንብ ፍንዳታዎች ቢያንስ 85 ሰዎች ሲሞቱ ከ250 በላይ ሰዎች ላይ  ጉዳት  መድረሱ ተገለጸ ፡፡

ጥቃቱን   ተከትሎም   የሃገሪቱ መንግስትም የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጇል፡፡

በአፍሪካ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሽብር ጥቃት ቢቀንስም አሁንም ግን ድንገት ብቅ እያለ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ በርካቶቹንም ለጉዳት እየዳረገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ቅዳሜ እለት በሶማሊያዋ መዲና ሞቃዲሾ በሁለት ተሸከርካሪዎች ላይ የተጠመዱ ቦንቦች ፈንድተው የ85 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ ከ250 በላይ ንፁሃን ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በአካባቢው የነበሩ ህንፃዎችም ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡

አልጀዚራ የዓይን እምኞችን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ይህ አደጋ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁሉ የከፋ ነው፡፡

 “ እንደዚህ አይነት ከባድ ፍንዳታ አይቼ አላውቅም፤ ተሸከርካሪው የፈነዳው በርካቶች በተሰባሰቡበት ቦታ ላይ ነው፤ ከባድ ውድመት ነው የፈጠረው፡፡ ከ20 በላይ ሰዎች ሞተው አይቻለሁ፡፡ ከ19 በላይ ህንጻዎች ወድመዋል” ብሏል ።

“ ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ እዚህ አካባቢ የነበሩ ህንፃዎች ወድመዋል፡፡ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ታድገናል፡፡ ጉዳት  የደረሰባቸው ዜጎችም እንደሚያገግሙ  ተስፋ አደርጋለሁ ” ብሏል ።

የሩሲያ ቱደይ ዘገባ ደግሞ በጥቃቱ ምክንያት ቢያንስ 22 ሆቴሎች አመድ ሆነዋል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፋርማጆ የሶስት ቀናት ብሔራዊ የሃዘን አውጀዋል፡፡ ተጠቂዎቹን ለማሰብም ፀሎት እንደሚደረግ በመግለፅ የተጎዱትን ለመታደግ ህዝባቸው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ለተጎጂዎች የሚሆንም የደም ልገሳም አከናውነዋል፡፡

ከሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር በተጨማሪም የተለያዩ መሪዎች የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ ጥቃቱን አውግዘውታል፡፡

ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም አልሸባባ ሳይሆን አይቀርም ሲል ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ከመጀመሪያው ፍንዳታ ሁለት ሰዓታት ዘግይቶ ሁለተኛው ፍንዳታ ላይ የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሏል ነው የተባለው፡፡  አረጋዊ ሰሎሞን